ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
የሱዳኑ የቀድሞ ፕሬዝዳንት ኦማር አልበሽር ሁለት ዓመት ተፈረደባቸው
የሱዳን የቀድሞ ፕሬዝዳንት ኦማር አልበሽር በሙስና ወንጀል ጥፋተኛ ተብለው የማህበራዊ ለውጥ ማዕከል ውስጥ ሁለት ዓመታት እንዲያሳልፉ ተፈርዶባቸዋል።
የፍርድ ቤቱ ዳኛ እንደተናገሩት በሱዳን ሕግ መሰረት እድሜያቸው ከ75 ዓመት በላይ የሆኑ ዜጎች ማረሚያ ቤት ውስጥ እንዲቆዩ የማይፈቀድ ሲሆን አልበሽር ደግሞ 75 ዓመት ሞልቷቸዋል።
አልበሽር ከዚህ በተጨማሪ እ.አ.አ. በ 1989 ወደ ስልጣን ካመጣቸው መፈንቅለ መንግስት ጋር በተያያዘ፣ በዘር ማጥፋት እና ባለፈው ሚያዝያ በርካታ ተቃዋሚዎችን በመግደል ወንጀል ክስ ቀርቦባቸዋል።
አልበሽር የፍርድ ሂደታቸው በሚከታተሉበት ሰአት ደጋፊዎቻቸው ብያኔው ፖለቲካዊ ነው በማለት ያጉረመረሙ ሲሆን የፍርድ ቤቱ ዳኛም በአፀፋው ችሎቱን ረብሻችኋል በማለት አባረዋቸዋል።
ከፍርድ ቤት ወጥተውም ውጪ ሆነው ተቃውሟቸውን አሰምተዋል።
ከብያኔው በኋላ የቀድሞው ፕሬዝዳንት ጠበቃ የሆኑት አህመድ ኢብራሂም በበኩላቸው ፍርዱ ተገቢ አይደለም ይግባኝም እንጠይቃለን ብለዋል።
ሌላኛው ጠበቃቸው አህመድ አል ሀሳን ደግሞ የፍርድ ሂደቱ የፍትህ ጉዳይ ሳይሆን ፖለቲካዊ መልእክት ያለው ነው ሲሉ ተደምጠዋል።
በኦማር አልበሽር ላይ የቀረበው የሙስና ክስ መካከል ከሳኡዲ ልዑል ሞሀመድ ቢን ሳልማን 25 ሚሊየን ዶላር ተቀብለዋል የሚል ሲሆን፤እሳቸው ግን ገንዘቡ በሁለቱ ሃገራት ስትራቴጂካዊ ግንኙነት ላይ የተመሰረት ድጋፍ ነው ብለዋል። ገንዘቡም ለግል ጥቅም በጭራሽ አልዋልም በማለት ተከራክረዋል።
አልበሽር ላይ ከቀረቡት ክሶች መካከል ዓለማቀፉ የወንጀለኞች ፍርድ ቤት (አይሲሲ) በዳርፉር ከተቀሰቀሰ ግጭትና የጦር ወንጀል ጋር በተያያዘ ከሚያቀርብቻው ክስ ጋር አይገናኝም ተብሏል።
በዳርፉሩ ግጭት እስከ 300 ሺ የሚደርሱ ሰዎች ሲገደሉ 2.5 ሚሊዮን ሰዎች ደግሞ ከመኖሪያቸው መፈናቀላቸውን የተባበሩት መንግሥታት መረጃ ያሳያል።
ትናንት ደግሞ የቀድሞው የሱዳን ፕሬዝዳንት ኦማር አልበሽር ባለቤት ወ/ሮ ዊዳድ ባቢከርን ፖሊስ ለምርመራ እፈልጋታለሁ ብሏቸዋል። ምርመራቸው የመሬት ካርታና የባንክ ሂሳብ ደብተር ጋር የተገናኘ እንደሆነ በአረብኛ የሚታተመው ባጅ ዜና አገልግሎት ዘግቧል።
ወ/ሮ ባቢከር ዘለግ ላለ ጊዜ በቁም እስር ላይ ነበሩ። ባለፈው ዓመት በሚያዚያ ባለቤታቸው ኦማር አልበሽር ሥልጣናቸው በሕዝባዊ አመጽ ከተነቃነቀ በኋላ ለምርመራ ሲጠሩ ግን የመጀመርያቸው ነው።