ዚምባብዌ ለሰው ሠራሽ ረሀብ ለመጋለጥ ተቃርባለች ተባለ.

ዚምባብዌ ሰው ሰራሽ ረሀብ ሊገጥማት መሆኑን የተባበሩት መንግሥታት አስጠነቀቀ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ታትሟል

ዚምባብዌ ለሰው ሠራሽ ረሀብ ለመጋለጥ ተቃርባለች ሲል የተባበሩት መንግሥታት ድረጅት አስጠነቀቀ።

ከአገሪቱ 14 ሚሊዮን ነዋሪዎች 60 በመቶ የሚሆኑት ለምግብ እጥረት መጋለጣቸውን መረጃዎች ያሳያሉ። የኑሮ መወደድ፣ ድህነትና ተፈጥሯዊ አደጋዎች ለችግሩ ምክንያት ከሆኑት መካከል ናቸው።

በተለይም ሴቶችና ህጻናት ለከፍተኛ አደጋ መጋለጣቸውም ተነግሯል። ከስድስት ወር እስከ ሁለት ዓመት ከሆኑ ህጻናት 90 በመቶው በቂ ምግብ እያገኙ አይደለም።

በተባበሩት መንግሥታት ውስጥ ምግብ የማግኘት መብት ክፍል ቃል አቀባይ የሆኑት ሂላል ኤልቨር ለ11 ቀን አገሪቱን ከጎበኙ በኋላ "ዚምባብዌ ውስጥ የተከሰተው ችግር አፋጣኝ መፍትሔ የሚፈልግ ነው" ብለዋል።

ችግሩ እየተባባሰ እንደሚሄድም አክለዋል።

ሂላል ኤልቨር እንዳሉት፤ ያገኟቸው በርካታ ሰዎች በቀን ከአንድ ጊዜ በላይ መመገብ አይችሉም፤ ብዙዎቹ ህጻናትም ቀንጭረዋል።

"በዚህ አስቸጋሪ ወቅት ልጆቻቸውን ለማትረፍ እየተጣጣሩ ያሉ እናቶች፣ አያቶችና አክስቶች የነገሩኝ አሰቃቂ ታሪኮች እስከወዲያኛው አብረውኝ ይኖራሉ" ሲሉ ሁኔታውን አስረድተዋል።

በአገሪቱ በከተማና ገጠር አካባቢም የተመጣጠነ ምግብ በማጣት በርካቶች ተጎድተዋል። ድርቅና ዝናብ ማጣት ግብርናው ላይ ከፍተኛ ተጽዕኖ አሳድሯል። የኑሮ ውድነት ደግሞ ነገሮችን በእጅጉ አባብሷል።

"መደብሮች ውስጥ ምግብ ቢኖርም ከ490 በመቶ በላይ የናረው የኑሮ መወደድ ዋጋውን የማይቀመስ አድርጎታል" ሲሉ የዚምባብዌ ነዋሪዎች ለሂላል ኤልቨር ገልጸዋል።

ሙስና እንዲሁም አገሪቱ ላይ የተጣሉ ማዕቀቦችም ችግሩን እያባባሱት እንደሚገኙም ተነግሯል። ዚምባብዌ ከፍተኛ የምግብ እጥረት ካለባቸው አራት አገሮች አንዷ ናት። አገሪቷ በግጭት እየተናጠችም ትገኛለች።

"የዚምባብዌ መንግሥት የነዋሪዎችን ሰብአዊ መብት የማክበር ግዴታውን መወጣት ይገባዋል። ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብም የምጣኔ ሃብት ማዕቀቦችን ማንሳት አለበት" ብለዋል ሂላል ኤልቨር።