ፖምፔዎ ቫይረሱ ከቻይና ቤተ ሙከራ ስለመምጣቱ 'በርካታ ማስረጃዎች' አሉን አሉ
የኮሮናቫይረስን ለመከላከል ክትባትም ሆነ ለማከም የሚውል መድኃኒት እስካሁን አልተገኘም። ነገር ግን በየአገራቱ ያሉ ባለሙያዎች ሌት ተቀን ጥረት እያደረጉ መሆናቸው እየተነገረ ነው። መቼ ውጤት ላይ ሊደርሱ እንደሚችሉ ግን በእርግጠኝነት መናገር አይቻልም። ስለዚህ በእጃችን ላይ ያሉትን የመከላከያ መንገዶች በመጠቀም እራስን ከበሽታው መጠበቅ ብቸኛው መንገድ ነው። ለዚህ ደግሞ አካላዊ ርቀታችንን እንጠብቅ፤ እጃችንን በተደጋጋሚ በሳሙናና በውሃ እንታጠብ። ስለወረርሽኙ የሚቀርቡ የቀጥታ ዘገባዎችንና መረጃዎችን ከዚህ ገጽ ይከታተሉ።
የቀጥታ ሽፋን
ደቡብ አፍሪካ የኮሮናቫይረስ ህጎቿን እያላላች ነው

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ደቡብ አፍሪካ የኮሮናቫይረስን መዛመት ለመግታት አስገዳጅ የቤት መቀመጥ እንዲሁም ሙሉ በሙሉ እንቅስቃሴ እንዲቆም ወስና የነበረ ቢሆንም ከሰሞኑ እነዚህን ህጎች ለማላላት ወስናለች።
ለአምስት ሳምንታት የቆየውንም ውሳኔ በማላላት አንዳንድ የንግድ ቦታዎች እንዲከፈቱ፣ ሬሰቶራንቶችም ምግብ ቤቶች ማድረስ እንዲችሉ እንዲሁም አካላዊ እንቅስቃሴም ማድረግ ከዛሬ ጀምሮ የሚፈቀድ ይሆናል።
ሆኖም መንግሥት ተጨማሪ ሰራዊት በማሰማራት የሰአት እላፊው መከበሩን ይቆጣጠራል። የመጠጥ ሽያጭም እንደተከለከለ ይቆያል።
የወረርሽኙን መዛመት ለመከላከል ደቡብ አፍሪካ በአህጉሪቷ ውስጥ ጥብቅ የሚባሉ መመሪያዎችን አስተላልፋ ነበር።
በአገሪቷ ውስጥ 100 ሰዎች በኮሮናቫይረስ ህይወታቸውን ያጡ ሲሆን፤ ሙሉ በሙሉ እንቅስቃሴም መቆሙ ኢኮኖሚዋ ላይ ከፍተኛ ጫና አሳርፏል ተብሏል።
በርካታ ዜጎቿ በድህነት በሚኖሩባት ደቡብ አፍሪካ ካለው የምጣኔ ኃብት ኢ-ፍትሃዊነትና የኮሮናቫይረስ ጫና ጋር ተደማምሮ በርካታ ችግሮችን እንደሚያስከትልም እየተነገረ ነው።
ክፉን ጊዜ ማለፍ ተጋግዞ ነው ያሉ ኢትዮጵያ ወጣቶች
እስክንድር ተሾመና ጓደኞቹ የሚኖሩት ኢትዮጵያ ነው። ኮሮናቫይረስ እንደተከሰተ ያስተዋሉት ነገር የበርካታ ቁሳቁሶችን እጥረት ነው።
እጥረቱ ግን አንድ ሰው ጋር ይከሰት እንጂ ሌላ ቦታ ትርፍ ሊኖር እንደሚችል ጥርጣሬ አልገባቸውም። ታዲያ ይህንን አንድ ቦታ እጥረት የሌላው ትርፍ ቁሳቁስን በምን መልኩ ሊያቃልሉት ይችላሉ? ድረገጽ በመክፈት።
እስክንድር ለቢቢሲ እንደገለፀው የተለያዩ የህክምና ቁሳቁሶች እጥረትን ለመቅረፍ ድረገፁ ሁነኛ መፍትሄ ነው።
“ለማይሰጥ ሰው ስጡኝን ማን አስተማረው” የሚለው እስክንድር ክፉ ጊዜን ማለፍ ተጋግዞ ነውና ያለንን እንለግስ ሲል ጥሪ ያቀርባል።
ለዚህ ነው ከረዳቶቹ ጋር በመሆን www.ethiopics.org ድረገጽ የከፈተው። የዚህ ድረገፅ ዓላማ ትርፍ ቁሳቁስ ያላቸው ሰዎች፣ ያላቸውን ለሌሎች ማጋራት እንዲችሉ መሆኑን እስክንድር ጨምሮ ያስረዳል።
ቁሳቁስ ለመለገስ ፍላጎት ያለው ሰው ወደ ድረገፁ ገብቶ መመዝገብ ይጠበቅበታል። ከዚያም ያለውን ትርፍ ቁሳቁስ ፎቶ በማንሳትና አንዳንድ መግለጫ በመጻፍ መለጠፍ ይችላል።
እነዚህን ቁሳቁሶች በየዓይነታቸው ከፋፍሎ ለተጠቃሚዎች ማሳየት የእስክንድር እና የጓደኞቹ ድርሻ ነው። ቁሳቁሶቹን የሚፈልግ ማንኛውም ሰው ወደ ድረገፁ ገብቶ የለጋሹን አድራሻ በቀላሉ ማግኘት እንደሚችል የሚናገሩት አቶ እስክንድር ከለጋሹ ጋር መልዕክት በመለዋወጥና በመነጋገር ይቀባበላሉ ብለዋል።
ታዲያ ምን ትርፍ ነገር አለዎት?

የፎቶው ባለመብት, Ethiopics Donation
በደቡብ አፍሪካ የሚገኙ ደጋግ ኢትዮጵያዊ እጆች

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የምስሉ መግለጫ, በጆሃንስበርግ የኢትዮጵያውያን የንግድ ማዕከል ተብላ የምትጠራው ጂፒ የኮሮና ወረርሽን ባስጨነቃቸው አገራት የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ሰብሰብ ብለው እርስ በእርስ እየተረዳዱ መሆኑን ሰምተናል።
በደቡብ አፍሪካ የተባበሩት የኢትዮጵያ ኮሚኒቲ አባል የሆኑት አቶ መሀመድ ረሺድና አቶ በላይ አዳነ ለቢቢሲ እንደተናገሩት በደቡብ አፍሪካ የሚገኙ ኢትዮጵያውያን አገሪቱ ጥላ ባለችው የእንቅስቃሴ ገደብ ምክንያት ኢትዮጵያውያንም ሆኑ ደቡብ አፍሪካውያን እንዳይቸገሩ በማሰብ የምግብ ድጋፍ እየደረጉ ነው።
እርዳታውን በጆሃንስበርግና በፕሪቶሪያ መሰጠቱን የገለፁት አቶ መሀመድ፣ ድጋፍ በማድረግ አንድ መቶ የሚሆኑ ኢትዮጵያውያን መሳተፋቸውን አቶ መሀመድ አክለው ተናግረዋል።
በጆሃንስበርግ 700 ለሚሆኑ ሰዎች የተለያዩ ምግቦችን እንዲሁም በተመሳይ በፕሪቶሪያ ደግሞ አንድ መቶ ሰው መረዳቱን ይናገራሉ።
ወደፊት ወደ ኢትዮጵያ አቅማቸውን በማሰባሰብ በኢምባሲው በኩል ለመላክ ዝግጁ መሆናቸውንም ጨምረው ገልፀዋል።
ያገገሙ ሰዎች ቁጥር 1 ሚሊየን መድረሱ ምን ይነግረናል?

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ከ3 ሚሊየን በላይ በኮሮናቫይረስ የተያዙ ሰዎች በዓለማችን አሉ። ከእነዚህ መካከል 1 ሚሊየኑ ከቫይረሱ ማገገማቸው ተነግሯል። ቢሆንም ይህ መረጃ በጥንቃቄ ሊታይ ይገባል።
ኮቪድ-19 የሞት መጠኑ ዝቅ ያለ ነው። ይህ ማለት ሁሉም ታማሚዎች ሊድኑ ይችላሉ። በአንዳንድ ሁኔታዎች ረዘም ያለ ጊዜ ሊወስድ ቢችልም።
ኦፊሴላዊ ከሆነው ውጭ ምን ያክል ሰዎች በትክክል እንደተያዙ ስለማይታወቅ የኮቪ-19 የሞት መጠን በወጉ ለመለየት አዳጋች አድርጎታል።
ዘ ላንሴት የተሰኘው ጆርናል የኮቪድ-19 የሞት መጠን ከኢንፍሉዌንዛ [0.1%] ይበልጣል፤ ከሳርስ [9.5%] ደግሞ ያንሳል ይላል።
ሁሉም ሰው የተመረመረበትና የታከመበት ቦታ [ለምሳሌ አንዲት የመዝናኛ መርከብ ላይ] የሞት መጠኑ 1 በመቶ ነው።
ነገር ግን የመመርመር አቅም ከሃገር ሃገር ስለሚለያይ [የትኛውም ሃገር መቶ በመቶ የመመርመር አቅም የለውም] የሞት መጠኑ የሚለካው መያዛቸው በምርመራ ከተረጋገጡት ጋር ተነፃፅሮ ነው።
በሽታው የፀናባቸው ሰዎች ብቻ ከተመረመሩ የሞት መጠኑ ከፍ ብሎ ሊታይ ይችላል። ይህም ማለት ብዙ ሰዎች ሳያውቁት ወይም አውቀውት ነገር ግን ወደ ጤና ማዕከል ሳይሄዱ ቫይረሱ ሊይዛቸው ይችላል። ይህ ደግሞ የተያዦችና ሟቾች ቁጥር ምን ያክል ነው የሚለውን ያዛበዋል።
ፕሬዝዳንት ትራምፕ ከአንድ ወር በኋላ ሽርሽር ሊሄዱ ነው

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ከአንድ ወር በላይ ከዋይት ኃውስ ውጪ ወደ የትም መንቀሳቀስ አልቻሉም ነበር።
አሁን ግን ዛሬ ሜሪላንድ ወደ ሚገኘው ካምፕ ዴቪድ ለሽርሽር ያመራሉ ተብሏል።
ፕሬዝዳንቱ ከዋይት ኃውስ 90 ኪሎ ሜትር ርቀው እንደሚሄዱ የተገለፀው ትናንት ነበር። ፕሬዝዳንቱ ምን ያህል ቀን በሽርሽር እንደሚያሳልፉ የታወቀ ነገር የለም።
ትራምፕ ለመጨረሻ ጊዜ ከዋይት ኃውስ የወጡት በጎርጎሳውያኑ አቆጣጠር መጋቢት 28 ሲሆን ጉዟቸውም ወደ ኖርፎክ፣ ቨርጂኒያ ነበር።
በቻይና አስራ ሁለት አዲስ ሰዎች በኮሮናቫይረስ ቢያዙም ሞት ሳይመዘገብ ቀረ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
በቻይና አስራ ሁለት አዲስ ሰዎች በኮሮናቫይረስ መያዛቸው የተገለፀ ሲሆን፣ ከነዚህም ውስጥ አራቱ ከቀናት በፊት የተመዘገቡ ናቸው።
ከነዚህም መካከል ስምንቱ ከሌላ አገራት የመጡ መንገደኞች ናቸው። በአገር ውስጥ በማህበረሰቡ መካከል ያለው መዛመት በአብዛኛው የቆመ ቢሆነም ሩሲያን በምታዋስናት ሄሊዮንጊያንግ ግዛት ባለፉት ሳምንታት በተወሰነ መልኩ ጭማሪ አሳይቷል ተብሏል።
በቫይረሱ ከተያዙት አዳዲሶቹ መካከል አምስቱ ከዚች ግዛት ናቸው።
የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ መነሻ በሆነችው ቻይና በአጠቃላይ 82ሺህ 874 ሰዎች በቫይረሱ ቢያዙም ዘጠና በመቶዎቹ አገግመዋል።
በአገሪቷ ውስጥ በኮሮናቫይረስ ምክንያት ሞት መመዝገብ ያቆመ ሲሆን፤ በአጠቃላይ በኮሮናቫይረስ ህይወታቸውን ያጡ ሰዎች ቁጥር 4ሺህ 633 ነው።
ትራምፕ ኮቪድ-19 ከቻይና ላቦራቶሪ ማምለጡን እርግጠኛ ናቸው

የፎቶው ባለመብት, EPA
የአሜሪካው ፕሬዝዳንት የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝን በሚመለከት ቻይናና የዓለም ጤና ድርጅትን ወረፉ።
ፕሬዝዳንቱ ቫይረሱ ከቻይና ቤተ ሙከራ ውስጥ ስለማምለጡ ከፍተኛ እምነት እንዳላቸው ተናግረዋል። ነገር ግን ቻይና በስህተት አልያም ይኹነኝ ብላ ቫይረሱን ታሰራጨው ምንም መናገር እንደማይፈልጉ ገልፀዋል።
ከዚህ ቀደም ብሎ፣ የአሜሪካ ደህንነት ባለስልጣናት ኮቪድ-19 " ሰው ሰራሽ ወይንም በላቦራቶሪ የተሰራ አይደለም" ብለው ነበር።
ከዚህ በፊት ትራምፕ ቻይና ስለቫይረሱ ለአሜሪካ ያልተናገረችው የእርሳቸውን ዳግም ምርጫ ለማደናቀፍ መሆኑን ተናግረው ነበር።
ፕሬዝዳንቱ የዓለም ጤና ድርጅትንም " የቻይና የሕዝብ ግንኙነት ሆኖ በመታየቱ ሊያፍር ይገባዋል" ሲሉ ወርፈውታል።
ከቻይና ጋር እሰጥ-አገባ ውስጥ ያለችው አውስትራሊያ ለታይዋን ወግናለች

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የአወስትራሊያ የዜና ምንጮች ሃገሪቱ ታይዋን ራሷን ችላ የዓለም ጤና ድርጅት አባል እንድትሆን ድጋፍ እያደረገች ነው ሲሉ ዘግበዋል።
አውስትራሊያ ከዚህ ቀደምም ቢሆን ታይዋን ሌላው ቢቀር የታዛቢነት ሚና እንዲሰጣት ትወተውት ነበር። በዚህ ሳምንት ደግሞ የታይዋን ጤና ሚኒስትር ከአውስትራሊያ ባለሥልጣናት ጋር በስልክ መክረዋል እየተባለ ነው።
ቻይና እና አውስትራሊያ ከሰሞኑ በክፉ እየተናቆሩ ነው።
ቻይና፤ ታይዋን ራሷን የቻለች አገር አይደለችም ብላ በመሞገት የዓለም ጤና ድርጅት አባል እንዳትሆን ከማገድ አልፋ የተባበሩት መንግሥታት አባል እንዳትሆን ማነቆ ሆናባታለች።
አውስትራሊያ ኮሮናቫይረስ መነሻው ከየት እንደሆነ በገለልተኛ ተቋም ይጣራ ማለቷ ነው ቻይናን ያስቆጣውና የንግድ ግንኙነቴን አቋርጣለሁ እስከሚል ዛቻ ያደረሳት።
የአውስትራሊያው ጠቅላይ ሚኒስትር ስኮት ሞሪሰን የቻይናን ትችት ችላ ብለው አሁንም ጉዳዩ ይጣራ በማለት ላይ ናቸው።
"የቱሪዝም እንቅስቃሴው ልክ መብራትን የማጥፋት ያህል በቅጽበት ቆሟል"
ከአንድ ሚሊየን በላይ ሰዎች ከኮቪድ-19 አገገሙ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
በዓለማችን ላይ ከኮሮናቫይረስ ያገገሙ ሰዎች ቁጥር ከአንድ ሚሊየን በላይ መሆኑ ተመዝግቧል።
እንደ ጆንስ ሆፕኪንስ አሁናዊ መረጃ ከሆነ በአጠቃላይ በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች ቁጥር ከሶስት ሚሊየን በላይ ነው።
በኮቪድ-19 ከተያዙት ሰዎች መካከል የሚሞቱት በጣም ጥቂቶቹ ናቸው። ይህም ማለት ከታመሙት መካከል አብዛኛዎቹ አገግመው ወደ ቀደመው ህይወታቸው የመመለስ እድላቸው ሰፊ ነው።
በርግጥ አንዳንዶች ለማገገም ረዘም ያለ ጊዜ ሊወስድባቸው ይችላል። በኮቪድ-19 ከተያዙት መካከል ምን ያህሉ ህይወታቸውን ያጣሉ? እንደ ላንሴት ሜዲካል ጆርናል ግምት ከሆነ ኮቪድ-19 ገዳይነቱ ከኢንፍሉዌንዛ (0.1%) ከፍ ያለ ከሳርስ (9.5%) ደግሞ ዝቅ ያለ ነው።
አገራት የመመርመር አቅማቸው ስለሚለያይ ያገገሙና ሕይወታቸውን ያጡ ሰዎችም ቁጥር በዚያው መጠን ይለያያል።
ከፍተኛ ምልክት የሚያሳዩ ሰዎችን በሚመረምር አገር የሚሞቱ ሰዎች ቁጥርም ከፍ ብሎ ሊገኝ እንደሚችል የሕክምና ባለሙያዎች ይናገራሉ።
የኮሮናቫይረስ እውነታን ስንመለከት በርካታ ሰዎች ሳይታወቅ በቫይረሱ ተይዘው ሊያገግሙ ይችላሉ። ይህም በዓለም አቀፍ በሚመዘገበው ይፋዊ ቁጥር ውስጥ አይካተትም።
እኛም ደህና ወዳጆቻችንም ጤና እንዲሆኑ በሕክምና ባለሙያዎች የሚሰጡ ምክሮችን ቸል አንበል።
እንደምን አደራችሁ የቢቢሲ ቤተሰቦች!
ሁሌም እንደምናደርገው ከኮሮናቫይረስ ጋር የተያያዙ የቀጥታ ዘገባችንን አሁን ማስነበብ እንጀምራለን።
- የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ኮቪድ-19 ከቻይና ቤተ ሙከራ ያመለጠ ስለመሆኑ እርግጠኛ ነኝ ስለማለታቸው
- ከኮሮናቫይረስ ያገገሙ ስንል ምን ማለታችን ነው?
- ደቡብ ኮሪያ ለሁለተኛ ቀን አንድም በአገር ውስጥ በቫይረሱ የተያዘ ሰው አለማግኘቷን
- በቻይና 12 ሰዎች በቫይረሱ ሲያዙ የሞተ ሰው ግን አለመኖሩንና ሌሎች አበይት ዜናዎችን መራርጠን እናስነብባችኋለን።
አብራችሁን ዋሉ!
መልካም ቀን ከቢቢሲ አማርኛ ጋር

በአየርላንድ መድኃኒቶችን ለማቀበል ሰው አልባ አውሮፕላኖች በስራ ላይ ዋሉ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
በኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ምክንያት ንክኪ የመፈጠሩ ሁኔታ በሚያሰጋበት ሁኔታ አየርላንድ በለይቶ ማቆያ ላሉ ግለሰቦች መድኃኒቶችን ለመስጠት ሰው አልባ አውሮፕላኖች (ድሮኖችን) በስራ ላይ አውላለች።
ሰው አልባ አውሮፕላኖቹ መድኃኒቶቹን በግለሰቦቹ በር ላይም ያስቀምጣሉ።
በሌሎች ቦታዎችም ሰው አልባ አውሮፕላኖችን መድኃኒቶች ለመላክ ሙከራ እየተደረገ ሲሆን፤ በአየርላንድ ያለውን ለየት የሚያደርገው የብሔራዊ ጤና ባለስልጣን በቀጥታ ተሳታፊ መሆኑ እንደሆነም ተዘግቧል።
የሩሲያ ጠቅላይ ሚኒስትር በኮሮና ተያዙ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የሩሲያ ጠቅላይ ሚኒስትር ሚሻይል ሚሹስቲን በኮሮና ቫይረስ መያዛቸው ተረጋግጧል።
እንደ ጆንስ ሆፕኪንስ መረጃ ከሆነ በሩሲያ እስካሁን 106 ሺህ 498 ሰዎች በቫይረሱ መያዛቸው ሲረጋገጥ 1 ሺህ 73 ሰዎች ሕይወታቸው አልፏል፡፡
ናይጄሪያውያን ባለሃብቶች ባዶ ህንፃዎቻቸውን ለለይቶ ማቆያነት እንዲሰጡ ተጠየቁ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የናይጄሪያ ጤና ሚኒስቴር በአገሪቱ ውስጥ ያሉ ባለሃብቶች ባዶ ህንፃዎቻቸውን በኮሮናቫይረስ ለተያዙ ህሙማን በለይቶ ማቆያነት እንዲያገለግሉ ለተወሰነ ጊዜ በውሰት እንዲሰጡ ጥሪ አቅርቧል።
የጤና ሚኒስትሩ ዶክተር ኦሳጊ ኤሃኒሬ እንደተናገሩት እነዚህ ህንፃዎች ለመንግሥት በውሰት የሚተላለፉት ለአጭር ጊዜ ነው ብለዋል።
የናይጄሪያ በሽታዎች ቁጥጥር ማዕከል ዳይሬክተር አገሪቷ የኮሮና ህሙማንን የምታክምበት ቦታ እጥረት እንደገጠማት ከሰሞኑ ተናግረው ነበር።
በመዲናዋ አቡጃና ካኖ ስጋቶች ቢኖሩም የወረርሽኙ ማእከል በሆነችው ሌጎስ ግን ችግሩ የከፋ እንደሆነም ዳይሬክተሩ አስረድተዋል።
ችግሩንም ለመቅረፍ ህሙማኑ የሚታከሙበትን የተለያዩ አማራጮችን እየፈለጉ እንደሆነ የተናገሩት ዳይሬክተሩ በቤት ውስጥ ሆኖ መታከምም አንዱ አማራጭ ነው ብለዋል።
ቦሪስ ጆንሰን ከኮሮና ካገገሙ በኋላ የመጀመሪያቸውን የሚኒስትሮች ስብሰባ መሩ

የፎቶው ባለመብት, No 10
የዩናይትድ ኪንግደም ጠቅላይ ሚኒስትር ቦሪስ ጆንሰን ከኮሮናቫይረስ ከዳኑ በኋላ የመጀመሪያቸውን የሚኒስትሮች ስብሰባ የመሩ ሲሆን ጋዜጣዊ መግለጫም ሰጥተዋል፡፡
ይህ ሳምንት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ፋታ ያጡበት እንደሆነ ተነግሯል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ወደ ስራ የተመለሱት ሰኞ ዕለት ሲሆን ትናንት ደግሞ የወንድ ልጅ አባት ሆነዋል፡፡
ዛሬ ደግሞ ከበሽታው ካገገሙ በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ የሚኒስትሮች ስብሰባን መርተዋል፡፡
ዛሬ በሰጡት መግለጫ ላይም በዩናይትድ ኪንግደም እስካሁን 26 ሺህ 771 ሰዎች በቫይረሱ መሞታቸውን ተናግረዋል፡፡
ሆኖም አገራቸው የወረርሽኙን ጣሪያ አልፋለች ብለዋል፡፡
ቦሪስ በሥራ ላይ ባልነበሩበት ጊዜ ስራቸውን በትጋት ሲያከናውኑ ለነበሩት በሙሉም ምስጋና አቅርበዋል፡፡

የፎቶው ባለመብት, No 10
በኮንጎ ማረሚያ ቤት በኮሮናቫይረስ የተያዙ ታራሚዎች ተገኙ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
በዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ በሚገኝ ማረሚያ ቤት በኮሮናቫይረስ የተያዙ የመጀመሪያ ታራሚዎች መገኘታቸው ተገልጿል።
አራት ታራሚዎች በኮሮናቫይረስ መያዛቸው የተረጋገጠ ሲሆን ሌሎች የተጠረጠሩ ታራሚዎች ደግሞ በመዲናዋ ኬንሻሳ በሚገኘው የንዶሎ ማረሚያ ቤት ለይቶ ማቆያ ገብተዋል።
በከፍተኛ ሁኔታ የተጨናነቀው ይህ ማረሚያ ቤት መያዝ ከሚገባው አራት እጥፍ በላይ ታራሚዎች ይገኙበታል።
የሰብአዊ መብት ድርጅቶች ቫይረሱ በቀላሉ ሊዛመት እንደሚችል ስጋታቸውን እየገለፁ ሲሆን፤ ከታራሚዎችም ተርፎ የሚጠይቋቸው ጎብኝዎችም ሊያዙ ይችላሉ ተብሏል።
እነዚሁ ድርጅቶች ቀላል የሚባል ወንጀል የፈፀሙ ታራሚዎች እንዲፈቱ የጠየቁ ሲሆን በዚህም መንገድ የማረሚያ ቤቱን መጨናነቅ መቀነስ ይቻላል እያሉም ነው።
የጤና ኃላፊዎች በማረሚያ ቤቱ አንድ ቡድን በማሰማራት ወረርሽኙ የደረሰበትን ሁኔታ ላይም ጥናት እያደረጉ መሆናቸው ተገልጿል።
በዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ኮሮናቫይረስ በሰባት ግዛቶቿ መዛመቱ የተረጋገጠ ሲሆን አብዛኛዎቹ በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች የሚገኙት ግን በመዲናዋ ኬንሻሳ ነው።
በሶማሊያ ወረርሽኙ ከተባለው በላይ ሊበረታ እንደሚችል ቀይ መስቀል አስጠነቀቀ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የምስሉ መግለጫ, በጎ ፈቃደኞች አንዳንድ ቁሳቁሶችን በስደተኞች ካምፕ እያሰራጩ ነው በሶማሊያ የሚገኘው ቀይ መስቀል በአገሪቷ በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች ቁጥር መንግሥት ካሳወቀው 582 በላይ እንዳይሆን ስጋት አለኝ ሲል አስጠነቀቀ፡፡
ሶማሊያ ወረርሽኙን ቀድሞ ለመከላከል ዝግጁነት አልነበራትም ተብሏል፡፡
የጤና ተቋማቷም ቢሆኑ ባለፉት ሦስት አስርት ዓመታት በነበረው ግጭት ወድመዋል፡፡ አብዛኞቹ ሆስፒታሎችም የህክምና መሳሪያዎች ቀርቶ የኤሌክትሪክ ኃይል እንኳን እንደ ልብ አያገኙም፡፡
በአገሪቷ የጤና አገልግሎት የሚያገኘውም ግማሽ የሚሆነው በከተማ የሚኖር ህዝብ ነው ፤ በገጠር አካባቢ አገልግሎቱን የሚያገኙ ሰዎች ቁጥር 15 በመቶ ቀንሷል፡፡
በመሆኑም በአገሪቷ ውስጥ ሰዎች እየሞቱ እንደሆነ ዶክተሮች እየተናገሩ ነው፡፡
አብዛኞቹ ሶማሊያዊያንም ውሃና ሳሙና በማይገኝባቸውና በተጨናነቁ ካምፖች ስለሚኖሩ ቫይረሱን ለመከላከል የሚደረጉ ጥንቃቄዎችን መፈጸም የማይታሰብ ነው፡፡
በአንዳንድ አካባቢዎች የሚሞቱ ሰዎች ቁጥር በመጨመሩ መቃብር ቆፋሪዎችን እንዳዳገተ ሪፖርቶች እየወጡ ነው፡፡
በሶማሊያ የአለም አቀፉ ቀይ መስቀል ኮሚቴ የጤና አስተባባሪ በመጭዎቹ ሳምንታት በቫይረሱ የሚያዙ ሰዎች ቁጥር ከፍተኛ ሊሆን ይችላል ብለዋል፡፡
በሞቃዲሾ የሚገኘው ማዲና ሆስፒታል ዳይሬክተር ዶ/ር መሐመድ ዩሱፍ በበኩላቸው በሽታውን ለመቆጣጠር የህክምና መሳሪያዎች ግብዓት እንደሌላቸው ተናግረዋል፡፡
ከኮሮናቫይረስ ያገገመው ኬንያዊ መገለል ደርሶብኛል እያለ ነው

የፎቶው ባለመብት, Ministry Health of Kenya
በኮሮናቫይረስ ተይዞ በማገገሙ በቅርቡ ከሆስፒታል የወጣው ኬንያዊ እሱም ይሁን ቤተሰቡ መገለል እንደደረሰባቸው ለሃገሪቱ ሚዲያ ገልጿል።
ከሲቲዝን ቴሌቪዥን ጋር ባደረገው ቆይታ ሳልቫዶር አጊና ጎረቤቶቹም ሆኑ የሚያውቃቸው ሰዎች እየደወሉ "መታመምህን እያወቅክ እንዴት ሰላምታ ትሰጠናለህ፤ መራቅ አለብህ" ይሉኛል።
ምንም እንኳን ባለቤቱም ሆነ ልጆቹ ተመርምረው ከቫይረሱ ነፃ መሆናቸው ቢረጋገጥም አንዳንድ ጎረቤቶቹ ልጆቹን ከልጆቻቸው ጋር እንዲጫወቱ ለምን እንደሚፈቅድላቸውና፤ ለምን ተገልለው እንደማይቀመጡ ይጠይቋቸዋል።
የኬንያ የጤና ሚኒስቴር የኮሮናቫይረስ ህመምተኞችንም ሆነ ያገገሙት መገለልና መድልዎ እንዳይደርስባቸው ለኬንያውያን በተደጋጋሚ ጥሪ በማቅረብ ላይ ነው።
በሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ የሚሰሩት ዶክተር ምዋንጋንጊ ከሰሞኑ ከሆስፒታል የወጡ ግለሰቦችን ማህበረሰቡ እንዲቀበላቸውና ወደ ቀድሞ ህይወታቸው እንዲመለሱ ማድረግ አለበትም ሲሉ መልእክታቸውን አስተላልፈዋል።
የጤና ሚኒስትሩ ሙታይ ካግዌም ከዚህ ቀደም በኮሮናቫይረስ የተያዙት የመጀመሪያዎቹ ኬንያውያን እንዴት እንዳገገሙ ታሪካቸውን መናገራቸውን ተከትሎ ውርጅብኝ ሲደርስባቸው ከጎናቸው በመቆም ደግፈዋቸዋል።
"ኮቪድ - 19 እየተዛመተ ስለመሆኑ የሚያሳይ ምልክት የለም " ዴንማርክ

የፎቶው ባለመብት, Reuters
የምስሉ መግለጫ, በዚህ ወር መጀመሪያ ላይ ዴንማርክ እስከ 11 ዓመት ላሉ ህጻናት ትምህርት ቤቶች እንዲከፈቱ ፈቅዳለች በዴንማርክ የእንቅስቃሴ ገደቡ ከተጣለ አንስቶ የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ እየተስፋፋ ባለመሆኑ በዚህ ወር መጀመሪያ ላይ የጣለቻቸውን ገደቦች አላልታለች፡፡
እንደ የወረርሽኝ መከላከል ዝግጁነት ተቋም ስቴት ሴረም ኢንስቲቲዩት መረጃ ከሆነ የቫይረሱ የስርጭት መጠን (R0) ከ1.0 በታች ነው፡፡ R0 አንድ በቫይረሱ የተያዘ ሰው በአማካይነት ሊያስከትላቸው የሚችሉ ኬዞች መጠን ማለት ነው፡፡
በዚህ ስሌት መሠረትም በዴንማርክ ከጎርጎሳውያኑ ሚያዝያ አጋማሽ ጀምሮ ቁጥሩ ጭማሬ ያሳየ ቢሆንም አሁን ግን ከ1.0 በታች ሆኗል፡፡
ቢሆንም ኮቪድ 19 እየተዛመተ ስለመሆኑ የሚያሳይ ምልክት የለም ብሏል ተቋሙ
በሌላ በኩል ጀርመን ወረርሽኙን ለመቆጣጠር የጣለቻቸውን ገደቦች ከባለፈው ሳምንት ጀምራ ማላላት ጀምራለች፡፡ የቫይረሱን የስርጭት መጠንም ከአንድ በታች ለማውረድ ትፈልጋለች፡፡
በጎርጎሳውያኑ መጋቢት መጀመሪያ አካባቢ ይህ መጠን 3 ነበር፤ ይሁን እንጅ በሚያዝያ አጋማሽ ላይ ከአንድ በታች ሆኖ ተመዝግቧል፡፡
ድጋሜ ከመቀነሱ በፊት ሰኞ እለት መጠኑ ከአንድ ከፍ ብሎ የነበረ ቢሆንም አሁን ላይ ያለው መጠን 0.76 ነው፡፡
