ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
የሰሜን ኮሪያ ሚዲያ ትራምፕን እያንቆለጳጰሰ ነው
በመንግሥት የሚተዳደረው የሰሜን ኮሪያው የዜና አውታር የፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ወደ ሃገሪቱ መምጣት ''አስገራሚ ክስተት'' ነው በማለት ገልጾታል።
እሁድ ዕለት ፕሬዝዳንት ትራምፕ ሰሜን ኮሪያ እግራቸውን ያሳረፉ የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ሆነዋል።
ዶናልድ ትራምፕ እና ኪም ጆንግ ኡን የተገናኘት ከጦርነት እና መሰል ኹነቶች ነፃ የሆነ ቦታ በመባል በሚታወቅ በሁለቱ ኮሪያዎች መካከል ባለ ሥፍራ ነው።
«ድጋሚ ስለተገናኘን ደስ ብሎኛል» በማለት ኪም ጆንግ ኡን ትራምፕን ተቀብለዋቸዋል።
ከመገናኘታቸው ቀደም ብሎ ፕሬዝዳንት ትራምፕ ደቡብ ኮሪያ ከመጣሁ አይቀር ለምን አንገናኝም ሲሉ በትዊተር ገጻቸው ላይ ለፕሬዝዳንት ኪም ጆንግ ኡን መልእክታቸውን አስተላልፈው ነበር።
ለብዙ አስርታት አሜሪካ የሰሜን ኮሪያ ዋነኛ ጠላት አሜሪካ ስለመሆኗ የሰሜን ኮሪያ ዜጎች ሲሰሙ ቆይተዋል። የአሁኑ ግንኙነት ደግሞ ታሪካዊና ወደላቀ ደረጃ የሚሸጋገር ነው በሚል ብዙ አድናቆትን አግኝቷል።
ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ወደ ሰሜን ኮሪያ ሲገቡና ከኪም ጋር ሲጨባበጡ መመልከት ለብዙ ሰሜን ኮሪያውያን አስገራሚና አንዳንዴም ለማመን የሚከብድ ነገር ነው።
ሁለቱ መሪዎች ከጋዜጠኞች ለቀረቡላቸው ጥያቄዎች አጠር ያለ ምላሽ ከሰጡ በኋላ ደቡብ ኮሪያ ድንበር ውስጥ በሚገኝ ቤት ውይይት አካሂደዋል።
ትራምፕ አቻቸው ኪም ጆንግ ኡንን አሜሪካን እንዲጎበኙ እጋብዛቸዋለሁ ሲሉም ለጋዜጠኞች ቃል ገብተዋል።
ለአንድ ሰዓት ያክል የቆየው የሁለቱ መሪዎች ግንኙነት ተጠናቆ ትራምፕ ከደቡብ ኮሪያው ፕሬዝደንት ሙን ጋር ወደ ሴዑል ሲመለሱ ኪም ደግሞ ወደ ሰሜን ኮሪያ አቅንተዋል።
ምንም እንኳን ሁለቱ መሪዎች ግንኙነታቸውን ለማጠናከርና በኒውክሌር ዙሪያ የሚያደርጉትን ድርድር ለማጠናከር እንዳሰቡ ቢናገሩም ተቺዎች ግን ተራ ፖለቲካዊ ተቀባይነት ለማግኘት የሚደረግ ጥረት ነው በማለት እያጣጣሉት ይገኛሉ።