የአሜሪካ ምርጫ፡ ሪፓብሊካኖች ብንሸነፍ ሥልጣን በሰላም እናስረክባለን አሉ

ታትሟል

የሪፐብሊካን መሪ ሚች መካኖል ከምርጫው በኋላ በትክክለኛው መንገድ የሥልጣን ሽግግር ይካሄዳል አሉ።

ሚች መካኖል በኅዳሩ ምርጫ ማንም ያሸንፍ ማን ሕጋዊ የሆነ የስልጣን ሽግግር ይካሄዳል ብለዋል።

የአሜሪካው ፕሬዘዳንት ዶናልድ ትራምፕ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ “የሚሆነውን እናያለን” ብለው ነበር።

ሚች መካኖል ግን ምርጫውን ማንም ያሸንፍ ማን በሰላማዊ መንገድ ሥልጣን ወደ ቀጣዩ መሪ ይሻገራል ሲሉ ተናግረዋል።

ትራምፕ በፖስታ ድምጽ የመስጠት ሂደት ላይ ጥርጣሬ እንዳላቸው ቢናገሩም የምርጫ ኃላፊዎች ግን የፖስታ ምርጫ አስተማማኝ መሆኑን ተናግረዋል።

ብዙ ግዛቶች መራጮች ለኮሮናቫይረስ እንዳይጋለጡ ድምጻቸውን በፖስታ እንዲልኩ እያበረታቱ ነው።

ትራምፕ የምርጫውን ውጤት አልቀበልም ካሉ ምን እንደሚከሰት በግልጽ አልታወቀም።

ተፎካካሪያቸው ጆ ባይደን እንደሚሉት፤ ትራምፕ ውጤቱን አልቀበልም ካሉ የአገሪቱ መከላከያ ከዋይት ሀውስ ያስወጣቸዋል።

የሪፐብሊካኖች ምላሽ

ሚች መካኖል “የኅዳሩን ምርጫ የሚያሸንፈው ሰው ጥር ላይ በዓለ ሲመቱ ይካሄዳል። ከ1972 ጀምሮ እንደነበረው ይህ ሂደት ዘንድሮም ሰላማዊ ይሆናል” ብለዋል በትዊተር ገጻቸው ላይ።

ሌሎች ሪፐብሊካኖችም ፍትሐዊ ምርጫ ይካሄዳል ብለዋል።

ከሪፐብሊካኖች አንዱ ሊንዚ ግርሀም “ሰላማዊ እንደሚሆን ላረጋግጥላችሁ እወዳለሁ። ውጤቱ ወደ ከፍተኛው ፍርድ ቤት ያመራል። ሪፐብሊካኖች ካሸነፍን እንቀበላለን። ፍርድ ቤቱ አሸናፊው ጆ ባይደን ነው ካለ እቀበላለሁ” ሲሉ ለፎክስ ኒውስ ተናግረዋል።

ሌላው ሪፐብሊካን ሚት ሮምኒ “ሰላማዊ የሥልጣን ሽግግር የዴሞክራሲ መሠረት ነው። ሕገ መንግሥቱን የማይቀበል ፕሬዘዳንት ተቀባይነት አይኖረውም” ሲሉ በትዊተር ገጻቸው ላይ አስፈረዋል።

ትራምፕ ያሉት ምንድን ነው?

ትራምፕ በፖስታ ድምጽ የመላክ ሂደት አስተማማኝ እንዳልሆነና ምርጫው በትክክለኛ መንገድ ይካሄዳል ብለው እንደማያምኑ ተናግረዋል።

ፕሬዘዳንቱ ይህን ከማለታቸው ቀደም ብሎ የዋይት ሀውስ ቃል አቀባይ “የነጻና ፍትሐዊ ምርጫ ውጤትን ይቀበላሉ” ብላ ነበር።

ባይደን ትራምፕን ካሸነፏቸው ትራምፕ ሥልጣን በሰላም ያስረክቡ እንደሆነ በጋዜጠኛ ተጠይቀው ነበር። እሳቸውም “በፖስታ ድምጽ የመስጠት ሂደት ላይ ቅሬታዬን ሳሰማ ነበር። ውጤታማ አይሆንም” ብለዋል።

ሕዝቡ ተቃውሞውን እያሰማ ስለመሆኑ ሲጠየቁ “በፖስታ ድምጽ መስጠት ከተወገደ ሰላማዊ ምርጫ እናካሂዳለን” የሚል ምላሽ ሰጥተዋል።

እአአ በ2016 ትራምፕ በሂላሪ ክሊንተን ከተሸነፉ ውጤቱን እንደማይቀበሉ መግለጻቸው አይዘነጋም።

የዴሞክራቶች ምላሽ

የምክር ቤቱ አፈ ጉባኤ ዴሞክራቷ ናንሲ ፔሎሲ ትራምፕ ሰላማዊ የሥልጣን ሽግግር አልቀበልም ማለታቻው ብዙም እንዳላስገረማቸው ተናግረዋል።

የሩስያው ቭላድሚር ፑቲን፣ የሰሜን ኮርያው ኪም ጆንግ ኡን እና የቱርኩን ረሲፕ ታይፕ ኤርዶዋን በማጣቀስ፤ “ትራምፕ ሥልጣናቸውን የሚበዘብዙ መሪዎች አድናቂ ነው” ብለዋል።

ፔሎሲ አያይዘውም “ያለነው ሰሜን ኮርያ፣ ቱርክ ወይም ሩስያ እንዳልሆነ ላስታውሰው እወዳለሁ። ስለዚህም ሥልጣን ሲይዝ የገባውን ቃል ያክብር” ብለዋል።

ባይደን የትራምፕ ንግግር “ምክንያት አልባ ነው” ብለው ምላሽ ሰጥተዋል።

የተቀሩት ዴሞክራቶችም “አሜሪካ መርህ የሚጥሱን ከዋይት ሀውስ በሰላም ማስወገድ ትችላለች” ሲሉም የባይደንን ሐሳብ አጠናክረዋል።

ባይደን “ዶናልድ ትራምፕ በድጋሚ ቢመረጥ አሜሪካ ውስጥ የሰላም መደፍረሱ ይቀንሳል ብሎ የሚያስብ ሰው አለ?” በማለት አለመረጋጋት እንዲፈጠር አድርገዋል በሚል ይተቻሉ።

ባለፈው ወር የቀድሞዋ የትራምፕ ተፎካካሪ ሂላሪ ክሊንተን “በማንኛውም ሁኔታ እጅ መስጠት የለብህም” በማለት ለባይደን መልዕክት አስተላልፈዋል።