ታጣቂዎች በካቡል ዩኒቨርሲቲ 19 ሰዎች ገደሉ

የፎቶው ባለመብት, REUTERS
ታጣቂዎች ካቡል ዩኒቨርሲቲ ገብተው አስራ ዘጠኝ ሰዎች ገደሉ።
ታጣዊዎቹ ከፀጥታ ኃይሎች ጋር ለሰዓታት የዘለቀ የተኩስ ልውውጥ አድርገዋል።
የአፍጋኒስታን የአገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ እንደተናገሩት ጥቃቱ የቆመው ሶስት ታጣቂዎች ከተገደሉ በኋላ ነው።
ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ቢያንስ 22 ሰዎች ቆስለዋል ሲል መግለጫ አውጥቷል።
የመንግሥት ባለሥልጣናት በዩኒቨርሲቲው ቅጥር ግቢ የሚከናወነውን የኢራን መፃሕፍት አውድ ርዕይ ለመታደም በተጠሩበት ሰዓት ነው።
ታሊባን በጥቃቱ እጁ እንደሌለበት አስታውቆ ጥቃቱን ኮንኖታል።
ኢስላሚክ ስቴት ከቅርብ ጊዜ ወዲህ አፍጋኒስታን ውስጥ ያሉ የትምህርት ማዕከላት ላይ ጥቃት እያደረሰ ይገኛል።
ባለፈው ወር አይኤስ ከካቡል ወጣ ብሎ የሚገኝ የትምህርት ማዕከል ላይ ጥቃት አድርሶ 24 ሰዎች መሞታቸው አይዘነጋም።
በአውሮፓውያኑ 2018 ከካቡል ዩኒቨርሲቲ ፊት ለፊት ለደረሰው ጥቃት ኃላፊነት የወሰደው አይኤስ ነበር።
ዛሬ [ሰኞ] የደረሰውን ጥቃት የሚያሳዩ ተንቀሳቃሽ ምስሎች ማሕበራዊ ድር አምባዎች ላይ ተንሰራፍተዋል። ተማሪዎች ጥቃቱን በመሸሽ ሲሮጡ በምስሉ ላይ ተመልክቷል።
የሃገር ውስጥ ጉዳይ ቃል አቀባይ ታሪቅ አርያን ከታጣቂዎቹ አንዱ ፈንጂ አፈንድቷል ብለዋል።
ታሊባን ከአፍጋኒስታን መንግሥት ጋር በኳታር ዋና ከተማ ዶሃ ውስጥ ንግግር ቢያደርጉም አፍንጋኒስታን ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ሰላም ርቋታል።
የተባበሩት መንግሥታት አል-ቃኢዳ አሁንም ከታሊባን ጋር እጅና ጓንት ነው ይላል።
ነገር ግን ታሊባን ከአል-ቃኢዳ ጋር አብሮ እየሠራ እንዳልሆነ ለአሜሪካ መንግሥት ማሳወቁ አይዘነጋም።












