ጥቁር አሜሪካዊውን በመግደል አባት እና ልጅ ክስ ተመሰረተባቸው

ታትሟል

በአሜሪካዋ ጆርጂያ ግዛት የአካል እንቅስቃሴ ሲያደርግ የነበረውን ጥቁር አሜሪካዊ ተኩሰው የገደሉት አባት እና ልጅ ክስ ተመስርቶባቸዋል።

ተከሳሾቹ የ64 ዓመቱ ጆርጅ ማክሚካኤል እና የ34 ዓመቱ ትራቪስ ማክሚካኤል ትናንት ነበር በቁጥጥር ሥር የዋሉት።

ሟች የ25 ዓመቱ አህሙድ አርቤረይ በአባት እና ልጅ ጥቃት ሲሰነዘርበት አካላዊ እንቅስቃሴ ለማድረግ በሩጫ ላይ ነበር።

እንደ መርማሪ ፖሊስ ከሆነ ወንጀሉ የተፈጸመው የካቲት 23 ሲሆን፤ አባት እና ልጅ በታጠቁት ጦር መሳሪያ ወጣቱን ያስፈራሩት ሲሆን፤ አህሙደን ተኩሶ የገደለው ግን የ34 ዓመቱ ትራቪስ ነው።

አባት እና ልጅ ለፖሊስ ቃላቸውብ ሲሰጡ፤ ሟች በተደጋጋሚ ቤት ሰብሮ ዘረፋ ይፈጽማል ተብሎ የተገለጸ ሰው ነው ብለው አምነዋል።

ለአካላዊ እንቅስቃሴ በሩጫ ላይ የነበረውን ወጣት ሲመለከቱ በመኪናቸው መከታተል ጀመሩ። የ64 ዓመቱ ተከሳሽ እና የቀድሞ የፖሊስ አባል፤ ለፖሊስ በሰጡት ቃል ላይ “ቁም ቁም ልናነጋግርህ እንፈልጋለን አልነው። ከዛ ትራቪስን ማጥቃት ጀመረ። ከዛ የተኩስ ድምጽ ተሰማ” ብለዋል።

የወንጀሉን ድርጊት አፈጻጸም ያሳያል የተባለ የ36 ሰከንድ ተንቀሳቃሽ ምሰልም በማህብራዊ ገጾች ላይ በስፋት ተሰራጭቷል። በቪዲዮ ላይ አንድ ወጣት እየሮጣ ይታያል። ከዚያም የሁለቱ ተጠርጣሪዎች ተሽከርካሪ እየሮጠ ወደላው ወጣት ይጠጋል። ከዚያም እየሮጠ የነበረው ወጣት መሳሪያ ከታጠቀ ሰው ጋር ሲታገል ያሳያል። ከዚያም የተኩስ ድምጽ ይሰማል። ቀጥሎ በቪዲዮ ላይ የሚታየው የ64 ዓመቱ አባት ሽጉጥ ይዞ ነው።

ወንጀሉ ከተፈጸመ በኋላ ፖሊስ ተጠርጣሪዎቹን በቁጥጥር ሥር ሳያውል እና ክስ ሳይመሰረትባቸው ለበርካታ ሳምንታት መቆየቱ በጥቁር አሜሪካውያን ዘንድ ከፍተኛ ቁጣን ቀስቅሶ ነበር።

የሟች እናት በበኩላቸው፤ ከክስተቱ በፊት ፖሊስ ልጃቸው በዘረፋ ወንጀል ተሳትፎ ነበር ሲል ነግሯቸዋል።

ልጃቸው በወንጀል ድርጊቶች ተሳትፎ ነበረው የተባለው “ሐሰት ነው” ብለዋል።