የኡበር መተግበሪያ ተኩስ አስከፍቶኛል ያለው አሽከርካሪ ጥፋተኛ መሆኑን አመነ

ጄሰን ዳልተን

የፎቶው ባለመብት, Reuters

ታትሟል

በአውሮፓውያኑ 2016 በከፈተው ተኩስ ስድስት ሰዎች በመሞታቸው ምክንያት ክስ ተመስርቶበት የነበረው ጄሰን ዳልተን የተባለው የኡበር አሽከርካሪ ጥፋተኛ መሆኑን አመነ።

አራቱ ግለሰቦች በሬስቶራንት ውስጥ ሲሞቱ ሁለቱ ደግሞ የመኪና መሸጫ ቦታ ላይ በጥይት ተመትተው ህይወታቸው አልፏል።

የአርባ ስምንት አመቱ አሽከርካሪ የኡበርን መተግበሪያ "ሰውነቴንና አእምሮየን ተቆጣጥሮኝ ነው ይህንን ድርጊት የፈፀምኩት" ቢልም የፍርድ ሂደቱ ከተጀመረ በኋላ ግን ጥፋተኝነቱን አምኗል።

ጥፋተኛ መሆኑን ማመኑ የፍርዱን ውሳኔ እንደማያቀልለት አቃቤ ህግ ተናግሯል።

ክሱ እንደሚያሳየው ስድስት ሰዎችን በመግደል፣ ሁለት ግለሰቦችን ለመግደል በመሞከርና ስምንት የተለያዩ ክሶች ደግሞ መሳሪያ ከመያዝ ጋር የተያያዙ ናቸው።

ፍርድ ቤቱም በዕድሜ ልክ እስራት እንዲቀጣ ወስኖበታል። ዳልተን የእምነት ክህደት ቃሉን የሰጠው ያለ ጠበቃው ስምምነት ነው።

ለፍርድ ቤቱም እንደተናገረውም ያለማንም ማስገደድ በነፃነት ቃሉን እንደሰጠ ነው፤ ይህንንም ለማድረግ ለረዥም ጊዜ ይፈልግ እንደነበር ተናግሯል።

ለፖሊስ ከዚህ በፊት በሰጠው ቃል የኡበር መተግበሪያው ወደ አሻንጉሊትነት እንደቀየረውና ዝም ብሎም ተኩስ እንዳስከፈተው ገልፆ ነበር።

ምንም እንኳን የሞቱትም ሆነ ጉዳቱ የደረሰባቸው የኡበር ደንበኞቹ ባይሆኑም ተኩሱን በከፈተበት ወቅትም እየነዳ እንደነበር ፖሊስ አስታውቋል።

ጥቃቱ የደረሰው በሶስት አካባቢዎች ሲሆን በሬስቶራንት፣ መኪና በመሸጫና በአንድ አፓርትመንት ህንፃ ላይ ነው።

በዛኑ ቀን በፖሊስ ቁጥጥር ከዋለ በኋላ ኡበር እንዳሳወቀው በኩባንያቸው ተመዝግቦ የሚሰራ ግለሰብ መሆኑና "በደረሰውም ጥቃት ከፍተኛ ሀዘን እንደተሰማው ገልጿል።