የፍልስጤም ዋና ተደራዳሪ በጠና ታመው ወደ የእስራኤል ሆስፒታል ተወሰዱ

የፍልስጤም ዋና ተደራዳሪ ሳኢብ ኢሬካት

የፎቶው ባለመብት, Reuters

ታትሟል

የፍልስጤም ዋና ተደራዳሪ ሳኢብ ኢሬካት በጠና ታመው በእስራኤሉ ሆስፒታል ሕክምና እየተደረገላቸው ይገኛል።

የፍልስጤም ዋና ተደራዳሪ ሳኢብ ኢሬካት በኮቪድ-19 ከተያዙ በኋላ የጤናቸው ሁኔታ አሳሳቢ ሁኔታ ላይ እንደሚገኙ ሕክምና እያደረገላቸው የሚገኘው ሆስፒታል ገልጿል።

ትናንት ጠዋት ላይ ሳኢብ ኢሬካት ሕመማቸው እየተባባሰ ሲመጣ ከመኖሪያ ቤታቸው ወጥተው ለእየሩሳሌም ቅርበት ወዳለው የዌስትባንክ ዩኒቨርሲቲተ ሆስፒታል እንዲገቡ ተደርገዋል።

ሳኢብ ኢሬካት በኮሮረናቫይረስ የተያዙት በያዝነው ወር መጀመሪያ አካባቢ ላይ ነበር።

የ65 ዓመቱ ተደራዳሪ እአአ 2017 ላይ ሳንባ ንቅለ ተከላ አድርገው ስለነበር አፋጣኝ ህክምና እንዳስፈለጋቸው የፍልስጤም ነጻነት ድርጅት አስታውቋል።

ድርጅቱ ባወጣው መግለጫ ላይም ሳኢብ ኢሬካት ወደ ሆስፒታል ሲወሰዱ የጤናቸው ሁኔታ በጣም አሳሳቢ የሚባል እንደነበረና አፋጣኝ ህክምና ያስፈልጋቸው እንደነበር ገልጿል።

''በአሁኑ ሰአት ከፍተኛ እውቀት ባላቸው ባለሙያዎች አጋዥነት ሕክምናቸውን እየተከታተሉ ነው። ሁሉም የህክምና ቡድኑ አባላት እሳቸው ቶሎ እንዲያገግሙ የተቻላቸውን በሙሉ ያደርጋሉ'' ብለዋል በሆስፒታሉ የሚሰሩት ፕ/ር ዚቭ ሮቲስቴይን።

ሳኢብ ኢሬካት ፍልስጤም ከእስራኤል ጋር በምታደርገው ድርድር ውስጥ ቁልፍ የሚባሉ ሰው ሲሆኑ ላለፉት በርካታ ዓመታትም በዋነኛ ተደራዳሪነት ሲያገልግሉ ቆይተዋል።

የፍልስጤም ነጻነት ድርጅት እሁድ ዕለት ባወጣው መግለጫ ''ሳኢብ ኢሬካት በኮሮረናቫይረስ ከመያቸው በፊትም ሌላ የጤና እክል ስላለባቸው የመተንፈሻ ችግር አጋጥሟቸዋል፤ ከፍተኛ የሕክምና ክትትል ያስፈልጋቸዋል'' ብሏል።

የአይን እማኞች ለሬውተርስ የዜና ወኪል እንደገለጹት ሳኢብ ሬካት ከመኖሪያ ቤታቸው የወጡት በስትሬቸር ላይ ተደርገው ሲሆን በእስራኤል አምቡላንስም ተወስደዋል።