ፍልስጤማውያን የቤተሰብ አባላትን የገደለው እስራኤላዊ ተፈረደበት

ታትሟል

የእስራኤል ፍርድ ቤት፤ በፈረንጆቹ 2015 ሶስት ፍልስጤማውያን የቤተሰብ አባላትን በመሣሪያ የገደለው አይሁድ ላይ ፍርድ አስተላለፈ።

የፍርድ ቤቱ ዳኞች አሚራም ቤን ኡሊዬል የተሰኘው አይሁድ፣ ዱማ በተሰኘችው የዌስት ባንክ የሰፈራ ጣብያ የሚገኙ ፍልስጤማውያን ቤተሰቦች ላይ ቦምብ ወርውሮ እናትና አባት እንዲሁም የ18 ወራት ሕፃን ልጃቸውን ገድሏል ብለዋል።

ወንጀለኛው፤ ሌላኛው በወቅቱ የአራት ዓመት ሕፃን የነበረው አሕመድ ላይ ደግሞ ጉዳት አድርሷል ተብሏል። ሰውዬው በግድያ ወንጀል ጥፋተኛ መሆኑ ሲረጋገጥ የአሸባሪ ቡድን አባል ግን አይደለም ተብሏል።

ጥፋተኛ የተባለው ግለሰብ ጠበቃዎች ደንበኛችን የእስራኤል መርማሪዎች ያልፈፀመውን ወንጀል እንዲያምን አስገድደውታል፤ ስለዚህ ይግባኝ ይጠይቃል ይላሉ።

በፍልስጤማውያኑ ቤተሰቦች ላይ የተፈፀመው ጥቃት በወቅቱ በእስራኤልና ፍልስጤም በኩል ያለውን ውጥረት ከማክረሩም በላይ የዓለም አቀፉ ማሕበረሰብ ድርጊቱን እንዲያወግዘው አድርጎ ነበር።

ሳድ፣ ሪሃምና ልጆቻቸው በተኙበት ነው ጭምብል ያጠለቁ ሰዎች በመስኮታቸው በኩል የወረወሩባቸው። ጥቃት አድራሾቹ የሂብሪው ኃይለ ቃላትን ተጠቅመዋል፣ 'በቀል' ሲሉ ጮኸዋልም ተብሏል።

የ18 ወራት ጨቅላ የነበረው አሊ ወዲያውኑ ሲሞት እናትና አባት ደግሞ ወደ ሆስፒታል ከሄዱ በኋላ ነው ህይወታቸውን ያጡት። አሕመድ ደግሞ ለወራት የሕክምና እርዳታ አስፈልጎት ነበር።

ጥቃቱ ከተፈፀመ ከአንድ ዓመት በኋላ ነው የእስራኤል አቃቤ ሕጎች ቤን ኡሊዬልን በሁለተኛ ደረጃ ግድያ የከሰሱት። ሌላኛው ከተሳሽ ደግሞ ስሙ ያልተጠቀሰ አንድ ታዳጊ ለግድያ በመተባበር ተከሶ ነበር።

የክስ መዝገቡ እንደሚያሳየው ተከሳሾቹ ጥቃቱን የፈፀሙት በበቀል ተነሳስተው ነው።

የእስራኤል መገናኛ ብዘሃን እንደዘገቡት ቤን ሶስት ጊዜ ጥቃቱን ፈፅሚያለሁ ብሎ ተናዝዟል። ነገር ግን ሁለት ጊዜ በግዴታ ነው የተናዘዘው በሚል ማስረጃው ውድቅ ተደርጎ ነበር።

ዳኞች፤ ተከሳሹ በሶስተኛው ኑዛዜው የፈፀመውን ወንጀል በገዛ ፈቃዱ ተናግሯል በሚል ተቀባይነት ሰጥተውታል።

የቤን ጠበቃዎች ፍርዱን 'የእስራኤል ፀሊም ቀን' ሲሉ አጣጥለውታል። ደንበኛችን ነፃ ነው ሲሉም ይከራከራሉ።

የአሕመድ ወንድ አያት 'ፍርድ ለሌች እንጂ ለኔ ምንም ጥቅም የለውም' ብለዋል። "ልጄን አይመልስልኝም። ባሏንም እንዲሁ። የልጅ ልጄንም ድጋሚ አላየውም። ነገር ግን ሌሎች ልጆች የአሕመድ ዕጣ ፈንታ እንዲገጥማቸው አልፈልግም። በኛ ላይ የደረሰው በማንም ላይ እንዲደርስ አልሻም።"

ብዙም መሰል ጉዳዮች ላይ አስተያየት የማይሰጡት እስራኤል ሃገር ውስጥ ሚኒስትር ሺን ቤት ፍርዱን 'የአይሁድ ሽብርተኝነትን ለመከላከል ወሳኝ እርምጃ' ብለውታል። አክለውም 'ይህ ቀይ መስመር የጣሰ በቀል ነው' ሲሉ ጥቃቱን ኮንነዋል።