ፕሬዝዳንት ትራምፕ ቱርክ ላይ ተጥሎ የነበረውን ማዕቀብ አነሱ

የፎቶው ባለመብት, Reuters
አሜሪካ ከዘጠኝ ቀን በፊት ቱርክ ሰሜን ሶሪያ ላይ ጥቃት በመክፈቷ ምክንያት ጥላው የነበረውን ማዕቀብ ማንሳቷን ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ተናገሩ።
ይህ ውሳኔያቸው የተሰማው ሩሲያ ከቱርክ ጋር በሥፍራው የተኩስ አቁሙ እንዲቀጥል ወታደሯን ለመላክ ከተስማማች በኋላ ነው።
"እኛን የማያስደስተን ነገር እስካልተፈጠረ ድረስ ማዕቀቡ ይነሳል" ነበር ያሉት ፕሬዝዳንት ትራምፕ በንግግራቸው።
በተጨማሪም ቱርክ በአካባቢው የጀመረችውን ጦርነት እንደምታቋርጥና የተኩስ አቁም ስምምነቱንም እንደምታከብር እንዳረጋገጠችላቸው ተናግረዋል።
የአሜሪካ ገንዘብ ሚኒስትርም የፕሬዝዳንቱን ንግግር ተከትሎ በቱርክ መከላከያና ኃይል ሚኒስትር እንዲሁም በሦስት የቱርክ ከፍተኛ ባለሥልጣናት ላይ ተጥሎ የነበረው ማዕቀብ መነሳቱን አረጋግጧል።
ቱርክ በሰሜን ሶሪያ የድንበር ከተሞች ላይ ጥቃቷን የጀመረችው አሜሪካ በሥፍራው የሚገኙ ወታደሮቿን ማስወጣት መወሰኗን ተከትሎ ነው።
ትራምፕ ከዋይት ሐውስ ሆነው በሰጡት መግለጫ ላይ "በዚህ ደም በተነከረ አሸዋ ላይ ደግሞ ሌሎች ሄደው ይዋጉ" ነበር ያሉት።
በሰሜን ሶሪያ የድንበር ከተሞች የሚገኙት ኩርዶች የአሜሪካ አጋር መሆናቸውና፣ አይ ኤስን ለመዋጋት ከአሜሪካውያን ጋር የከፈሉትን መስዋዕትነት በማንሳት ዲሞክራቶችም ሆኑ ሪፐብሊካን፣ የአሜሪካ ወታደሮች ከሥፍራው እንዲወጡ መወሰኑን በመቃወም ፕሬዝዳንቱን እጅጉን ተተችተዋል።
ቱርክ አሜሪካ እንደምትወጣ በተናገረች ማግስት በድንበር ከተሞች የሚገኙት የኩርድ ወታደሮች ላይ ጥቃት እንዲከፈት አዝዛለች።
ቱርክ በሶሪያ ግዛት ውስጥ 30 ኪሎ ሜትር ስፋት ያለውና ከኩርድ ወታደሮች ነፃ የሆነ "ደህንነቱ የተጠበቀ ቀጠና" መመስረት እንደምትፈልግ ስትናገር ቆይታለች።
በዚህ ሥፍራ በሀገሯ ውስጥ የሚገኙ 2 ሚሊየን ሶሪያዊ ስደተኞችን የማስፈር እቅድ አላት።
ፕሬዝዳንት ትራምፕ ቱርክ የተኩስ አቁም ለማድረግ ከተስማማች በኋላ የተወሰኑ ወታደሮችን በአካባቢው ለማቆየት ወስነው ነበር።
በተጨማሪም ቱርክ የአይ ኤስ እስረኛ ወታደሮችን እንድትረከብ እንዲሁም በሶሪያ ምድር አክራሪ ቡድኖች ምንም ዓይነት የበላይነት እንዳያገኙና ቦታዎችን እንዳይቆጣጠሩ እንድትቆጣጠር ተናግረዋል።
አንድ ከፍተኛ የአሜሪካ ባለሥልጣን እስካሁን በነበረው ውጊያ 100 የአይ ኤስ ወታደሮች ማምለጣቸውን ተናግረው እስካሁን ድረስ አለመያዛቸቸውን ገልፀዋል።

















