ለደቡብ ኮርያው ባለስልጣን ግድያ ኪም ጆንግ ይቅርታ ጠየቁ

ታትሟል

አንድ የደቡብ ኮርያ ባለስልጣን በሰሜን ኮሪያ ወታደሮች መገደሉን ተከትሎ የሰሜን ኮርያው መሪ ኪም ጆንግ ኡን ባልተለመደ መልኩ ይቅርታ መጠየቃቸውን የደቡብ ኮሪያ ፕሬዝዳንት ጽ/ቤት አስታወቀ።

ኪም ጆንግ ኡን ለደቡብ ኮሪያ ፕሬዝደንት ሙን ጄ ኢን በላኩት ደብዳቤ ላይ የደቡብ ኮሪያው ባለስልጣን መገደል እንዳሳዘናቸው ገልጸዋል።

አደጋው ከነጭራሹ መከሰት አልነበረበትም ማለታቸው ተገልጿል።

የደቡብ ኮሪያ ኮርያ ባለስልጣናት የ47 ዓመት ደቡብ ኮርያዊ ሰሜን ኮሪያ ጥገኝነት ለመጠየቅ ወደ ሰሜን ኮሪያ የውሃ ክልል መግባቱን ተከትሎ በወታደሮች ተይዟል ይላሉ።

በመቀጠልም ተተኩሶበት ከተገደለ በኋላ አስክሬኑ በእሳት እንዲቃጠልም ተደርጓል ብለዋል የደቡብ ኮርያ ባለስልጣናት።

የሁለቱ ኮርያዎች አዋሳኝ ድንበር እጅግ ጠንካራ ጥበቃ ከሚደረግላቸው ድንበሮች መከካል አንዱ ሲሆን ሰሜን ኮሪያ ደግሞ የኮሮረናቫይረስ ስርጭትን ለመከላከል ወደ ድንበሯ ለመግባት የሚሞክሩ ሰዎችን ተኩሶ መግደል ፈቅዳለች ተብሏል።

የኪም ጆንግ ኡን የይቅርታ ደብዳቤ ቀጥታ የተላከው ለፕሬዝዳንት ሙን ጄ ኢን ሲሆን ለተፈጠረው ነገር ይቅርታ ከጠየቁ በኋላ ክስተቱ ከነጭራሹ መፈጠር አልነበረበትም ማለታቸውን ኃላፊዎች አስታውቀዋል።

ኪም ''በተጠረው ነገርና ፕሬዝዳንት ሙን ጄ ኢንን በማሳዘኔ በጣም አዝኛለሁ'' ማለታቸውን ዮንሃፕ የዜና ወኪል ዘግቧል።

ሰሜን ኮሪያ ከዚህ በተጨማሪ ስለግድያው ተጨማሪ መረጃዎችን ያጋራች ሲሆን ሟች አስር ጊዜ ጥይት እንደተተኮሰበትም ገልጻለች።

በማከልም ኃላፊው ከተገደለ በኋላ አስክሬን እንዳልተቃጠለና በእሳት የተቃጠለው ግን ሰውዬው የነበረበት መንሳፈፊያ መሳሪያ እንደሆነ ተገልጿል።