ኮሮናቫይረስ፡ በሕንድ በባቡር ሀዲድ ላይ ተኝተው የነበሩ 16 ስደተኛ ሠራተኞች ተገጭተው ሞቱ

ታትሟል
የንባብ ጊዜ: 1 ደቂቃ

ሕንድ ውስጥ ማሃራሽትራ በምትባለው ግዛት 16 ሰዎች በእቃ ጫኝ ባቡር ተገጭተው መሞታቸው ተነገ። ይህንንም ተከትሎ ባለስልጣናት በአደጋው ዙሪያ ምርመራ እንዲደረግ አዘዋል።

ሟቾቹ ከሌላ አካባቢ መጥተው በከተሞች የሚሰሩ ስደተኛ ሠራተኞች ነበሩ የተባለ ሲሆን ወደ ቀያቸው ለመሄድ ባቡር የሚያገኙበት ስፍራ ሀዲዱ ላይ ተኝተው ነበር ተብሏል።

ሕንድ ስደተኛ ሠራተኞቹ ወደ ቀያቸው የሚያደርስ የተለየ ባቡር ማዘጋጀቷ ተገልጿል።

ሕንድ የኮረናቫይረስ ወረርሽኝ ስርጭትን ለመከላከል የእንቅስቃሴ ገደብ ጥላ በነበረበት ወቅት በአስር ሺህዎች የሚቆጠሩ ስደተኛ ሠራተኞች ወደ ትውልድ መንደራቸው በእግራቸው ጉዞ ጀምረዋል።

የሕንድ ስደተኛ ሠራተኞች ከአገሪቱ የተለያዩ የገጠር መንደሮች የተሻለ ክፍያና ህይወት በመፈለግ ወደ ከተሞች የፈለሱ ናቸው።

የባቡር ጣብያው ሠራተኞች ስደተኞቹ ወደ አውራንጋባድ የሚወስደውን አውራ ጎዳና ይዘው እየሄዱ የነበረ ቢሆንም በኋላ ግን ወደ አውራንጋባድ የሚወስደው ባቡር መስመር ላይ መጥተዋል ብለዋል።

ስደተኞቹ በእግራቸው 36 ኪሎ ሜትር ያህል ከተጓዙ በኋላ በድካም በመዛላቸው የባቡር ሀዲዱ ላይ መተኛታቸውም ተነግሯል።

እንደ አገር ውስጥ መገናኛ ብዙኀን ዘገባ ከሆነ በእንቅስቃሴ ገደቡ ምክንያት ባቡር አይመጣም ብለው በማሰባቸው ሀዲዱ ላይ ተኝተዋል።

በማኅበራዊ መገናኛ ብዙኀን ላይ የሚዘዋወሩ ምስሎች ላይ እንደሚታየው ከስደተኞቹ አስክሬን አቅራቢያ ደረቅ ዳቦ ወድቆ ይታያል።

ሕንድ ከአንድ ወር ከአስራምስት ቀን በፊት የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝን ለመከላከል ያለምንም ቅድመ ማስጠንቀቂያ የእንቅስቃሴ ገደብ ስትጥል ከሌላ አካባቢ ወደ ከተሞች የመጡ ሠራተኞች የምንመገበው እናጣለን ብለው በመስጋታቸው በእግራቸው ወደ ትውልድ ቀያቸው መመለስ ጀምረዋል።

በርካቶች የመጓጓዣ እንቅስቃሴ በመቆሙ ምክንያት በእግራቸው ወደ ትውልድ ቀያቸው ለመመለስ መገደዳቸው በአገሪቱ ውስጥ ትልቅ መነጋገሪያ ሆኖ ነበር።

የእንቅስቃሴ ገደቡ በተወሰነ መልኩ መላላቱን ተከትሎ የሕንድ መንግሥት ስደተኞቹ በተዘጋጀላቸው ልዩ ባቡርና አውቶቡስ ወደ አካባቢያቸው መመለስ እንደሚችሉ ተናግሯል።

የሕንድ ጠቅላይ ሚኒስትር በ16 ሰዎች ሞት የተሰማቸውን ሀዘን ገልፀዋል።