ከማንዴላ ጋር አብረው ከታሰሩት መካከል የመጨረሻው ግለሰብ አረፉ

ታትሟል

አንድሪው ምላንጌኒ ከኔልሰን ማንዴላ ጋር ፀረ-አፓርታይድ እንቅስቃሴ አራምዳችኋል ተብለው ከታሠሩ ሰዎች መካከል በህይወት የቀሩ የመጨረሻው ነበሩ።

ሰውዬው በ95 ዓመታቸው ባደረባቸው ህመም አርፈዋል።

የሪቮኒያ ችሎት በመባል ይታወቃል። ማንዴላና አጋሮቻቸው ለምን አፓርታይድን ተቃወማችሁ ተብለው የተከሰሱበትና የተቀጡበት መድረክ ነው። ይህ ችሎት ማንዴላን ከዓለም ያስተዋወቀ ነው ይባልለታል።

ፕሬዝደንት ሲሪል ራማፎሳ የምላንጌኒ መሞት የታሪካዊው ትውድል ማብቂያ ምልክት ነው። ቀጣዩ ታሪክ ሰሪዎች እኛ ነን ሲሉ ተደምጠዋል።

ምላንጌኒ ማናቸው?

የምላንጌኒን ሕይወት የሚዳስስ መፅሐፍ የታተመው ከሦስት ዓመት በፊት ነው። 'ዘ ባክሩም ቦይ' የተሰኘ ርዕስ አለው።

ማንዴላ፤ ምላንጌኒን ጨምሮ አምስት ፀረ-አፓርታይድ አራማጅ ደቡብ አፍሪካውያን ቻይና ሄደው ሥልጠና እንዲወስዱ ልከዋቸው ነበር። ሥልጠናው ፈንጂ መሥራት፣ ደፈጣ ውጊያ እንዲሁም ምስጢራዊ ግንኙነትን የተመለከተ ነበር።

ሰውዬው ወደ ደቡብ አፍሪካ የተመለሱት በአውሮፓውያኑ 1963 ነው። ከዚያም የኤኤንሲ አመራር ሆነው ተሾሙ።

ማንነታቸውን ሸሽገው ቄስ በመምሰል ደቡብ አፍሪካን በመዞር ለትግል የሚሆኑ ወጣቶችን መልምለዋል። በስተመጨረሻ ግን ተይዘው በአገር ክህደት ወንጀል ተከሰሱ።

ምላንጌኒ፤ 26 ዓመታትን በእስር አሳልፈዋል። እኒህን የእስር ጊዜያት ያሳለፉት ሮቢን ደሴት በሚገኝ እስር ቤት ሲሆን ማንዴላም አብረዋቸው ነበሩ።

ሰውዬው በ1989 ከእሥር ከተፈቱ በኋላ በደቡብ አፍሪካ ፓርላማ የሕዝብ እንደራሴ ሆነው አገልግለዋል። እስከ ዕለተ ሞታቸው የኖሩትም ሶዌቶ በተሰኘችው መንደር ነው።

ምላንጌኒ፤ አቋማቸው የፀና ሰው እንደነበሩ ብዙዎች ይመሰክራሉ። በዚህም በርካታ ደቡብ አፍሪካውያን ይኮሩባቸዋል።

ራሳቸውን 'ዘ ባክሩም ቦይ' ሲሉ ነው የሚገልፁት። በግርድፉ ከመጋረጃው በስተጀርባ ያለሁ ሰው ነኝ ይላሉ። ፖለቲካዊ እውቅና እንደማይሹ ወዳጅ ዘመዶቻቸው ይናገራሉ።

ደቡብ አፍሪካ በነጭ የበላይነት ከሚተዳደረው የአፓርታይድ ሥርዓት አገዛዝ ተላቃ እንደ አዲስ ራሷን እንድትገነባ የበኩላቸውን አበርክተዋል።

ከምላንጌኒ ጋር በሪቮኒያ የፍርድ አደባባይ ኦፓርታይድን በመቃወማቸው ክህደት ፈፅማችኋል ተብለው የተፈረደባቸው አጋሮቻቸው ሁሉም ይህችን ዓለም ተሰናብተዋል። ምላንጌኒ የመጨረሻው ሰው ናቸው።

ምላንጌኒ ጥቁሮች መብታቸው ሊከበር ይገባል ሲሉ ተሟግተዋል። ስለአንድነትም ብዙ አቀንቅነዋል።

የሪቮኒያ ችሎት ማንዴላ፣ ምላንጌኒና ሌሎች ስድስት ደቡብ አፍሪካውያን በነጭ የአፓርታይድ አገዛዝ ዘመን ለረዥም ዓመታት እስር ተላልፈው የተሰጡበት ነው። አብዛኛዎች የ26 ዓመታት ፍርድ ሲቀበሉ ማንዴላ 27 ዓመታት እስር ተፈረደባቸው።

በ1990 ከእሥር የተለቀቁት ማንዴላ በ95 ዓመታቸው በ2013 ከዚህ ዓለም በሞት መለየታቸው አይዘነጋም።