የኮሶቮው ፕሬዝዳንት በጦር ወንጀል በሄግ ፍርድ ቤት ቀረቡ

ፕሬዚዳንት ሃሺም ታቺ

የፎቶው ባለመብት, Reuters

ታትሟል

የኮሶቮው ፕሬዝዳንት ሃሺም ታቺ 'ዘ ሄግ' በሚገኘው የመቆያ ማዕከል ውስጥ እንደሚገኙ ተገልጿል።

ፕሬዝዳንቱ በማቆያው እንዲሆኑ የተደረገው ከጦር ወንጀል ጋር በተያያዘ ክስ ሊቀርብባቸው መሆኑን ተከትሎ ከስልጣናቸው ከወረዱ በሰአታት ውስጥ ነው።

ፕሬዝዳንቱና ሌሎች ሁለት ተጠርጣሪዎች ወደ ዓለማቀፉ ፍርድ ቤት ተወስደዋል።

በያዝነው የአውሮፐውያኑ ዓመት መጀመሪያ አካባቢ አቃቤ ሕግ ፕሬዝዳንት ሀሺም ታቺ እና ሌሎች ከአውሮፓውያኑ 1998 እስከ 99 ኮሶቮ ከሰርቢያ ነጻነቷን ለማግኘት ባደረገቸው ጦርነት ወቅት ከተገደሉ 100 ሰዎች ጋር በተያያዘ ወንጅሏቸው ነበር።

ፕሬዚዳንቱ ምንም አይነት ወንጀል እንዳልፈጸሙ ገልጸዋል።

በኮሶቮ ነጻ አውጪ ጦር ውስጥ ከፍተኛ አመራር የነበሩት የቀድሞ ወታደር ፊታቸውን ወደ ፖለቲካው በማዞር የጦር ሜዳ ወዳጆቻቸውን በማስከተል ነበር አሁን የሚገኙበት ደረጃ ላይ መድረስ የቻሉት።

ሁለት የቀድሞ የኮሶቮ ነጻ አውጪ ጦር አመራሮችም በአውሮፕላን ተጭነው ተወስደዋል።

ሃሺም ታቺ ከስልጣናቸው የወረዱት በኃላፊነት ላይ እያሉ ክስ እንዳይመሰረትባቸው በማሰብ እንደሆን አስታውቀዋል።

"ከስልጣኔ መውረዴም የአገሪቱን አብሮነትና ሉአላዊነት ለማስከበር ይረዳል" ያሉ ሲሆን ህዝቡ እንዲረጋጋም ጠይቀዋል።

ፕሬዝዳንቱ በአቃቤ ሕግ ከ100 ሰዎች ግድያ፣ ማሰቃየት እና የሰዎች ደብዛ መጥፋት ጋር በተያያዘ ክስ ከመሰረተባቸው በኋላ ከስልጣናቸው ሊለቁ እንደሚችሉ በስፋት ሲጠበቅ የነበረ ጉዳይ ነው።

ሃሺም ታቺ ከኮሶቮ የነጻነት ጦርነት መጠናቀቅ ጀምሮ በስልጣን ላይ የነበሩ ሲሆን በወቅቱ ከ10 ሺህ በላይ ሰዎች ሕይወታቸው አልፏል።

ኮሰቮ በአውሮፓውያኑ 2008 ነጻነቷን አውጃለች። አሜሪካ እና ትልልቅ የአውሮፓ አገራትም ኮሶቮን እንደ ሉአላዊት አገር ተቀብለዋታል።