45 ሺህ ሹፌሮች ያሉት ኡበር የሎንዶን የሥራ ፍቃዱን ተነጠቀ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ኡበር የተሰኘው የታክሲ አገልግሎት ሰጭ ድርጅት በእንግሊዝ ከተማ ሎንዶን እንዲሠራ የተሰጠው ፈቃድ ተነጠቀ።
'ትራንስፖርት ፎር ሎንዶን' የተሰኘው የታክሲ አገልግሎት ኩባንያዎች ፈቃድ ሰጭ መሥሪያ ቤት ኡበር ሎንዶን ውስጥ ለመሥራት አቅምና አግባብነት የለውም ሲሉ ነው ፈቃዱን የነጠቁት።
ኡበር፤ በግሪጎሪ አቆጣጠር 2017 ላይ በተመሳሳይ የሎንዶን የሥራ ፈቃዱን ተነጥቆ ነበር። ምክንያቱ ደግሞ የተጠቃሚዎች ደህንነት ነው። በጊዜው ይግባኝ የጠየቀው ኡበር የ15 ወራት ፈቃድ ተሰጥቶታል።
ይህ ፈቃድ በ21 ቀናት ውስጥ የሚጠናቀቀው ኡበር የሥራ ፈቃዱ ድጋሚ እንደማይታደስ ያሳወቁት የትራንስፖርት ፎር ሎንዶን የሥራ ፈቃድ ሰጭ ሊቀመንበር ሄለን ቻፕማን ናቸው።
«ደህንነት ቅድሚያ የምንሰጠው ጉዳይ ነው። ምንም እንኳ ኡበር በጎ ለውጦችን ቢያመጣም ማንነታቸው የማይታወቅ ሰዎች ሹፌር ሆነው እንዲቀጠሩ መፍቀዱ አግባብ አይደለም» ሲሉ ኃላፊዋ ፈቃድ የነሱበትን ምክንያት ያስረዳሉ።
ኡበር ይግባኝ እንደሚጠይቅ ይጠበቃል።
45 ሺህ ገደማ አሽከርካሪዎች ለኡበር ይሠራሉ። የኡበር የሥራ ፈቃድ ለዘለቄታው የሚሠረዝ ከሆነ እኒህ ሹፌሮች ከሥራ ውጭ ይሆናሉ የሚል ስጋት አለ።
ነገር ግን ከዓለም አቀፍ ኡበር ጋር የተመሳሰለ ሥራ የሚሠሩ በርካታ ድርጅቶች በሎንዶን መኖራቸው ይታወቃል።
'ትራንስፖርት ፎር ሎንዶን' ለድርጅቶች ብዙ ጊዜ የአምስት ዓመት ፈቃድ በመስጠት ይታወቃል። ቢሆንም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ፈቃድ መስጠት ላይ ቆጠብ ያለ ይመስላል።
ድርጅቱ 'የተጠቃሚዎች ደህንነት' አደጋ ላይ ሊወድቅ እንዳይችል ነው ፈቃድ የነሳሁት ይላል። ውሳኔው ከሎንዶን ከንቲባ ሳዲቅ ካህን ድጋፍ አግኝቷል።
ኡበር ሎንዶን ውሰስጥ ብቻ ሳይሆን በሌሎች ከተሞችም ተቃውሞ ይገጥመዋል። ብዙ ቦታዎች ተቃውሞ የሞመጣው በባሕላዊ መንገድ የታክሲ ግልጋሎት ከሚሰጡ ሰዎች ነው።












