ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ቮልስዋገን ለቀድሞ የብራዚል ሠራተኞቹ 6.4 ሚሊዮን ዶላር ካሳ ሊሰጥ ነው
ቮልስዋገን ለቀድሞ የብራዚል ሠራተኞች 6.4 ሚሊዮን ዶላር ካሳ ሊከፍል ነው።
የጀርመኑ መኪና አምራች ቮልስዋገን ቀድሞ በብራዚል ይሠሩ ለነበሩ ተቀጣሪዎቹ 6.4 ሚሊዮን ዶላር ካሳ ሊሰጥ ነው። ሠራተኞቹ ቮልስዋገን ከቀድሞው የአገሪቱ ወታደራዊ አገዛዝ ጋር ተባብሯል ብለው ክስ መስርተው ነበር።
ድርጅቱ የሰብአዊ መብት ጥሰት ፈጽሟል ሲሉ ሠራተኞቹ እና ቤተሰቦቻቸው ከአምስት ዓመታት በፊት ከሰዋል።
እአአ 2016 ላይ የወጣ ሪፖርት እንደሚያሳየው የቮልስዋገን ወኪሎች የሠራተኞችን ስም ለፖሊስ አስተላልፈዋል።
ሠራተኞቹ ታግተው እንግልት ደርሶባቸዋል።
የቮልስዋገን ዋና ኃላፊ ሂልተርድ ወርነር “ከዚህ ቀደም የደረሰው እንግልት አሳዝኖናል። በብራዚል የደረሰው ነገር በድርጅቱ ታሪክ ጥቁር ነጥብ ጥሎ አልፏል። ስለዚህም ኃላፊነትና ግልጽነት በተሞላው ሁኔታ ልንይዘው ይገባል” ብለዋል።
ድርጅቱ ከሚሰጠው ካሳ በተጨማሪ በአምባገነኑ ሥርዓት ለተጎዱ ሰዎች መታሰቢያ ሃውልት ለማሠራትም ተስማምቷል።
12 የቀድሞ ሠራተኞች በ2016 በቮልስዋገን ፋብሪካ ውስጥ ታስረው እንደተንገላቱ ተናግረዋል። ሌሎች ደግሞ ከሥራ ተባረዋል።
የድርጅቱ ጠባቂዎች የኮሚኒስት በራሪ ወረቀት የነበራቸው ሠራተኞችን እየተቆጣጠሩ ለወታደራዊ ኃይሉ መረጃ ይሰጡ እንደነበረም በምርመራ ተደርሶበታል።
በቢንፊልድ ዩኒቨርስቲ የታሪክ መምህር የሆኑት ፕ/ር ክሪስቶፈር ኮፐር “የቮልስዋገን አመራሮች ለወታደራዊው መንግሥት ታማኝ ነበሩ” ይላሉ።
የብራዚል የእውነት ኮሚሽን 2014 ላይ ያወጣው ሪፖርት ሉስዮ ቤለንታኒ የተባለ ሠራተኛን ታሪክ ይዳስሳል።
ወታደራዊው አገዛዝ ሰዎችን በሕግ ወጥ መንገድ ያስር፣ ያሰቃይ፣ ይገድልም እንደነበር የኮሚሽኑ መግለጫ ይጠቁማል። የኮምኒስት አቀንቃኙ ሉስዮ ሥራ ላይ ሳለ ሁለት ግለሰቦች መሣሪያ ይዘው እንደወሰዱት ያስታውሳል።
“እጄን የፊጥኝ አሰሩኝና ቮልስዋገን የጸጥታ ክፍል ውስጥ ወስደው ደበደቡኝ።”
ከ400 በላይ ሰዎች እንደተገደሉና ወደ 40,000 ሰዎች እንደተሰቃዩ የኮሚሽኑ ሪፖርት ያሳያል።
አገሪቱ በወታደራዊው አገዛዝ ከደረሰው ሰቆቃ ገና እያገገመች ነው።
ቀኝ ዘመሙ ፕሬዘዳንት ዣቪር ቦልሶናሮ የቀድሞውን አምባገነን ሥርዓት ሲያሞግሱ ተደምጠዋል። አንዳንድ የቀድሞው መርሆች ዳግመኛ መተግበር አለባቸውም ብለዋል።