የኤርትራ የጦርና የደኅንነት ከፍተኛ ባለስልጣናት ጉብኝት በሱዳን

ታትሟል

የኤርትራ ከፍተኛ የጦር ሠራዊትና የደኅንነት አመራር አባላት ልዑካን ቡድን ወደ ሱዳን በማቅናት ከአገሪቱ ከፍተኛ ባለስልጣናት ጋር እየተወያየ መሆኑ ተነገረ።

የኤርትራው ከፍተኛ ወታደራዊ የልዑካን ቡድን በአገሪቱ የጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኤታማዦር ሹም በጄነራል ፊሊጶስ ወልደዮሐንስ የተመራ ሲሆን በተጨማሪም የማዕከላዊ ዞን አዛዡ ሜጀር ጄነራል ሮሞዳን አወሊያ፣ የባሕር ኃይል አዛዡ ሜጀር ጄነራል ሁመድ ካርኬሪ እና የብሔራዊ ደኅንነት ኃላፊው ብርጋዴር ጄነራል ብረሐ ካሳ ይገኙበታል።

የልዑካን ቡድኑ ከኤርትራው ፕሬዝዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ የተላከ መልዕክትን ለሱዳን ሉአላዊ የሽግግር ምክር ቤት ሊቀመንበርና የሱዳን ጦር ሠራዊት ጠቅላይ አዛዥ ለሆኑት ሉቴናንት ጄነራል አብዱል ፋታህ አል-ቡርሃን አብዱል ራህማን ማቅረቡን የሱዳን ዜና ወኪል ገልጿል።

የፕሬዝዳንቱ መልዕክትም በሁለቱ አገራት መካከል በወታደራዊው ዘርፍ ስለሚኖረው ትብብርና እነሱንም የበለጠ በማጠናከር ላይ ያተኮረ እንደሆነ ተዘግቧል።

ከፕሬዝዳንት ኢሳያስ የተላከውን መልዕክት ለሱዳን ምክር ቤት ሊቀመንበር ያቀረቡት የኤርትራን ልዑካን ቡድንን የሚመሩት ጠቅላይ ኤታማዦር ሹሙ ጄነራል ፊሊጶስ ወልደዮሐንስ ሲሆኑ በሥነ ሥርዓቱ ላይ በካርቱም የኤርትራ አምባሳደርን ጨምሮ የሱዳን ከፍተኛ የደኅንነትና የሠራዊት አመራሮች መገኘታቸውን ዜና አገልግሎቱ ገልጿል።

የሽግግር አስተዳደሩ ሊቀ መንበር አል-ቡርሃን እንዳሉት የሁለቱ አገራት ሠራዊት አመራሮች የሕዝባቸውን ፍላጎት ለማሟላት በወታደራዊውም ሆነ በደኅንነት ዘርፎች ያለውን ግንኙነቱን ለማጠናከር መልካም አጋጣሚዎችን መጠቀም እንዳለባቸው ተናግረዋል።

በተጨማሪም ጄነራል ፊሊጶስ ወልደዮሐንስና ልዑካን ቡድናቸው ከሱዳኑ የጦር ኃይሉ ጠቅላይ ኤታማዦር ሹም ሜጀር ጄነራል ሞሐመድ ኦስማን አል-ሁሴን እንዲሁም ከሱዳን የደኅንነት መስሪያ ቤት ኃላፊ ጋር በመሆን ውይይት ማድረጋቸው ተገልጿል።

የኤርትራ ከፍተኛ ወታደራዊ ባለስልጣናት ለቀናት የሚቆይ ጉብኝት ለማድረግ ወደ ሱዳን መሄዳቸው የተነገረ ሲሆን በዋናነት በሁለቱ አገራት ስላለው ወታደራዊና የደኅንነት ሁኔታዎች ላይ እንደሚወያዩ ተነግሯል።

ከሁለቱም ወገን በከፍተኛ ወታደራዊና የደኅንነት ባለስልጣናት መካከል የሚደረገው ውይይት ያላቸውን ግንኙነት ከማጠናከር ባሻገር ስለጉብኝቱ ዓላማ በዝርዝር የተገለጸ ነገር የለም።

በኤርትራና በሱዳን መካከል ያለው የድንበር መተላለፊያ ዝግ ከሆነ ረዘም ያለ ጊዜ ያስቆጠረ ቢሆንም የሁለቱ አገራት ግንኙነት ላየወ እስካሁን የጎላ ችግር አልታየም።

በቅርቡ የኤርትራው ፕሬዝዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ ወደ ካርቱም በማቅናት ለቀናት የቆየ ጉብኝት ያደረጉ ሲሆን ከአገሪቱ ከፍተኛ ባለስልጣናት ጋርም መወያየታቸው ይታወሳል።