ከዝምባብዌ ሕዝብ አንድ ሦስተኛው 'ለረሃብ ተጋልጧል'

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት በዝምባብዌ አምስት ሚሊዮን ሰዎች የአስቸኳይ ጊዜ እርዳታ ያስፈልጋቸዋል ሲል የእርዳታ ጥሪ አቀረበ።
እርዳታ የሚያስፈልጋቸው ሰዎች ቁጥር ከጠቅላላ የሀገሪቱ ህዝብ አንድ ሦስተኛው ይሆናል ተብሏል።
ዝምባብዌ በድርቅ፣ በኢኮኖሚ ቀውስና በከባድ አውሎ ነፋስና ዝናብ ተደራራቢ ችግሮች የተጎዳች ሲሆን የዓለም ምግብ ፕሮግራምም ለችግሩ ፈጣን ምላሽ መስጠት እንድችል በማለት የ331 ሚሊዮን ዶላር እርዳታ ጥሪ አቅርቧል።
የዓለም ምግብ ፕሮግራም ኃላፊ ዴቪድ ቤዝሊ እንዳሉት "የአስቸኳይ ጊዜ እርዳታ ፈላጊዎቹ ወደ ረሃብ እያመሩ ነው" ሲሉ ሁኔታውን ገልፀውታል።
በአንድ ወቅት በቀጠናው የዳቦ ቅርጫት እንደሆነች ሲነገርላት የቆየችው ዝምባብዌ ለዓመታት በችግር ውስጥ ተዘፍቃ ቆይታለች።
የዚህ ዓመት እርሻ በድርቁ ምክንያት የተጎዳ ሲሆን የምግብ ዋጋም ጣሪያ ነክቷል። በኃይል ማመንጫ ግድቦችም ያለው የውሃ መጠን በከፍተኛ ሁኔታ በመቀነሱ በመላ ሀገሪቱ የኤሌትሪክ እጥረት ተከስቷል።
ማክሰኞ ዕለት የእርዳታ ጥሪውን ያቀረቡት ሚስተር ቤዝሊ 2.5 ሚሊዮን የሚደርሱ የሀገሪቱ ዜጎች ከረሃብ አፋፍ ላይ ደርሰዋል ሲሉ ተናግረዋል።
"እየተነጋገርን ያለነው የእርዳታ እጃችንን ካልዘረጋንላቸው ወደ ረሃብ እየገሰገሱ ስላሉ ሰዎች ነው" ሲሉ ችግሩን ገልጸውታል።
የዚምባብዌ ችግር ከድጡ ወደ ማጡ የሆነው በዚህ ዓመት ሳይክሎን ክፉኛ ከመታት በኋላ ነው።
ይህ ከባድ አውሎ ነፋስ ከፊል ማላዊንና ሞዛምቢክንም ያጠቃ ሲሆን 570 ሺህ ዝምባዌያውያን ተጎድተዋል፤ በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ ደግሞ ቤት አልባ ሆነዋል።
ባለፈው ሳምንት የፋይናንስ ሚኒስትሩ መንግሥት በከተማና በገጠር ለሚኖሩ 757 ሺህ አባወራዎች ከታኅሳስ ወር ጀምሮ የምግብ እህል ድጋፍ እያደረገ መሆኑን ገልጸው ነበር።
የሀገሪቱ ፕሬዝዳንት ኤመርሰን ምናንጋግዋ በበኩላቸው የተከሰተውን ረሀብ ብሔራዊ ቀውስ ሲሉ ገልፀውታል።
የተባበሩት መንግሥታት 294 ሚሊዮን ዶላር እርዳታ ጠይቆ የነበረ ሲሆን፤ ነገር ግን ድርቁ ሰፊ አካባቢዎችን ስለሚሸፍን ተጨማሪ ድጋፍ ያስፈልገኛል ብሏል።












