ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
የእስራኤልና ገልፍ አገራት ስምምነት በጋዛ ግጭትን አቀጣጠለ
የእስራኤልና የገልፍ አገራት (የአረቡ አለም) ግንኙነታቸውን በማደስ ሰላም ማውረዳቸውን ተከትሎ በጋዛ ያለው ግጭት እንደ አዲስ ተቀጣጥሏል።
ሁለቱ የገልፍ አረብ አገራት በዋሽንግተን ከእስራኤል ጋር ስምምነት መፈራረማቸው በጋዛ ውስጥ የእስራኤል ጦርና የፍልስጥኤም ታጣቂዎች አንዲፋጠጡ ምክንያት ሆኗል ተብሏል።
የፍልስጥኤም ታጣቂዎች በእስራኤል ላይ ሁለት ሮኬቶች በትናንትናው ዕለት ያስወነጨፉ ሲሆን፤ አንደኛው ሮኬትም የባህር ዳርቻ ከተማዋን አሽዶድ ላይ አርፎ ሁለት ግለሰቦችም መቁሰላቸው ተዘግቧል።
በዛሬው ዕለትም 13 ሮኬቶችን ንጋት ላይ ተወንጭፈዋል ተብሏል።
እስራኤልም በአፀፋው የፍልስጥኤሙ ሃማስ ይዞታ ነው በሚባሉ የጋዛ ቦታዎችን በቦምብ ደብድባለች።
በታሪካዊው ቀንም የፍልስጥኤም ታጣቂዎች እስራኤልን ማጥቃታቸው ብዙ እንዳላስደነቃቸው የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትርን ቤንያሚን ኔታንያሁ ዋሽንግተን ላሉ ሪፖርተሮች ተናግረዋል።
"ሰላም እንዲሆን አይፈልጉም ይህ ደግሞ መቼም አይሳካላቸውም። ሊጎዱን እጃቸውን በሚያነሱ ሁሉ የአፀፋ ምላሻችን የከፋ ይሆናል" ብለዋል ጠቅላይ ሚኒስትሩ
ጋዛን የሚቆጣጠረው ሃማስ በበኩሉ እስራኤል "በህዝባችን ላይ የምታደርሰው ግድያና በምታደርሰው በደል ዋጋዋን የምታገኝ ይሆናል" ብሏል።
"ወራሪዋ እስራኤል በያዘችው ቦታ ላይ በዚሁ በወራሪነትዋ የምትቀጥል ከሆነ ምላሻችንም እየጨመረ ይሄዳል" ብሏል።
የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ናታንያሁና የተባበሩት አረብ ኤምሬትስና ባህሬን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች በአሜሪካው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ አሸማጋይነት ታሪካዊ የተባለውን ስምምነት ፈርመዋል።
ዶናልድ ትራምፕ የእስራኤልና የአረቡ አለም መቀራረብ በግጭት በሚናጠው መካከለኛው ምስራቅ ላይ ሰላም ያሰፍናል ብለዋል።
ሆኖም ይህ ሁኔታ ፍልስጥኤማውያንን አስቆጥቷል፤ እንደ ክህደትም ነው ያዩት።
ፍልስጥኤም ራሷን የቻለች አገር ሆና እስክትቆም እንዲሁም በፍልስጥኤማውያን ነፃነት ዙሪያ ላለመደራደርም የትኛውም አረብ አገር ቃል ገብተው ነበር።ፍልስጥኤማውያን መድኃኒት በልመና፣ መብራት በፈረቃ ነው የሚያገኙት፡፡
የፍልስጥኤም ግዛት ፕሬዚዳንት ማህሙድ አባስ "የእስራኤል ወራሪነትና የተቆጣጠረቻቸውን የፍልስጥኤም ግዛቶች እስካልለቀቀች ድረስ ሰላም ደህንነትና መረጋጋት በቀጠናው አይኖርም" ብዋል።
ከተባበሩት አረብ ኤምሬትስና ባህሬን በፊት ለእስራኤል እውቅና የሰጧት ሁለቱ የአረብ አገራት ግብፅና ዮርዳኖስ ነበሩ።