በቪየና ‹የሽብር› ጥቃት የሰዎች ሕይወት አለፈ

በቪየና ‹የሽብር› ጥቃት የሰዎች ሕይወት አለፈ

የፎቶው ባለመብት, Reuters

ታትሟል

ታጣቂዎች በማዕከላዊ ቪየና ስድስት የተለያዩ ቦታዎች ተኩስ ከፍተው ሁለት ሰዎችን ገድለው በርካቶችን ማቁሰላቸውን ፖሊስ አስታወቀ።

የኦስትሪያው ቻንስለር ሴባስቲያን ኩርዝ “አስጸያፊ የሽብር ጥቃት” ባሉት ጥቃት አንድ ታጣቂም ተገድሏል ብለዋል፡፡

አንድ ጥቃት ፈጻሚ በቁጥጥር ሥር አለመዋሉን ተከትሎ ፖሊስ ፍለጋ ላይ መሆኑን የአገር ውስጥ ሚኒስትሩ ተናግረዋል፡፡

ጥቃቱ የተፈጸመው በማዕከላዊ ቪየና ማምለኪያ አቅራቢያ ቢሆንም ጥቃቱ ኢላማውን ያደረገው ማምለኪያው ላይ ስለመሆኑ አልተረጋገጠም፡፡

ከንቲባው ማእክል ሉድዊግ፤ ከተጎጂዎች መካከል አንዱ የተኩስ ልውውጡ በተፈፀመበት ቦታ የተገደለ ሲሆን ሁለተኛዋ ሆስፒታል ውስጥ ህይወቷ ማለፉን ተናግረዋል፡፡

14 ሰዎች በሆስፒታል ህክምና እየተሰጣቸው የሚቆዩ ሲሆን ስድስቱ ከባድ ጉዳት አስተናግደዋል ተብሏል፡፡

የአገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስትሩ እንዳሉት ከተጎዱት መካከል አንድ የፖሊስ መኮንን ይገኝበታል፡፡

ጥቃቱ የተከሰተው ኦስትሪያ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ የመጣውን የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ለመግታት አዲስ ብሔራዊ እገዳ ከመጣሏ ከጥቂት ሰዓታት በፊት ነው፡፡

ብዙ ሰዎች ለአንድ ወር በሚዘጉት መጠጥ እና ምግብ ቤቶች እየተዝናኑ ነበር ተብሏል፡፡

የአውሮፓ መሪዎች ጥቃቱ አጥብቀው አውግዘዋል፡፡

ስለ ጥቃቱ ምን እናውቃለን?

በቪየና ዋናው መቅደስ በሆነው አካባቢ ጥቃቱ መፈጸሙን ፖሊስ አስታውቋል፡፡

የአይሁድ ማህበረሰብ መሪ ኦስካር ዶቼ ጥቃቱ በጀመረበት ወቅት ማምለኪያ ስፍራው እንደተዘጋ በትዊተር ገፃቸው ገልፀዋል።

ከተጎጂዎች መካከል የማምለኪያ ስፍራው የሚጠብቅ መኮንን አንዱ መሆኑን የሃገሪቱ ጋዜጣ ዘግቧል፡፡

በጥቃቱ ምን ያህል ሰዎች እንደተሳተፉ ግልጽ አልሆነም፡፡

የአገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስትሩን ጠቅሰው የኦስትሪያ መገናኛ ብዙሃን አንድ ሰው መያዙን ተናግረዋል፡፡

የተኩስ ድምጽ ሲሰማ ሰዎች በጎዳናዎች ላይ ሲሮጡ በማኅበራዊ አውታረ መረቦች ላይ የተለጠፉ ቪዲዮዎች አሳይተዋል፡፡

የተኩስ ልውውጡ ሲጀመር ክሪስ ዣዎ የተባሉ ግለሰብ በአቅራቢያው ባለምግብ ቤት ነበሩ፡፡

ዣዎ ለቢቢሲ እንደገለጹት፤ “ርችት የሚመስል ድምጽ ሰማን። ከ 20 እስከ 30 ያህል ጊዜ ሰምተናል። እናም በትክክል የተኩስ ድምጽ ነው ብለን አሰብን፡፡ አምቡላንስ ሲያልፍ አየን፡፡ ተጎጂዎችም ነበሩ። የሚያሳዝነው አንደ ሰው ተመቶ ወድቆ ከጎናችን አይተናል” ብለዋል።

ሰዎች ከአካባቢው እንዲርቁ እና የህዝብ ማመላለሻ ትራንስፖርት እንዳይጠቀሙ ፖሊስ አሳስቧል፡፡

ፖሊስ በከተማው ማዕከል ዙሪያ መንገዶችን ዘግቷል።

የጎረቤት አገር ቼክ ሪፐብሊክ ፖሊስ ታጣቂዎቹ ወደዚያ አቅጣጫ ሊያቀኑ ይችላሉ በሚል ስጋት በኦስትሪያ ድንበር ላይ ድንገተኛ ፍተሻ መጀመሩን ገልጿል፡፡