ሰሜን ኮሪያ በስምንት ቀናት ውስጥ ለሦስተኛ ጊዜ ተወንጫፊ መሳሪያ ሞከረች

ታትሟል

ሰሜን ኮሪያ ሁለት ተወንጫፊ የጦር መሳሪያዎችን የተኮሰች ሲሆን የደቡብ ኮሪያ ባለሥልጣናት እነዚህ በአጫጭር ርቀት የሚምዘገዘጉ ሚሳኤሎች በዓይነታቸው አዲስ መሆናቸውን ተናግረዋል።

በስምንት ቀናት ውስጥ ለሦስተኛ ጊዜ የተተኮሰው ይህ ተምዘግዛጊ የጦር መሳሪያ ከሰሜን ኮሪያ ምስራቃዊ ባህር ዳርቻ አካባቢ መነሳቱን ለማወቅ ተችሏል።

ይህ በተከታታይ የተደረገ የአጭር ርቀት ሚሳኤል ሙከራ የታየው ደቡብ ኮሪያ ከአሜሪካ ጋር ለማድረግ ያቀደችውን የጦር ልምምድ ተከትሎ ነው።

ሐሙስ ዕለት ዩናይትድ ኪንግደም፣ ፈረንሳይና ጀርመን ሰሜን ኮሪያ ከአሜሪካ ጋር "ረብ ያለው" ንግግር እንድታካሄድ ጥሪ አቅርበው ነበር።

በተባበሩት መንግሥታት የፀጥታው ምክር ቤት ዝግ ስብሰባ ካደረጉ በኋላም፤ ፒዮንግ ያንግ የኒውክለርና ባሌስቲክ ሚሳኤል ፕሮግራሞቿን ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ እስክታቆም ድረስ ዓለም አቀፍ ማዕቀብ ሙሉ በሙሉ ተግባራዊ መደረግ እንዳለበት ወስነዋል።

ሰሜን ኮሪያ በቅርብ ጊዜ ሙከራ ያደረገችው ሐሙስ ዕለት ሲሆን ተወንጫፊ መሳሪያው ከመሬት የነበረው ከፍታ እጅጉን ዝቅ ያለ እንደነበርና 220 ኪሎ ሜትር መምዘግዘግ መቻሉ ተነግሯል።

የዘርፉ ባለሙያዎችም መሳሪያው ከተለመደው በላይ በፍጥነት ይምዘገዘግ ነበር ብለዋል።

የደቡብ ኮሪያ ፕሬዝዳንት ጽህፈት ቤት ቃል አቀባይ አጭር ርቀት መጓዝ የሚችል አዲስ ባሌስቲክ ሚሳኤል ሊሆን እንደሚችል ገልጸዋል።

ይህ ሙከራ በዚሁ ሳምንት ከተደረጉ ሁለት ሌላ ሙከራዎች ጋር ተመሳሳይ ነው ሲሉም አክለዋል።

ሰሜን ኮሪያ አሁን ካስወነጨፈችበት ሥፍራ ከዚህ ቀደም ሞክራ እንደማታውቅ ደግሞ የተናገሩት አሜሪካዊው ተመራማሪ አንኪት ፓንዳ ናቸው።

የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ በበኩላቸው በዚህ ሳምንት የተደረጉ የማስወንጨፍ ሙከራዎች በቅርብ ጊዜ ከተካሄደው ንግግር ውስጥ አለመካተቱን በመጥቀስ ሙከራዎቹ "መደበኛ ናቸው" በማለት እንደማያሳስባቸው ተናግረዋል።

እንደ ደቡብ ኮሪያ ከሆነ ረቡዕ ዕለት ሰሜን ኮሪያ በጃፓን ባህር ላይ ከማረፋቸው በፊት 250 ኪሎ ሜትር መጓዝ የሚችሉ እና በ30 ኪሎ ሜትር ከፍታ የሚምዘገዘጉ ሁለት ሚሳኤሎችን ሞክራለች።

ደቡብ ኮሪያ ሚሳኤሎቹ ከዚህ በፊት ሰሜን ኮሪያ ታስወነጭፋቸው ከነበሩት ሚሳኤሎች የተለዩ መሆናቸውን ተናግራለች።

ሐሙስ ዕለት ግን ከዚህኛው የሚለይ ማብራሪያ ከፒዮንግያንግ ወገን ተሰምቷል።

ሙከራው ሮኬት ማስወንጨፊያ እንደሆነ በመጥቀስ ዝርዝሩን ግን ከመስጠት ተቆጥባለች።

እአአ ሐምሌ 25 ሰሜን ኮሪያ ሁለት ሚሳኤሎችን ያስወነጨፈች ሲሆን አንዱ 690 ኪሎ ሜትር ርቀት ተምዘግዝጓል።

ይህ ሙከራ የተካሄደው ፕሬዝዳንት ትራምፕ እና ኪም ጆንግ ኡን ሰኔ ወር ላይ ከወታደራዊ እንቅስቃሴ ነፃ በሆነው ሥፍራ ከተገናኙና ቀጠናውን ከኒውክለር መሳሪያ ነፃ የማድረግ ንግግሩን ዳግመኛ ለመጀመር ከተስማሙ በኋላ ነው።