ፖምፔዎ ቫይረሱ ከቻይና ቤተ ሙከራ ስለመምጣቱ 'በርካታ ማስረጃዎች' አሉን አሉ

የኮሮናቫይረስን ለመከላከል ክትባትም ሆነ ለማከም የሚውል መድኃኒት እስካሁን አልተገኘም። ነገር ግን በየአገራቱ ያሉ ባለሙያዎች ሌት ተቀን ጥረት እያደረጉ መሆናቸው እየተነገረ ነው። መቼ ውጤት ላይ ሊደርሱ እንደሚችሉ ግን በእርግጠኝነት መናገር አይቻልም። ስለዚህ በእጃችን ላይ ያሉትን የመከላከያ መንገዶች በመጠቀም እራስን ከበሽታው መጠበቅ ብቸኛው መንገድ ነው። ለዚህ ደግሞ አካላዊ ርቀታችንን እንጠብቅ፤ እጃችንን በተደጋጋሚ በሳሙናና በውሃ እንታጠብ። ስለወረርሽኙ የሚቀርቡ የቀጥታ ዘገባዎችንና መረጃዎችን ከዚህ ገጽ ይከታተሉ።

የቀጥታ ሽፋን

  1. በአፍሪካ የኮሮናቫይረስን ፈውስ ለማግኘት እየተደረጉ ካሉ ሙከራዎች በጥቂቱ

    የመድኃኒት ብልቃጥ

    የፎቶው ባለመብት, Getty Images

    የአፍሪካ የበሽታዎች ቁጥጥር ማእከል ከሰሞኑ በአፍሪካ ውስጥ የኮሮናቫይረስን ፈውስ ለማግኘት እየተደረጉ ስላሉ የመድኃኒቶች እንዲሁም የክትባት ሙከራዎች ይፋ አድርጓል።

    እስካሁን ባለው መረጃ በአህጉሪቷ ውስጥ በ52 ሃገራት በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች መኖራቸው ተረጋግጧል፤ በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች ቁጥርም 37ሺህ ደርሷል።

    ከሌሎች አህጉራት ጋር ሲነፃፀር በአፍሪካ ውስጥ እየተደረጉ ያሉ ሙከራዎች በቁጥር ትንሽ መሆናቸውን ማእከሉ አስታውቋል።

    የማዕከሉ ዶክተር ታጂ ራጁዲን ከጠቀሷቸው ሙከራዎች መካከል፦

    • በግብፅ አስራ ሶስት ያህል ሙከራዎች እየተከናወኑ ሲሆን ከነዚህም መካከል ሁለት ክትባት ላይ ያተኮሩ ናቸው። ከዚህም በተጨማሪ የተለያዩ ተፈጥሯዊ ንጥረ ነገሮችም ላይ ምርምር በማድረግ ላይ ሲሆኑ ለምሳሌ ማር ምን ያህል የሰውነት በሽታን የመከላከል አቅምን ይጨምራል የሚለውንም በጥልቀት እያጠኑት ነው።
    • በዛምቢያ የወባ መድኃኒት በሆነው ሃይድሮክሲክሎሮኪን ላይ ምርምሮች ቀጥለዋል።
    • በደቡብ አፍሪካም በክሎሮኪን፣ ኢንተርፌሮንና ሬምዴሲቪር የሚባሉ መድኃኒቶች የኮሮናቫይረስን ይፈውሱት ይሆን የሚሉ ምርምሮች እየተደረጉ ነው።
    • በናይጄሪያም እንዲሁ የሰውነትን የማገገም አቅምን መጨመር የሚችሉ ንጥረ ነገሮች ላይ አተኩረዋል።
    • በቱኒዝያም ሁለት ሙከራዎች እየተካሄዱ ሲሆን ዝርዝሩ አልተነገረም።

    የአፍሪካ የበሽታዎች ቁጥጥር ማዕከል በአህጉሪቷ እየተደረጉ ያሉ ምርምሮችን በማጠናቀር ላይ ሲሆን አህጉሪቷ ተመልካች ብቻ ሳትሆን አስተዋፅኦ ማድረግ እንደምትችልም ለማሳየት ያለመ ነው።

  2. ኒው ደልሂ ውስጥ የነበሩ ኢትዮጵያውያን ታካሚዎች ወደ ሀገራቸው ተመለሱ

  3. በአሜሪካ የሥራ አጦች ቁጥር 30 ሚሊየን ደረሰ

    በአሜሪካ የሥራ አጦች ቁጥር 30 ሚሊየን ደረሰ

    የፎቶው ባለመብት, Getty Images

    የአሜሪካ የሰራተኞች መስሪያ ቤት ባወጣው አዲስ መረጃ ከባለፈው ሳምንት ጀምሮ የሥራ አጥ ቁጥር እየጨመረ መምጣቱን አመልክቷል፡፡

    በዚህም መሰረት ባለፈው ሳምንት ተጨማሪ 3.8 ሚሊየን ሰዎች ስራ እንደሌላቸው ተመዝግበዋል፡፡ የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ባስከተለው ጫና በአሜሪካ ያለው የሥራ አጦች ቁጥር 30 ሚሊየን አድርሶታል፡፡

    የኮቪድ-19 ወረርሽኝን ለመግታት ግዛቶች የጣሏቸው ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ገደቦች ምክንያት ሆነው ቀርበዋል፡፡

    ይህንን ተከትሎም የመንግሥት የኢኮኖሚ ተቋማትን እንዲከፍት የሚያሳስቡ ተቃውሞዎች በመላ አገሪቷ ተካሂደዋል፡፡

    በመሆኑም የቢዝነስ ተቋማት እንዲከፈቱ ለማድረግ በርካታ የአገሪቷ ግዛቶች የጣሏቸውን ገደቦች ማላላት ጀምረዋል፡፡

    አንዳንድ የምጣኔ ሐብት ምሁራን በጎርጎሳውያኑ ሚያዝያ ወር መጨረሻ የአገሪቷ የስራ ቅጥር 20 በመቶ ሊደርስ እንደሚችል ገምተዋል፡፡ ይህ ቁጥርም ከአንድ ምዕተ ዓመት በፊት ከነበረው የኢኮኖሚ ውድቀት የሚያንሰው 5 በመቶ ብቻ ነው፡፡

  4. ፖምፔዎ ቫይረሱ ከቻይና ቤተ ሙከራ ስለመምጣቱ 'በርካታ ማስረጃዎች' አሉን አሉ

  5. ወረርሽኙ የዓለምን የካርቦን ልቀት ምን ያህል ቀንሷል?

    እንቅስቃሴ የማይታይበት መንገድ

    የፎቶው ባለመብት, Getty Images

    የምስሉ መግለጫ, በወረርሽኙ ሳቢያ የተጣለው የጉዞ እገዳ የአየር ብክለትን ቀንሷል

    በኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ሳቢያ አገራት የጣሉትን የእንቅስቃሴ ገደብን ተከትሎ በዚህ ዓመት የዓለማችንን የካርቦን ልቀት 8 በመቶ ለመቀነስ ታስቧል፡፡

    ዓለምአቀፉ የኢነርጂ ኤጀንሲ ቅናሹም በጎርጎሮሳዊያኑ 2008 ከፍተኛ ሆኖ ተመዝግቦ ከነበረው በስድስት እጥፍ ሊበልጥ እንደሚችል ትንበያውን አስቀምጧል፡፡

    የካርቦንዳይኦክሳይድ ልቀቱ በአስር ዓመት ውስጥ ወደ ዝቅተኛ ደረጃ እንደሚመለስም ኤጀንሲው ጠቁሟል፡፡

    በጉዞ ላይ እንዲሁም በንግድ ተቋማት ላይ የተጣለው ገደብ የአየር ብክለት ማስወገዱን ኤጀንሲው አስታውቋል፡፡ ነገር ግን የቀነሰበት ምክንያት የሚያስደስት አይደለም ብለዋል፡፡

    የካርቦንዳይኦክሳይድ (በካይ ጋዝ) ልቀት በፍጥነት መቀነስ አለበት፤ ነገር ግን ኢኮኖሚውን በመዝጋት መሆን እንደሌለበት ተመራማሪዎች ተናግረዋል፡፡

  6. በናይጄሪያ የቤት ውስጥ ጥቃት በከፍተኛ ሁኔታ መጨመሩ ተገለፀ

    በናይጄሪያ እየተራመደች ያለች ሴት

    የፎቶው ባለመብት, Getty Images

    በናይጄሪያ የቤት ውስጥና ወሲባዊ ጥቃቶች በከፍተኛ ሁኔታ መጨመራቸውን በስርአተ-ፆታ ላይ የሚሰሩ ባለሙያዎች ተናግረዋል። የድረሱልን ጥሪዎችም በማስተናገድ ላይ መሆናቸውን ገልፀዋል።

    የኮሮናቫይረስን መዛመት ለመግታት አገራት የእንቅስቃሴ ገደቦችን እንዲሁም አስገዳጅ ቤት መቀመጥ ውሳኔዎችን ተከትሎ በአለም ላይ የቤት ውስጥ አካላዊ ጥቃቶች፣ መደፈሮች በከፍተኛ ሁኔታ መጨመራቸውን ሪፖርት እንደደረሰው የተባበሩት መንግሥታት አሳውቆ ነበር።

    የሌጎስ የቤትና ወሲባዊ ጥቃቶች ምላሽ ሰጪ ቡድን እንዳሳወቀው የሚደርሷቸው ሪፖርቶች እንዲሁም የስልክ ጥሪዎች በከፍተኛ ሁኔታ በመጨመራቸው ተጨማሪ ሰራተኞችን መቅጠር ግድ ሆኖባቸዋል።

    "ጥቃት የደረሰባቸው ሴቶች በምን ሁኔታ መከላከል ወይም እንዴት እንደሚያመልጡ ግራ ገብቷቸዋል። ከቤት መውጣት አይችሉም፤ እርዳታም መጠየቅ አልቻሉም፤ አጣብቂኝ ውስጥ ነው ያሉት" በማለት የቡድኑ አስተባባሪ ቲቲዮላ ቪቮር አዴንየ ተናግረዋል።

    "ፖሊሶች ጋር በመተባበር ጥቃት የደረሰባቸውን ሴቶች ከቤታቸው ማስወጣት ችለናል። በአንዳንድ ቤቶች ላይ ደግሞ ጥቃት አድራሾቹን በግዳጅ ከቤት እንዲወጡ አድርገናል" ብለዋል።

    በናይጄሪያ ጥቃት የደረሰባቸውን ሴቶች ትክክለኛ ቁጥር ማግኘት አዳጋች ነው ምክንያቱም ብዙዎቹ ደብቀው ስለሚይዙት ነው።

    "በአንዳንድ ማህበረሰብ ውስጥ መስማት የማይፈልጉት ጉዳይ ነው። አንዲት ሴት ጥቃት ደረሰብኝ ብላ ብትናገር እንደ ቆሻሻ፣ ቤተሰቦቿን እንዳዋረደች ትታያለች" በማለት ወሲባዊ ጥቃት ከደረሰባቸው ጋር የሚሰሩት የስነ ልቦና ባለሙያ ኦኖኖ አናታኩ ይናገራሉ።

    በአገሪቷ ውስጥ ያሉት የድጋፍ ሰጪ ማዕከላት ጥቃት የደረሰባቸውን ሴቶች ድጋፍ በመስጠት ላይ ይገኛሉ።

    የተባበሩት መንግሥታት መረጃ እንደሚያሳየው በናይጄሪያ 23 በመቶ የሚሆኑት ሴቶች አካላዊ እንዲሁም ወሲባዊ ጥቃቶች በትዳር አጋሮቻቸው ይደርስባቸዋል።

  7. በለንደን በቫይረሱ በርካታ ጥቁሮች ሞተዋል ተባለ

    አፍና አፍንጫዋን በማስክ የሸፈነች ሴት

    በለንደን በቫይረሱ የሞቱ ጥቁሮች ቁጥር ካላቸው ብዛት ጋር ሲነጻጸር ያልተመጣጠነ መሆኑ ተነገረ፡፡

    የብሔራዊ ጤና አግልግሎት አዲስ ባወጣው መረጃ በለንደን ሆስፒታል በኮሮናቫይረስ የሞቱ ሰዎችን ዘር ይፋ አድርጓል፡፡

    በዚህም መሰረት ከከተማዋ ህዝብ 13 በመቶ የሚሆነውን የሚሸፍኑት ጥቁሮች ቢሆኑም በቫይረሱ ከሞቱት 16 በመቶዎቹ ጥቁሮች መሆናቸው ተገልጿል፡፡

    የወረርሽኝ በሽታ ባለሙያ የሆኑት ዶ/ር ሺክታ ዳስ በከተማዋ አነስተኛ ቁጥር ያላቸው ጥቁሮች በብዛት በሽታውን ለመቆጣጠር በግንባር ቀደምትነት ከተሰለፉ ባለሙያዎች መካከል ይገኙ ነበር ብለዋል፡፡ ይህም ለበሽታው ይበልጥ ተጋላጭ እንዲሆኑ አድርጓቸዋል፡፡

    ይሁን እንጅ ዶ/ር ዳስ ተጨባጭ ዝርዝር መረጃ ስለሚያስፈልግ ትክክለኛ ምክንያቱ እንዲህ ነው ብሎ መደምደም አስቸጋሪ ነው ብለዋል፡፡

    ቢቢሲ ከብሔራዊ የጤና አገልግሎት ባገኘው መረጃ 3 ሺህ 929 ሞቶችን ዘር ላይ ተመስርቶ ተንትኗል፡፡ በዚህም መሠረት በለንደን ሆስፒታል ቁጥራቸው ያልተመጣጠነ ጥቁሮች በኮቪድ -19 ሞተዋል፡፡

    ከሞቱት መካከል 55 በመቶ የሚሆኑት ነጮች ቢሆኑም ነጮች ግን የከተማዋን ሕዝብ ሰፊ ቁጥር የሚሸፍኑ ናቸው፡፡ በተመሳሳይ በቫይረሱ የሞቱ እስያዊያን ቁጥርም አነስተኛ ነው ተብሏል፡፡

    በለንደን ከቫይረሱ ጋር በተያያዘ 5 ሺህ የሚጠጉ ሰዎች ሕይወታቸው አልፏል፡፡

  8. በአሜሪካ በቬንትሌተር ታግዛ የወለደችው ታራሚ አረፈች

    የታሰሩ ሰዎች ይፈቱ እያለች የምትቃወም ሴት

    የፎቶው ባለመብት, Getty Images

    በአሜሪካ ታራሚ የሆነችው አንድሪያ ሰርክል ቤር በቬንትሌተር በመታገዝ ልጇን ከተገላገለች በኋላ ሕይወቷ አልፏል።

    በኮቪድ-19 በፅኑ ታማ የነበረችው አንድሪያ በቬንትለተርም ነው ስትተነፍስ የነበረችው።

    ከሁለት ቀናት በፊት ህይወቷ ያለፈው አንድሪያ ከአደንዛዥ ዕፅ ማዘዋወር ጋር በተያያዘ ወንጀል ሁለት አመት ከሁለት ወር ተፈርዶባት ደቡብ ዳኮታ ውስጥ በእስር ላይ ነበረች።

    በኮሮናቫይረስ ክፉኛ በተመታችው አሜሪካም በማረሚያ ቤት በኮሮና የሞተች የመጀመሪያ ሴት ታራሚ ሆናለች።

    የአሜሪካ የማረሚያ ቤቶች አስተዳደር ጨቅላዋ በምን ሁኔታ ላይ እንዳለች ከመግለፅ ተቆጥቧል።

    እስካሁን ባለው መረጃ በአሜሪካ ባሉ ማረሚያ ቤቶች 30 ታራሚዎች በኮሮናቫይረስ ህይወታቸውን አጥተዋል።

    የኮሮናቫይረስ መዛመትንም ለመከላከል 1ሺህ 751 ታራሚዎች ወደ ለይቶ ማቆያ ቤቶች ተወስደዋል። ነገር ግን አንድሪያ ቅድሚያ ይሰጣቸው ከተባሉ ታራሚዎች መካከል ውስጥ አልተካተተችም።

    በአጠቃላይ 2.3 ሚሊዮን የሚሆኑ ሰዎች በታሰሩባት አሜሪካ፣ ሚሊዮኖችን እስር ቤት በማስገባትም ከአለም ቀዳሚዋ ሃገር ናት።

  9. ላይቤሪያ የቤተ ሙከራ ሠራተኞችን ስልክ መፈተሽ ጀመረች

    የኮሮናቫይረስ ምርመራ ውጤቶች ሾልከው እየወጡ ነው በሚል የላይቤሪያ መንግሥት የቤተ ሙከራ ሠራተኞችን ስልክ መፈተሽ ጀምሯል።

    ኦኬ ኤፍኤም ሠራተኞቹን ጠቅሶ እንደዘገበው፤ ፕሬዘዳንት ጆርጅ ዊሃ ቫይረሱ ተገኝቶባቸዋል የሚል ወሬ በማኅበራዊ ሚዲያ መናፈሱን ተከትሎ ነው እርምጃው የተወሰደው።

    ፕሬዘዳንቱ ቫይረሱ አልተገኘብኝም ብለዋል።

    ወሬው መናፈስ የጀመረው የአገሪቱ የፍትሕ እና የመረጃ ሚንስትሮች ቫይረሱ እንደተገኘባቸው ከተገለጸ በኋላ ነበር።

    ኮቪድ-19ን ለመቆጣጠር የተቋቋመውን ግብረ ሀይል የሚመሩት ዶ/ር ሞሶካ ፋላህ፤ የአገሪቱ ደህንነት ተቋም የቤተ ሙከራ ሠራተኞችን ስልክ እየፈተሸ ስለመሆኑ አስተያየት ከመስጠት ተቆጥበዋል።

    ላይቤሪያ

    የፎቶው ባለመብት, Getty Images

  10. በኢትዮጵያ እስካሁን 17842 የኮቪድ-19 የላብራቶሪ ምርመራ ተደርጓል ተባለ

    በኢትዮጵያ ባለፉት 24 ሰዓታት 1408 የላብራቶሪ ምርመራ ተደርጎ አንድ ሰው በኮሮናቫይረስ መያዙ መረጋገጡን ጤና ሚንስትር አስታወቀ።

    ባለፉት 24 ሰዓታት የተደረገው የላብራቶሪ ምርመራ ከዚህ ቀደም ከተደረጉት ከፍተኛው ነው።

    ዛሬ በሽታው እንደተገኘባቸው የተገለጸው ሴት የ45 ዓመት የባህር ዳር ነዋሪ ሲሆኑ፤ በቫይረሱ ከተያዘ ሰው ጋር ንክኪ ነበራቸው ተብሏል። እስካሁን ኢትዮጵያ ውስጥ በበሽታው የተያዙ ሰዎች 131 ደርሰዋል።

    ኢትዮጵያ እስካሁን ድረስ 17842 የላብራቶሪ ምርመራ ያደረገች ሲሆን፤ ባለፉት 24 ሰዓታት 1408 ምርመራ ተደርጓል።

    በበሽታው ከተያዙ መካከል በለይቶ ህክምና ውስጥ ያሉት 67 ሲሆኑ፤ 59 ሰዎች አገግመዋል። ሦስት ሰዎች ደግሞ በቫይረሱ ሳቢያ ሕይወታቸውን አጥተዋል።

  11. የልጄን ገዳይ ልቀቁልኝ ያሉት እናት

  12. የአፍሪካ ቀንድ ሶስት ችግሮችን በአንድ ላይ ተጋፍጧል ተባለ

    በሶማሊያ በጎ ፈቃደኛ በስደተኞች መጠለያ ውስጥ የንጽህና መጠበቂያ ስታከፋፍል

    የፎቶው ባለመብት, Getty Images

    ሴቭ ዘ ችልድረን በአፍሪካ ቀንድ ታይተው የማይታወቁ ሶስት ችግሮች በአንድ ላይ እንደተደቀኑበት አስጠነቀቀ።

    እንደ ግብረ ሰናይ ድርጅቱ ማስጠንቀቂያ የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ፣ የአንበጣ መንጋ ወረርሽኝና የጎርፍ መጥለቅለቅ የአፍሪካ ቀንድን በአንዴ እየፈተኑ ያሉ ሶስት ችግሮች ናቸው።

    እንደ ድርጅቱ ከሆነ እድሜያቸው ከአምስት አመት በታች የሆነ ከአምስት ሚሊየን ሕፃናት በላይ በከፍተኛ የምግብ እጥረት ተጎድተዋል፣ እንዲሁም የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ደግሞ የአገራቱን ምጣኔ ሃብት እና የጤና ስርዓት እየጎዳው ይገኛል።

    በአፍሪካ ቀንድ በቅርቡ የጣለው ተከታታይ ዝናብ የጎርፍ አደጋ ማስከተሉ የሚታወስ ሲሆን፣ የአንበጣ መንጋ ወረርሽኝም በመጪው ሰኔ ወር ተስፋፍቶ ቀጠናውን እንደሚያጠቃ ተገምቷል።

    ሴቭ ዘ ችልድረን የዓለም አቀፍ ድርጅቶች ሁኔታው ከቁጥጥር ውጪ ሊወጣ ይችላል በማለት ሶማሊያን፣ ኬንያን፣ ኢትዮጵያን ችግሩን መቋቋም እንዲችሉ ድጋፍ እንዲያደርጉ አስቸኳይ ጥሪ አቅርቧል።

    ድርጅቱ አክሎም በእነዚህ አገራት ወረርሽኙ ሚሊየኖች በሚገኙበት የተፈናቃዮች መጠለያ ጣብያዎች ሊስፋፋ ይችላል ብሏል።

  13. ኬንያውያን መንግሥታቸው ላይ ተበሳጭተዋል

    ዝቅተኛ ገቢ ያላቸው ኬንያውያን በዚህ የኮሮና ወረርሽኝ ወቅት የምግብ እርዳታ ከመንግሥት ይቀበላሉ

    የፎቶው ባለመብት, AFP

    ኬንያውያን በአገራቸው የጤና ሚኒስቴር ብስጭት ብለዋል። ሚኒስቴሩ ለሻይ፣ ኩኪስና ለሰራተኞቹ ተንቀሳቃሽ ስልክ አየር ሰዓት ሚሊየኖችን አውጥቷል በሚል ነው የተቆጡት።

    ይህ ወጪ ደግሞ የተመዘገበው በዚህ የኮሮናቫይረስ ስርጭት በተስፋፋበት ወቅት መሆኑ የኬንያውያኑን ቁጣ አግሎታል።

    4 ሚሊየን የኬንያ ሽልንግ ወደ አሜሪካ ዶላር ሲቀየር 37 ሺህ ማለት ነው። ሚኒስቴሩ ይፋ ባደረገው የበጀት ሪፖርት ላይ ሁለት ሚሊየን ሽልንጉ የተመዘገበው ለሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ሰራተኞች የአየር ሰዓት ወጪ በሚል ነው።

    ይህ ከተመደበው ወጪ ውስጥ 10 ሚሊየን ሺሊንግ ላልተጠቀሰ ጊዜ ለሻይና ለኩኪስ፣ ስድስት ሚሊየን ደግሞ ለአየር ሰዓት ወጪ ለሶስት ወር በሚል ተቀምጧል።

    ከሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ በጀት መካከል አምቡላንስ ለመመደብ፣ ለቢሮ ጽህፈት መሳረሪያዎች ግዢ እና ለነዳጅ የወጣው ገንዘብ የኬንያውያኑን ቁጣ ያጋለ ሆኗል።

    ይህ ወጪ የተደረገው የዓለም ባንክ ለኬንያ የኮሮና ወረርሽኝን ለመከላከል ከሰጠው 9.3 ሚሊየን ዶላር ውስጥ የሚካተት ነው ተብሏል።

    የኬንያ ጋዜጦች ይህንን ዜና በፊት ገፃቸው ይዘው ሲወጡ ኬንያውያን ደግሞ በማህበራዊ መገናኛ ብዙኀን በኩል 'የሚበሉት የሌላቸው ኬንያውያን እንዲሁም በቂ መከላከያ የማያገኙ የህክምና ባለሙያዎች ምንኛ ያሳዝናሉ' በማለት በሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ወጪ ላይ ያላቸውን ምሬት ገልፀዋል።

    የ X ይዘትን ይለፉት
    ይዘቱን X ይፈቅዳሉ?

    ይህ ጽሑፍ በX. የቀረበ ይዘት ይዟል። ገጹ ቴክኖሎጂዎች ወይም ኩኪዎች ሊኖረው ስለሚችል ገጹ ከመከፈቱ በፊት የእርስዎን ፍቃድ እንጠይቃለን። ፍቃድዎን ከመስጠትዎ በፊት የX ኩኪ ፖሊሲ እና የ ማንበብ ይፈልጉ ይሆናል። ይዘቱን ለማንበብ ‘እቀበላለሁ ቀጥል’ የሚለውን ይምረጡ።

    ማሳሰቢያ: በሌሎች ገጾች ላይ ላሉ ይዘቶች ቢቢሲ ኃላፊነት አይወስድም።

    የ X ይዘት መጨረሻ

    " በዚህ ዓለም አቀፍ ወረርሽኝ ወቅት ኬንያውያንን ለአስገዳጅ ለይቶ ማወቆያ እና ተያይዞ ላሉ ሕክምናዎች ታስከፍላላችሁ፤ ነገር ግን ያለ እፍረት ሚሊየኖችን ለሻይና ለጽህፈት መሳሪያ ማውጣታችሁን ትነግሩናላችሁ" በማህበራዊ ሚዲያ ከተሰጡ አስተያየቶች መካከል ይገኝበታል።

  14. በጀርመን የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ዳግም እያንሰራራ ነው

    ኮሮናን ለመዋጋት እንተባበር የሚል ጽሑፍ

    የፎቶው ባለመብት, EPA

    በጀርመን ባለፉት 24 ሰዓታት ብቻ 1ሺህ 478 ሰዎች በኮቪድ-19 መያዛቸው በምርመራ መረጋገጡ ተነገረ። በኮሮናቫይረስ የተያዙ ሰዎች ቁጥር በተከታታይ ሲጨምር ይህ አራተኛ ቀኑ ነው።

    በጀርመን በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች አጠቃላይ ቁጥር 160 ሺህ የደረሰ ሲሆን ከእነዚህም መካከል 75 በመቶ ያህሉ አገግመዋል ተብሏል።

    አሁን ሕክምናቸውን እየተከታተሉ ያሉ ሰዎች ደግሞ 34,672 መሆናቸው ተገልጿል።

    ከኮቪድ-19 ጋር የተያያዙ ሞቶች ከ173 ወደ 6,288 ከፍ ማለቱም ነው የተነገረው።

    ጀርመን ባለፈው ሳምንት የእንቅስቃሴ ገደቡን ማላላት ጀምራ የነበረ ቢሆንም አሁን የቫይረሱ ስርጭት ዳግም ከፍ ለማለቱ ምክንያት ይሁን አይሁን የተባለ ነገር የለም።

    አብዛኛዎቹ ጀርመናውያን መንግሥት የእንቅስቃሴ ገደቡን በማንሳቱ ደስተኞች አይደሉም ተብሏል።

  15. የ17 ዓመቷ ታዳጊ ዩኒሴፍን ረዳች

    ግሬታ ተንበርግ

    የፎቶው ባለመብት, Getty Images

    ስዊድናዊቷ የአየር ንብረት ተሟጋች ግሬታ ተንበርግ፣ በሽልማት የተቀበለችውን 100ሺህ ዶላር ለተባበሩት መንግሥታት ህጻናት ኤጀንሲ ድጋፍ አደረገች። ገንዘቡ የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝን ለመከላከል ይውላል ተብሏል።

    ግሬታ የሰጠችውን የገንዘብ ሽልማት ልክ ረሃብን ለማጥፋት የሚሰራው የዳኒሽ ድርጅት (Danish anti-poverty organisation Human Act) ለዩኒሴፍ አበርክቷል።

    "ልክ እንደ አየር ንብረት ለውጥ ቀውስ ወረርሽኙም የሕፃናት ችግር ነው" ብላለች ግሬታ።

    "ሁሉንም ሕፃናት አሁንም ሆነ በረዥም ጊዜ ያጠቃል፤ ነገር ግን ተጋላጭ የሆኑ ቡድኖች የበለጠ ይጎዳሉ። ሁሉንም አካላት የምጠይቀው ህፃናትን ለመከላከልና ትምህርትን ለማስቀጠል ዩኒሴፍን በመደገፍ አብራችሁኝ እንድትቆሙ ነው።"

  16. የሴራሊዮን ማረሚያ ቤት በተቃውሞ እየተናጠ ነው

    ማረሚያ ቤት

    የፎቶው ባለመብት, Anadolu / Getty Images

    በሴራሊዮን በቅርቡ ማረሚያ ቤት የገባ ግለሰብ የኮሮናቫይረስ ምልክቶች ማሳየቱን ተከትሎ ታራሚዎች ለማምለጥ ሙከራ ማድረጋቸው ተገለጸ።

    ፓዴምባ ሮድ በተባለው ማረሚያ ቤት በተነሳው ተቃውሞ አስተዳዳሪው ሲሞት፤ ብዙዎች ጉዳት ደርሶባቸዋል። እስር ቤቱም በእሳት ጋይቷል።

    ማረሚያ ቤቱ 300 ሰዎች ማቆየት ቢችልም አሁን የታሰሩት ከ1,000 በላይ ናቸው።

    በሴራሊዮን የኮሮናቫይረስ ስርጭትን ለመግታት ፍርድ ቤቶች ሥራ አቁመዋል።

    በአገሪቱ 104 ሰዎች በቫይረሱ ሲያዙ አራት ሰዎች ደግሞ ሞተዋል።

  17. ናይጄሪያ የመንግሥት መሥሪያ ቤቶችና ባንኮች ልትከፍት ነው

    ናይጄሪያ

    የፎቶው ባለመብት, AFP

    በናይጄሪያ ከሰኞ ጀምሮ የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች እና ባንኮች እንደሚከፈቱ ተገለጸ።

    የኮሮናቫይረስ ስርጭትን ለመግታት የተቋቋመው ግብረ ኃይል፤ አቡጃ፣ ሌጎስ እና ኦጉን ቀስ በቀስ እንቅስቃሴ ይጀምራሉ ብሏል።

    የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች ሲከፈቱ በሠራተኞች እንዳይጨናነቁ በመጀመሪያው ዙር ሥራ የሚጀምሩ ሰዎች ተለይተዋል። ባንኮች ከጠዋቱ ሁለት ሰዓት እስከ ስምንት ሰዓት ብቻ ይሠራሉ።

    የግብረ ኃይሉ አስተባባሪ ሳኒ አሊዩ፤ ትምህርት ቤቶች እንደማይከፈቱና ሬስቶራንቶች የመስተንግዶ አገልግሎት ባይሰጡም ለተጠቃሚዎች ምግብ እንደሚያደርሱ ተናግረዋል።

    የሕዝብ ማጓጓዣ ከጠዋቱ 12 ሰዓት እስከ ምሽቱ 12 ሰዓት ድረስ አገልግሎት ይሰጣል።

    አምራቾችም ወደ ሥራ እንዲመለሱ ቢፈቀድም፤ ማሰማት የሚችሉት የተወሰኑ ሠራተኞች ብቻ ነው።

  18. ፖምፒዮ ደቡብ አፍሪካ የኩባ ዶክተሮችን በመቀበሏ ወረፉ

    ደቡብ አፍሪካ የኩባ የሕክምና ባለሙያዎችን ድጋፍ ከጠየቁ 22 አገራት መካከል አንዷ ናት

    የፎቶው ባለመብት, Getty Images

    የአሜሪካው ውጪ ጉዳይ ሚኒስትር ደቡብ አፍሪካ የኮቪድ-19 ስርጭትን ለመግታት የምታደርገውን ጥረት እንዲያግዟት ከ200 በላይ የኩባ ዶክተሮችን መቀበሏን ወረፉ።

    ደቡብ አፍሪካ የኩባ የሕክምና ባለሙያዎችን ድጋፍ ከጠየቁ 22 አገራት መካከል አንዷ ናት።

    ማይክ ፖምፒዮ ኩባን ከወረርሽኙ ለማትረፍ እየተሯሯጠች ነው ሲሉ ለአጃንስ ፍራንስ ፕሬስ ተናግረዋል።

    "በብራዚል፣ኢኳዶር፣ ቦሊቪያና ሌሎች አገራት በኩባ ያለውን ጨቋኝ መንግሥት እንዳላዩ ለማለፍ ባለመምረጣቸው እናደንቃቸዋለን" ብለዋል።

    "እና ሁሉም አገራት ተመሳሳይ ነገር እንዲያደርጉ እንጠይቃለን፤ ደቡብ አፍሪካንና ኳታርን ጨምሮ።"

    የኩባ የሕክምና ቡድን ደቡብ አፍሪካ የደረሰው እሁድ እለት ነበር። የተለያዩ ባለሙያዎች ስብጥር መሆኑም ተነግሯል።

    የኩባው ፕሬዝዳንት በበኩላቸው "አሜሪካ ሆን ብላ የኩባን ዓለም አቀፍ የሕክምና ትብብርን በውሸት ስም ለማጥፋት እየሰራች ነው" ሲሉ በትዊተራቸው ላይ ምላሽ ሰጥተዋል።

  19. ኮሮናቫይረስ አንድ ጊዜ ከያዘን በቀሪው ህይወታችን አብሮን ይኖራልን?

  20. በዓለማችን በኮቪድ-19 ምከንያት ከፍተኛ ሞት ያስመዘገቡ አገራት

    ኮሮናቫይረስ

    የፎቶው ባለመብት, Getty Images

    የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ከተከሰተ ጊዜ አንስቶ የስርጭት አድማሱን ባሰፋ ቁጥር ማዕከሉም ይቀያየራል።

    ከቻይና የተነሳው ይህ ቫይረስ ደቡብ አውሮፓን ማዕከል አድርጎ ከቆየ በኋላ አሁን ደግሞ በአሜሪካ እየተስፋፋ ይገኛል። እንደ ዓለም ጤና ድርጅት ከሆነ ቀጠዩ የቫይረሱ ማዕከል የምትሆነው አፍሪካ ናት።

    የትኞቹ አገራት በቫይረሱ ምከንያት በርካታ ሰዎችን አጡ?

    ይህ ጥያቄ ቀላል ይምሰል እንጂ ውስብስብ ነው። ምክንያቱ ደግሞ የተለያዩ አገራት የሞት ሁኔታን የሚመዘግቡት በተለያየ መልኩ መሆኑ ነው።

    ለምሳሌ ቤልጂየምን ብንወስድ በርካታ የአረጋውያን መጦሪያና ማገገሚያ ቤቶች የተከሰቱ ሞቶችን በኮቪድ-19 የተከሰቱ መሆናቸውን አልመዘገበችም። ይህንን አድርጋ ቢሆን በሰንጠረዡ ላይ ካሉ ከተመሳሳይ አገራት ጋር ስትነፃፀር ከፍተኛ የሞት ቁጥር ካስመዘገቡት ቀዳሚዎች ተርታ ትሰለፍ ነበር።

    ዕሮብ እለት በዩናይትድ ኪንግደም የተከሰቱ ሞቶች በስፔንና ፈረንሳይ ከተከሰቱት በልጦ ታይቷል። ይህ ደግሞ የሆነው ሆስፒታል ሳይመጡ በአዛውንቶች የእንክብካቤ ማዕከላት የሞቱትን ለመጀመሪያ ጊዜ መመዝገብ በመጀመሯ ነው።

    ጆንስ ሆፕኪንስ ዩኒቨርስቲ በቅደም ተከተል ያስቀመታቸው አስር አገራትን እነሆ፡

    • አሜሪካ 61,000
    • ጣልያን 27,682
    • ዩናይትድ ኪንግደም 26,166 (መንግሥት 26,097 ሞቶች ናቸው ብሏል)
    • ስፔን 24,275
    • ፈረንሳይ 24,121
    • ቤልጂየም 7,501
    • ጀርመን 6,467
    • ኢራን 5,957
    • ኔዘርላንድስ 4,727
    • ቻይና 4,637