የተባበሩት አረብ ኢምሬትስ ሚኒስትር ኣሼክ ናህያን በወሲብ ትንኮሳ ተከሰሱ

ሼክ ናህያን

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, ሼክ ናህያን
ታትሟል

ሼክ ናህያን 69 ዓመታቸው ነው፡፡ ከሳሻቸው ካትሊን ማክ ናማራ ትባላለች፡፡ እንግዛዊት ናት፡፡ ባለፈው ዓመት ሼኩ በአቡዳቢ ወሲባዊ ትንኮሳ አድርሰውብኛል ብላለች፡፡

ሁለቱን ያገናኛቸው ዝነኛው የሄይ የሥነ ጽሑፍ ፌስቲቫል ነው፡፡

ሄይ የሥነ ጽሑፍ ፌስቲቫል በዓለም ላይ የሚገኙ ደራሲዎችን፣ አታሚዎችንና አሳታሚዎችን ከአንባቢዎች ጋር በአንድ የሚያገናኝ ታዋቂ ፌስቲቫል ሲሆን በየዓመቱ በመቶ ሺዎች የሚታደሙበት ፌስቲቫል ነው፡፡

ይህ ፌስቲቫል ቀጣዩ ዙር በአቡዳቢ እንዲካሄድ ንግግር ተጀምሮ ነበር፡፡

ሼክ ናህያን ቢን ሙባራክ አልናህያን ደግሞ በተባበሩት አረብ ኢምሬትስ ‹‹የመቻቻልና የታጋሽነት›› ሚኒስትር ናቸው፡፡ ከመቻቻልና ታጋሽነት ሚኒስትር ጋር በተባበሩት አረብ ኢምሬትስ የደስታ ሚኒስቴር ይጠቀሳል፡፡

ይህ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤት የባሕልና ተያያዥ ጉዳዮች የሚመለከቱት ነው፡፡ ይህንን መሥሪያ ቤት በሚኒስትርነት የሚመሩት ሰው ናቸው ታዲያ በወሲባዊ ትንኮሳ የተከሰሰቱት፡፡

የዚህ ሄይ ፌስቲቫል ሠራተኛ የነበረችውን ሴት ካትሊን ማክናማርን ተንኩሰዋል በሚል ከተወነጀሉ በኋላ ፌስቲቫሉ ተሰርዟል፡፡

የሄይ ፌስቲቫል ሊቀመንበር ካሮላይን ሚሸል ‹ሼክ ናህያን በሚኒስትርነት እያሉ ፌስቲቫሉ በአቡዳቢ እንዲካሄድ አንፈቅድም›› ብለዋል፡፡

ሼክ ናህያን በበኩላቸው ድርጊቱን አልፈጸምኩም ሲሉ አስተባብለዋል፡፡

የ32 ዓመቷ ማክናማራ ለሰንደይ ታይምስ ጋዜጣ እንደተናገረችው ትንኮሳው የደረሰባት በፌብሩዋሪ 14 በአቡዳቢ ውስጥ ነበር፡፡

‹‹ከአቡዳቢ ራቅ ብሎ በሚገኝ ደሴት ላይ ባለ አንድ ቪላ ስለ ፌስቲቫሉ ለመነጋገር በተጋበዝኩበት ወቅት ነበር ሼኩ ሚኒስትር ትንኮሳ ያደረሱብኝ›› ብላለች፡፡

በዚያ ወቅት በፌስቲቫሉ ታሪክ ለመጀመርያ ጊዜ በአቡዳቢ ሊካሄድ የቀሩት 11 ቀናት ብቻ ነበሩ፡፡

ትንኮሳው ከተፈጸመባት በኋላ ለሰራተኞቿና ባልደረቦቿ ጉዳዩን ያሳወቀች ሲሆን ለእንግሊዝ ኤምባሲም ስለ ጉዳዩ ሪፖርት አድርጊያለሁ ብላለች፡፡

በእንግሊዝ የኮቪድ የእንቅስቃሴ ገደብ ሲነሳም ወደ ፖሊስ ሄዳ ቃሏን ሰጥታለች፡፡

ማክናማራ ለጋዜጣው እንደተናገረችው ከሆነ ስሟንና ማንነቷን መሸሸግ እየቻለች ያንን ማድረግ ያልመረጠችው በምክንያት ነው፡፡

‹‹እንደሳቸው ያለ ትልቅ ሥልጣንና ገንዘብ እንዲሁም ዝና ያላቸው ወንዶች በሴቶች ላይ የሚያደርሱትን አድርሰው ምንም አንሆንም ብለው ያስባሉ፡፡ ይህን አስተሳሰብ ለመፋረስ ነው በይፋ ክሱን የመሰረትኩት ብላለች፡፡

እኚህ ባለሥልጣን ጥቃት ሲያደርሱ ምናልባት እኔ የመጀመርያዋም የመጨረሻዋም ሴት ላልሆን እችላለሁ፡፡ ነገር ግን ያደረሱብኝ ጠባሳ ከባድ ነው። ለሳቸው ግን ተራ ቅጽበታዊ ክስተት ሊሆን ይችላል ብላለች፡፡

ሰንደይ ታይምስ ጋዜጣ ሼክ ናህያንን ለማግኘት ያደረገው ሙከራ አልተሳካለትም፡፡ ሆኖም ሼኩን በሎንዶን የሚወክላቸው የጠበቆች ቡድን በጉዳዩ ምላሽ ሰጥቷል፡፡

‹‹ደንበኛችን ተፈጸመ ከተባለ 8 ወራት ያለፈውን ወሲባዊ ትንኮሳ ክስ በመስማታቸው አዝነዋል፣ ተደናግጠዋልም፡፡ ድርጊቱ ሐሰት ነው›› ብሏል የጠበቆቻቸው ቢሮ፡፡

የሄይ የሥነጽሑፍ ፌስቲቫል ሊቀመንበር ካሮላይን ሚሸል በትዊተር ሰሌዳቸው እንደጻፉት ‹በሴት ሰራተኛቸው ላይ ባለፈው ፌብሩዋሪ በአቡዳቢ የደረሰው ጾታዊ ጥቃት አሳፋሪ በመሆኑ በመናገር ነጻነትና ሴቶችን በማብቃት ላይ የተሰነዘረ ጥቃት አድርገው ስለተመለከቱት ፌስቲቫሉ ወደ ሌላ አገር ተዛውሯል፡፡

‹‹ሰራተኛችንን የክሱን ሂደት እንድትገፋበት ሙሉ ድጋፍ የምናደርግ ሲሆን እኚህ ሚኒስትር በቦታቸው ሳሉ ግን ፌስቲቫሉን ወደ አቡዳቢ እንደማንወስደው እናረጋግጣለን›› ብለዋል ሊቀመንበሯ፡፡