ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
የሕክምና መስጫ ከሆስፒታል ይዞ ሊወጣ ነበር የተባለው ጥቁር አሜሪካዊ ጉዳይ እያወዛገበ ነው
የአሜሪካ ፖሊስ፤ በኢሊኖይስ ግዛት ሆስፒታል አቅራቢያ መድሃኒት ለመስጠት የተገጠመለትን የአይቪ ማሽን ከሆስፒታል ይዞ ሊወጣ ነበር ያለውን ጥቁር አሜሪካዊ በቁጥጥር ስር ያዋለበትን መንገድ እየመረመረ መሆኑ ተሰማ።
የቺካጎ ነዋሪ የሆነው የ24 ዓመቱ ጥቁር አሜሪካዊ ፣ ሻኩዌል ዱክ የሚባል ሲሆን ኒሞኒያ ታሞ ነበር ሆስፒታል የገባው።
ሻኩዌል እንደሚለው፤ በሃኪሙ ትዕዛዝ ሰውነቱን ለማንቀሳቀስ አጭር የእግር ጉዞ ለማድረግ ከሆስፒታሉ ሲወጣ የሆስፒታሉ ጥበቃ "የተሰካልህን የመድሃኒት መስጫ ማሽን ልትሰርቅ ነው" በማለት በቁጥጥር ሥር አውሎታል።
ሻኩዌል ዘርን መሰረት ያደረገ ጥቃት ተፈጽሞብኛል የሚል ክስ ከፍቷል።
ፖሊሶች ባልደረባቸው ''ማድረግ የሚገባውን በትክክል ፈጽሟል'' ካሉ በኋላ ሁኔታውን በገለልተኛነት የሚያጣራ ቡድን አዋቅረዋል።
ሻኩዌል እየታከመበት የነበረው 'ፈሪፖርት ሔልዝ ኔትዎርክ ሜሞሪያል ሆስፒታል' በጉዳዩ ላይ ያለው ነገር የለም።
ጉዳዩ የተከሰተው ከጥቂት ሳምንታት በፊት ቢሆንም የአሜሪካ መገናኛ ብዙሃን ዜናውን ከተቀባበሉት በኋላ የአሜሪካውያን መነጋገሪያ ሆኖዋል።
ሻኩዌል፤ ሐኪሞች እየተዘዋወረ እግሩን እንዲያፍታታ ከነገሩት በኋላ ዘረኛ የሆነ ነጭ ጥበቃ በቁጥጥር ስር እንዳዋለውና የተሰካለትን አይቪ ኢ-ቤይ ላይ ሊሸጠው እየወሰደው መሆኑን በመግለፅ ፖሊስ መጥራቱን በፌስቡክ ገፁ ላይ አስፍሯል።
ፖሊስም ለመስረቅ በመሞከር ወንጀል በቁጥጥር ስር አውሎታል።
ሻኩዌል እንደሚለው በቁጥጥር ስር በዋለበት ወቅት አይቪው የተነቀለው በዶክተሮች ሳይሆን በፖሊስ ነው።
"ፖሊስ፣ የአየር መተንፈሻዬንና መድሃኒቴን ነቃቅሎ ወደ ፖሊስ ጣቢያ ሲወስደኝ መኪና ውስጥ ያንቀጠቅጠኝ ጀመር፤ መተንፈስም አልቻልኩም። ከፖሊሱ ለመተንፈስ የሚያግዘኝን መሣሪያ ለመውሰድ የተወሰነ ጊዜ ፈጅቶብኛል። በኋላም ራሴን ስስት መተንፈሻውን ገጠሙልኝ" ብሏል።
የፍሪፖርት ፖሊስ በፌስ በክ ገጹ ላይ "ፖሊስ የተከሰተውን ጉዳይ አጣርቶ ሙሉ በሙሉ መረጃ እስኪሰጥ ድረስ ህብረተሰቡ የራሱን መላምት ከመስጠት እንዲቆጠብ" ጠይቋል።
የሕመምተኛው መሣሪያ የተነቀለው በፖሊስ ሳይሆን በህክምና ባለሙያ መሆኑንም ጨምሮ አስረድቷል።
የአካባቢው ባለሥልጣናት፤ ህምተኛው የአይቪ ማሽኑ ተሰክቶለት የሆስፒታሉን ሕንፃ ለቆ እንዲወጣ እንዳልተፈቀደለት ተናግረዋል።
ሻኩዌል በሚቀጥለው ወር ፍርድ ቤት እንደሚቀርብ የመገናኛ ብዙኀን ዘገባ ያስረዳል።