ሰዎች በወበቅ ወቅት የበለጠ ህመም ይሰማቸዋል

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
እንደ ቁርጥማት ያለ የረዥም ጊዜ የጤና ችግር ያለባቸው ሰዎች በእርጥበት አዘል አየር [ወበቅ] ወቅት የበለጠ ሕመም እንደሚሰማቸው በእንግሊዝ የተደረገ ጥናት አመለከተ።
እንዲሁ በዘልማድ ቅዝቃዜ ህመምን ያባብሳል የሚል ነገር ቢኖርም የአየር ጠባይ ሕመም ላይ ያለው ተጽዕኖ ላይ የተሠሩ ጥናቶች ትንሽ ናቸው።
የማንችስተር ዩኒቨርስቲ ከ2500 ሰዎች ስማርት ስልክ መረጃዎችን የሰበሰበ ሲሆን የቁርጥማት ህመማቸው በሞቃታማ ወይም በጨፍጋጋ ቀን የባሰ መሆኑን መረዳት ችለዋል።
ተመራማሪዎቹ ይህ ግኝታቸው ለወደፊት ለሚደረጉ ጥናቶች 'ለምን ይህ ሆነ?' የሚለውን እንዲያጠኑ መነሻ ይሆናል ሲሉ ተናግረዋል።
ሰዎች በቅዝቃዜ ወቅት የሚነዘንዝና የሚጠዘጥዝ ቁርጥማት ተሰማን ሲሉ መስማት የተለመደ ነው።
አንዳንዶች እንደውም ቁርጥማታቸው ሲጀምራቸው "ቅዝቃዜ እየመጣ ነው" በማለት አየር ሁኔታውን ሊተነብዩ ይችላሉ።
ነገር ግን የተለያየ የአየር ጠባይ ህመም ላይ ያለውን ተጽዕኖ ሳይንሳዊ የሆነ ምርምር በማድረግ መለየት ፈታኝ ሊሆን ይችላል ሲሉ ይናገራሉ ተመራማሪዎቹ።
ከዚህ ቀደም የተደረጉ ጥናቶችም ትንሽ ብቻ ሳይሆኑ የአጭር ጊዜ ውጤትን ብቻ እንዲያመለክቱ ተደርገው የተሠሩ ናቸው ሲሉም ያስረዳሉ።
ተመራማሪዎቹ ለዚሁ ጥናት፣ በመላው ዩኬ ካሉ ቁርጥማት፣ የጡንቻ መሸማቀቅ፣ ከፍተኛ የራስ ምታት (ማይግሪን)፣ ከነርቭ ጋር የተያያዘ ችግር ያለባቸውን 2500 ሰዎች መርጠዋል።
ከአንድ እስከ 15 ወር በየቀኑ የሚሰማቸውን የህመም ስሜት ስልካቸው ካሉበት ሥፍራ ከሚመዘግበው የአየር ሁኔታ ጋር እየተገናዘበ ተሰንዷል።
ከዚህም መረዳት የተቻለው ጨፍጋጋና ንፋሳማ ቀናት ከተለመደው በ20 በመቶ ላቅ ያለ የህመም ስሜት እንደሚፈጥር ነው።
ቀዝቃዛና ጨፍጋጋ ቀናት ሕመምን የበለጠ ያከብዳሉ። ነገር ግን ህመሙን ከሙቀትም ሆነ ከዝናብ ጋር ብቻ የሚያይዘው ነገር የለም።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ህመም ትንበያ
በማንችስተር ዩኒቨርስቲ የተካሄደውን ይህን የምርምር ሥራ የሚመሩት ፕሮፌሰር ዊል ዲክሰን " ከግሪኩ የሕክምና ሊቅ ሂፖክራተስ ጀምሮ ቁርጥማት ያለባቸው ሕሙማንን የአየር ጠባይ ሁኔታው ተጽዕኖ እንዳለው ይታመን ነበር" ሲሉ ይናገራሉ።
"ቁርጥማት ከሚያስቸግራቸው 3/4ኛዎቹም የአየር ጠባዩ ቁርጥማታቸው ላይ ተጽዕኖ እንዳለው ያምናሉ" ሲሉ ያብራራሉ።
ፕሮፌሰር ዲክሰን አክለውም ሌሎች ተመራማሪዎች " ወበቅ ስለምን ከሕመሙ ጋር እንደተገናኘ ቢመለከቱት ለአዲስ ሕክምና በር ከፋች ነው" ሲሉ መክረዋል።
እንዲሁም " የሕመም ትንበያ" ለማካሄድ የሚያስችል መንገድን ለማዳበርና ቁርጥማት የሚታመሙ ሰዎች አስቀድመው ማድረግ ያለባቸውን እንዲወስኑ ይረዳቸዋል ብለዋል።
በእንግሊዝ 10 ሚሊየን ሰዎች በቁርጥማት ህመም የሚሰቃዩ ሲሆን አብዛኞቹም በየዕለቱ መፈጠርን በሚያስረግም ህመም ውስጥ ያልፋሉ ተብሏል።
ዶ/ር ስቴፈን ሲምፕሰን በበኩላቸው "ቁርጥማትና የአየር ጠባይ ያላቸው ዝምድና በዘልማድ ብቻ ነበር የሚነገረው፤ ነገር ግን ይህ የሰዎች የተኖረ ልምድ እንጂ ጥናት አይደለም" ብለዋል።
አክለውም "እንዲህ ዓይነት ምርምር ፈር ቀዳጅ ሲሆን ድምዳሜ ላይም ለመድረስ ወሳኝ መንገድ ነው" ብለዋል።

















