ፖምፔዎ ቫይረሱ ከቻይና ቤተ ሙከራ ስለመምጣቱ 'በርካታ ማስረጃዎች' አሉን አሉ
የኮሮናቫይረስን ለመከላከል ክትባትም ሆነ ለማከም የሚውል መድኃኒት እስካሁን አልተገኘም። ነገር ግን በየአገራቱ ያሉ ባለሙያዎች ሌት ተቀን ጥረት እያደረጉ መሆናቸው እየተነገረ ነው። መቼ ውጤት ላይ ሊደርሱ እንደሚችሉ ግን በእርግጠኝነት መናገር አይቻልም። ስለዚህ በእጃችን ላይ ያሉትን የመከላከያ መንገዶች በመጠቀም እራስን ከበሽታው መጠበቅ ብቸኛው መንገድ ነው። ለዚህ ደግሞ አካላዊ ርቀታችንን እንጠብቅ፤ እጃችንን በተደጋጋሚ በሳሙናና በውሃ እንታጠብ። ስለወረርሽኙ የሚቀርቡ የቀጥታ ዘገባዎችንና መረጃዎችን ከዚህ ገጽ ይከታተሉ።
የቀጥታ ሽፋን
የቻይናው ዜና ወኪል አሜሪካ ላይ የሚያሾፍ አኒሜሽን ፊልም ሠራ

የፎቶው ባለመብት, Xinhua News Agency
የቻይናና አሜሪካ ውዝግብ ወደ አኒሜሽን ፊልም ገብቷል።
የቻይናው ዜና ወኪል ዢንዋ ሌጎ የተሰኝውን አኒሜሽን ተጠቅሞ አሜሪካ ላይ የሚዘባበት ፊልም አሳይቷል።
የአሜሪካው ፕሬዝደንት ዶናልድ ትራምፕ የኮሮናቫይረስን በተመለከተ ቻይናን በተደጋጋሚ መውቀሳቸውን ተከትሎ ነው የዜና ወኪሉ ፖለቲካውን በአኒሜሽን ፊልም ያደራው።
ፊልሙ ሁለቱን ወገኖች በገፀ-ባሕርይ ስሎ ነው ያሳየው። አሜሪካ በነፃነት ሐውልት ስትወከል ቻይና ደግሞ በታሪካዊ አርበኛ ተወክላለች።
ገፀ-ባሕርያቱ በቃላት ጦርነት ውስጥ ሆነው ይታያሉ። በስተመጨረሻም የቻይናው አርበኛ ያሸንፋል።
ሌጎ የተሰኘው የአኒሜሽን ፊልም ድርጅት "እኔ የለሁበትም" የሚል መግለጫ ለቋል።
በቻይናና አሜሪካ መካከል ያለው ፍጥጫ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጦዘ መጥቷል። በተለይ ከኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ በኋላ ደግሞ ነገሮች እየከረሩ ነው።
የእንግሊዝ ፕሪሚዬር ሊግ በገለልተኛ ሜዳ ሊጠናቀቅ ይሆን?
ሰበር, በኢትዮጵያ ከ2 ሺህ በላይ የኮቪድ-19 ምርመራ ተደርጎ ሁሉም ነጻ ሆነው ተገኙ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ኢትዮጵያ በአንድ ቀን እስካሁን ካደረገችው የኮሮናቫይረስ ምርመራ ከፍተኛውን ቁጥር ባደረገችበት ፍተሻ ምንም በበሽታው የተያዘ ሰው አለመገኘቱ ተገለጸ።
የጤና ጥበቃ ሚኒስቴርና የማኅበረሰብ ጤና ተቋም በየዕለቱ በሚያወጡት ሪፖርት በዛሬው ላይ እንደተመለከተው እስከዛሬ ከተደረጉት የምርመራዎች ብዛት ከፍተኛው ቁጥር ተደርጓል።
በዚህም መሰረት 2016 ናሙናዎች ላይ የላብራቶሪ ምርመራ የተደረገ ሲሆን ሁሉም ነጻ ሆነው መገኘታቸው ሪፖርቱ አመልክቷል።
በተጨማሪም ቀደም ሲል ቫይረሱ ተገኝቶባቸው በለይቶ የህክምና መስጫ ማዕከል ህክምና ሲከታተሉ ከነበሩ ሰዎች መካከል ሦስቱ ከወረርሽኙ ማገገማቸውም ተጠቅሷል።
በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ በቫይረሱ ተይዘው በለይቶ ህክምና መስጫ ማዕከል ውስጥ የሚገኙት ሰዎች ቁጥር 59 ሲሆኑ ከመካከላቸውም በጽኑ የህክምና ክፍል የሚገኝ ታማሚ እንደሌለ ዕለታዊው መግለጫ አመልክቷል።
በአገሪቱ የመጀመሪያው በኮሮናቫይረስ የተያዘ ሰው መገኘቱ ከተገለጸ ሁለት ወራት ሊሆን እየተቃረበ ሲሆን በዚህ ጊዜ ውስጥ ወደ 20 ሺህ በሚጠጉ ሰዎች ላይ የኮቪድ-19 ምርመራ ተደርጓል።
ከተመረመሩት ውስጥም በበሽታው መያዛቸው የተረጋገጠው ሰዎች ቁጥር 133 ሲሆን ሦስት ሰዎች በወረርሽኙ ሳቢያ ህይወታቸው አልፏል።
ከኮሮናቫይረስ መከሰት በኋላ አመፅ በማያጣት ኤል-ሳልቫዶር ወንጀል ቀነሰ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ለወትሮው አመፅ የማያጣት ደቡብ አሜሪካዊቷ አገር በኤል-ሳልቫዶር በኮሮናቫይረስ ምክንያት ወንጀል እጅጉን ቀነሰ።
አገሪቱ ከዓለማች አመፅ ከማያጣቸው አገሮች ትመደብ የነበረ ቢሆንም አሁን ግን ወንጀል ቢያንስ በግማሽ ቀንሷል ይላል ከኤል-ሳልቫዶር የወጣ መረጃ።
በዚህ ዓመት በመጀመሪያዎቹ አራት ወራት ብቻ 441 ግድያዎች የተመዘገቡ ሲሆን ባለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ግን 1059 ግድያዎች ተመዝግበው ነበር።
ኤል-ሳልቫዶር የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝን ለመግታት በሚል ጥብቅ የሆነ ሕግ አውጃለች።
ፕሬዝደንት ናይብ ቡኬሌ ፀጥታ አስከባሪዎች ሕጉን እንዲያስከብሩ ሙሉ ስልጣን መስጠታቸው አይዘነጋም። በተለይ ደግሞ በለይቶ ማቆያዎች ውስጥ ያሉ ሰዎች እንቅስቃሴያቸው እንዲገታ አሳስበው ነበር።
ነገር ግን በርካታ ወጣት የአመፀኛ ቡድን አባላት ተጨናንቀው የታሠሩባቸው እስር ቤቶች ውስጥ ቫይረሱ ክፉኛ ይስፋፋል የሚል ስጋት አለ።
በናይጄሪያ የኮቪድ-19 መቆጣጠሪያ ኃላፊ በበሽታው መያዛቸው ተረጋገጠ

የምስሉ መግለጫ, ዶክተር ቦዋሌ አቢምቦላ በናይጄሪያ የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝን መቆጣጠር ዋነኛ ሥራው የሆነው ተቋም ኃላፊ በኮቪድ-19 መያዛቸው በምርመራ ተረጋገጠ።
ኃላፊው ዶክተር ቦዋሌ አቢምቦላ የካቲት ወር መጨረሻ ላይ በንግድ ከተማዋ ሌጎስ ውስጥ በሚገኘው ያባ የተላላፊ በሽታዎች ሆስፒታል ውስጥ በአገሪቱ የመጀመሪያዎቹ የቫይረሱ ታማሚዎች ተቀብለው አገልግሎት ከሰጡት ሐኪሞች መካከል አንዱ ናቸው።
ዶክተሩ ከማሳል ውጪ ያሉትን የበሽታውን ምልክቶች የማያሳዩ ሲሆን በአሁኑ ጊዜ ተለይተው ህክምና እየተደረገላቸው መሆኑ ተገልጿል።
ዶክትር ቦዋሌ በናይጄሪያ ውስጥ ከፊት መስመር ሆነው የኮሮናቫይረስ ህክምና በመስጠት ላይ እያሉ በኮሮናቫይረስ ተይዘው ከተገኙ 113 የጤና ባለሙያዎች መካከል አንዱ ሆነዋል።
የናይጄሪያ የበሽታ መቆጣጠሪያ ማዕከል እንዳለው በአገሪቱ ውስጥ ከ1932 በላይ በበሽታው የተያዙ ሰዎች ሲኖሩ ቢያንስ 50 ሰዎች ሞተዋል። 300 የሚደርሱት ደግሞ ከበሽታው አገግመዋል።
ቤልጂዬም ውስጥ በኮቪድ-19 ብዙዎች እየሞቱ ያሉት ለምንድነው?

የፎቶው ባለመብት, Reuters
ቤልጂዬም በኮሮናቫይረስ በዓለም እጅጉን ከተጠቁ አገራት አንዷ ናት።
ይህም የሆነው ቤልጂዬም ውስጥ እየተመዘገበ ያለው የሞት መጠን ከሕዝብ ቁጥሯ ጋር ሲሰላ ከፍተኛ በመሆኑ ነው።
እንዲያውም በቅርቡ ዶናልድ ትራምፕ ቤልጂዬምን እየጠቆሙ አገራቸው በሞት ደረጃ ሰባተኛ ደረጃ ላይ መቀመጧን ሲያሳዩ ነበር።
ቤልጂዬም 11.5 ሚሊዮን ሕዝብ አላት። ይህ ማለት ደግሞ ከእያንዳንዱ 100 ሺህ ሕዝብ 66 ሰዎች በኮሮናቫይረስ ምክንያት ሞተዋል ማለት ነው።
ዩናይትድ ስቴትስ ደግሞ 330 ሚሊዮን ሕዝብ ሲኖራት ከ100 ሺህ ሰዎች 19 ሰዎች በኮቪድ-19 ሕይወታቸውን አጥተዋል።
ቢሆንም ይህ ንፅፅር የሚያሳምን አይደለም የሚሉ በርካቶች ናቸው።
የቤልጂዬም ባለሥልጣናት ሌሎች አገራት ሆስፒታል ውስጥ ብቻ የሞቱትን ነው የሚመዝግቡት እኛ ግን በአረጋውያን መንከባከቢያ ውስጥ የሞቱትንም ጭምር እየመዘገብን ስለሆነ ነው ቁጥሩ የላቀው ይላሉ።
እንደ ቤልጂዬም ባለሥልጣናት ከሆነ ከ7 ሺህ 703 የተመዘገበ ሞት መካከል ከግማሽ በላይ [53 በመቶ] በአረጋውያን መንከባከቢያ ውስጥ የነበሩ ናቸው። ሌላው ቀርቶ በኮሮናቫይረስ ተጠርጥረው የሞቱትንም ጭምር ነው የመዘገብነው ባይ ናቸው።
ቤልጂዬም የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ መስፋፋትን ለመግታት እንቅስቃሴ ካገደች አንድ ወር አልፏታል።
ልጃቸውን አዝለው ስብሰባ የገቡት ወንድ ሚኒስትር

የፎቶው ባለመብት, AISSATOU BAH
የሴራሊዮን ትምህርት ሚኒስትር የሆኑት ዳቪድ ሞይኒና የ10 ወር ልጃቸውን አዝለው ስብሰባ ገብተዋል።
ሚኒስትሩ በኮሮናቫይረስ ምክንያት ከቤታቸው ሆነው ዙም በተሰኘው የቪድዮ መደዋወያ ቴክኖሎጂ በተሳተፉበት ስብሰባ ላይ ሴት ልጃቸውን በጨርቅ ጀርባቸው ላይ አዝለው ታይተዋል።
ሚኒስትሩ ይህን ያደረጉት ለሌሎች ወንዶች ምሳሌ ለመሆን አስበው እንደሆነ ለቢቢሲ ተናግረዋል።
የ33 ዓመቱ ሚኒስትር ሴት ሚኒስትር ልጇን አዝላ ብትታይ ኖሮ ዜና አይሆንም ነበር፤ ምክንያቱም ሁልጊዜ ስለምታደርገው። ይህ ፆታዊ ኢ-ፍትሃዊነት እንዳለ ማሳያ ነው ብለዋል።
ሚኒስትሩ 'በጎ ምሳሌ' የሚል ስያሜ ተሰጥቷቸዋል።
ሚኒስትሩ ሴት ልጃቸው ፒየኒናን ኩሽና ውስጥ ሆነው እየመገቡ ነበር ስብሰባ ሲሳተፉ የነበረው። ትንሽ ቆይቶ እንቅልፏ እንደመጣ ሲመለከቱ ነው በጀርባቸው ያዘሏት።
የሚኒስትሩን ፎቶ የተመለከቱ ወንዶች ልጆቻቸውን እያዘሉ የተነሱትን ፎቶ በማኅበራዊ መድረኮች ላይ እያጋሩ ነው።
የህሙማንን የመተንፈሻ መሳሪያ የምታቋርጠው ነርስ

የፎቶው ባለመብት, Juanita Nittla
እናም የመጨረሻዋ ደቂቃ ስትቃረብ፣ በማሽንም መተንፈስ ሲያዳግት፣ ማሽኑ ሊነቀል ግድ ይላል። ወደ ሞት እየሄዱ ላሉ ህሙማን ምን አይነት ስሜት ይኖረው ይሆን? ማሽኑን ለሚነቅሉት የጤና ባለሙያዎችስ?
በለንደን ሮያል ፍሪ ሆስፒታል በፅኑ ህሙማን ክፍል ውስጥ ለምትሰራው ዋና ነርስ ጁዋኒታ ኒትላ በአብዛኛው መተንፈሻ ማሽኖችን መንቀል የሥራዋ አንድ አካል ነው።
በብሔራዊ የጤና አገልግሎት በፅኑ ህሙማን ልዩ ነርስ በመሆንም ለአስራ ስድስት ዓመታት ያህል አገልግላለች። ነገር ግን ጊዜው ሥራውንም ሆነ የሚሰማትን ስሜት አላቀለለውም።
"ልብ የሚሰብር ነው፣ ህመሙም ጠልቆ ይሰማኛል" የምትለው የ42 ዓመቷ ጁዋኒታ "አንዳንድ ጊዜም ለእነዚህ ሰዎች ሞት ተጠያቂ ነኝ ብዬ አስባለሁ" ትላለች። ሙሉውን ታሪክ እዚህ ያንብቡ የሚሞቱ ህሙማንን የመጨረሻ ኑዛዜያቸውን የምትቀበለው ነርስ
ዶክተር ቴድሮስ ድርጅታቸው በኮሮናቫይረስ ዙሪያ የሚጠበቅበትን ማድረጉን ገለጹ

የፎቶው ባለመብት, Reuters
የዓለም ጤና ድርጅት የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ አያያዙ ላይ የቀረበበት ትችትን በመከላከል እርምጃ በመውሰድ በኩል ምንም ያባከነው ጊዜ እንደሌለ አሳወቀ።
የድርጅቱ ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ቴድሮስ አድኃኖም እንዳሉት፤ በሽታው ዓለም አቀፍ የጤና ስጋት እንደሆነ በጥር ወር መጨረሻ ላይ ይፋ መደረጉን በመጥቀስ “ይህም ዓለም በወረርሽኙ ዙሪያ አስፈላጊውን እርምጃ እንዲወስድ በቂ ጊዜ የሰጠ ነው” ብለዋል።
በዚያ ጊዜም ከቻይና ውጪ በኮሮናቫይረስ የተያዙ ሰዎች ቁጥር 82 ብቻ የነበሩ ሲሆን የሞተ ሰው አልነበረም።
ከሦስት ወራት በኋላ ዛሬ በዓለም ዙሪያ ከ3.2 ሚሊዮን በላይ ሰዎች በበሽታው የተያዙ ሲሆን 234 ሺህ ሰዎች ደግሞ ለሞት ተዳርገዋል።
በዓለም የጤና ድርጅት ላይ ተደጋጋሚ ትችት እያቀረቡ ያሉት የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ሲሆኑ ለቻይና ያደላል ሲሉም ይከሱታል።
በዚህም ሳቢያ ለድርጅቱ ከማንም በላይ ከፍተኛውን ገንዘብ የምትለግሰው አገራቸውም ስጦታዋን እንደምታቋርጥም ፕሬዝዳንቱ ማሳወቃቸው ይታወሳል።
ዶክተር ቴድሮስ አርብ ምሽት በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ ድርጅታቸው ከመነሻው ጀምሮ የሚጠበቅበትን ማከናወኑን በመግለጽ ለሚቀርቡ ትችቶች ምላሽ ሰጥተዋል፤ በተጨማሪም አሁንም በሽታው “የዓለም ኅብረተሰብ ጤና ስጋት” ሆኖ መቀጠሉን አመልክተዋል።
ዋና ዳይሬክተሩ ጨምረውም በአሁኑ ጊዜ ደካማ የጤና አገልግሎት ሥርዓት ባላቸው አገራት ውስጥ በሽታው እየጨመረ በመምጣቱ ሊያስከትለው የሚችለው ጉዳት “ክፉኛ እንደሚያሳስባቸው” ተናግረዋል።
"ስለምንወዳችሁ ሠርጋችን ላይ አትምጡ" የአዲስ አበባዎቹ ሙሽሮች
የኢቦላ መድኃኒት ኮሮናቫይረስን ለማከም እንዲውል ተፈቀደ

የፎቶው ባለመብት, Reuters
የአሜሪካ ምግብና መድኃኒት አስተዳደር ተቋም የቦላ በሽታን ለማከም የሚውለውን ሬምዴሲቪር የተባለውን መድኃኒት ለአስቸኳይ ጊዜ የኮሮናቫይረስ ህክምና እንዲውል ፈቀደ።
በዚህም መሰረት ይህ ጸረ ቫይረስ የሆነው ይህ መድኃኒት በኮሮናቫይረስ በጽኑ ታመው ሆስፒታል የሚገኙ ሰዎችን ለማከም ይውላል።
የአሜሪካ ምግብና መድኃኒት አስተዳደር ኮሚሽነር የሆኑት ስቴፈን ሃን እንዳሉት “ይህ የኮሮናቫይረስን ለማከም ዕውቅና የተሰጠው የመጀመሪያው መድኃኒት ነው” ብለዋል።
በቅርቡ ሬምዴሲቪርን በመጠቀም በተደረገ ሙከራ በኮሮናቫይረስ ክፉኛ ታመው ሆስፒታል የገቡ ሰዎች የሚያገግሙበትን ጊዜ ለማፋጠን እንዳስቻለ ተረጋግጧል።
ነገር ግን ይህ በተቋሙ መድኃኒቱን ለመጠቀም የተሰጠው የአስቸኳይ ጊዜ ፈቃድ ሙሉ ፈቃድ አለመሆኑ የተገለጸ ሲሆን፤ መደበኛ ዕውቅና ለማግኘት ከፍ ያለ ምዘናን ይጠይቃል።
ባለሙያዎች እንደሚሉት ይህ ኢቦላን ለማከም የተሰራው መድኃኒት ኮሮናቫይረስን እንደሚፈውስ ተአምረኛ መፍትሄ መወሰድ የለበትም።
ጊሌድ የተባለው የመድኃኒቱ አምራች ኩባንያ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ዋይት ሐውስ ውስጥ ከዶናልድ ትራምፕ ጋር በነበራቸው ውይይት እንዳሉት ለመድኃኒቱ የተሰጠው ፈቃድ ጠቃሚ እርምጃ መሆኑን አመልከተው፤ ከፍተኛ መጠን ያለው መድኃኒት ጥቅም ላይ እንዲውል እንደሚለግሱ አሳውቀዋል።
የቢቢሲ አማርኛ የሚያዝያ 24/2012 ዓ.ም የቀጥታ ዘገባ ገጽ
እንደምን አደራችሁ!
ዕለተ ቅዳሜ፤ ሚያዝያ 24/2012 ዓ.ም
ቢቢሲ አማርኛ፤ ቀኑ የሠላምና የጤና ይሆንላችሁ ዘንድ እንመኛለን።
በተለይ ደግሞ እራሳችንንና ሌሎችን ከወቅቱ አሳሳቢ ወረርሽኝ [ኮቪድ-19] በመጠበቅ መልካም ዕለት እንዲሆን የባለሙያዎችን ምክር ተግባራዊ እናድርግ።
ስለዚህም የግድ አስፈላጊ ለሆኑ ጉዳዮች ካልሆነ በስተቀር በቤታችን ውስጥ እንወሰን፤ በተጨማሪም የእጃችንን ንጽህና በአግባቡ እንጠብቅ። በየትኛውም ቦታ ላይና አጋጣሚ ከሰዎች ጋር የሚኖረ አካላዊ ቅርበት ከሁለት እርምጃዎች ያነሰ አይሁን።
መዘናጋት በተለያዩ አገራት ውስጥ እያስከፈለው ያለውን ውድ ዋጋ እየተመለከትን ባለበት በአሁኑ ወቅት የምንችለውን ሁሉ ጥንቃቄ በማድረግ ወረርሽኙን ለመከላከል እንጣር።
ይህ የቢቢሲ አማርኛ የቀጥታ ዘገባ ገጽ፤ ከኢትዮጵያና ከዓለም ዙሪያ ስለበሽታው በየደቂቃው የሚወጡ ዜናና መረጃዎችን ያቀርባል እናንተም ባገኛችሁት አጋጣሚ ሁሉ ይህንን ገጽ እንድትጎበኙ እንጋብዛለን።
መልካም ነገሮችን የምንሰማበት ዕለት ይሆን ዘንድ ምኞታችን ነው!

የአሜሪካ መንግሥት 100,000 ተጨማሪ የአስክሬን መጠቅለያ አዘዘ

የፎቶው ባለመብት, EPA
የአሜሪካ መንግሥት 100 ሺህ ተጨማሪ የአስክሬን መጠቅለያ ፕላስቲኮች ማዘዙን የአገሪቱ መገናኛ ብዙኃን ያገኙት የስምምነት ሰነድ ጠቁሟል።
በ5.1 ሚሊዮን ዶላር ወጪ፣ ካሊፎርንያ ውስጥ ለሚገኝ ‘ኢኤም ኦይል ትራንስፖርት’ ለሚባል አምራች ድርጅት ትዕዛዙ መተላለፉ ተገልጿል።
ትዕዛዙ የተሰጠው ባለፈው ወር በአገሪቱ የአደጋ ጊዜ መሥሪያ ቤት በኩል ነው።
የአምራች ድርጅቱ ቃል አቀባይ ከኤንቢሲ ጋር ባደረጉት ቆይታ “ይህ ሁሉ አስክሬን መጠቅለያ እንዳያስፈልግ እጸልያለሁ፤ ትዕዛዙን ይሰርዙታል ብዬም አስባለሁ” ብለዋል።
የአደጋ ጊዜ መሥሪያ ቤቱ ቃል አቀባይ “ወረርሽኙ ከመጣ ጀምሮ ለከፋ ነገር እየተዘጋጀን ነው” ሲሉ ለዋል ስትሪት ጆርናል ተናግረዋል።
ባለፈው ሰኞ ፕሬዚዳንት ትራምፕ ከፍተኛው የሟቾች ቁጥር ከ60,000 እስከ 70,000 ቢደርስ ነው ብለው ነበር። ነገር ግን አርብ የሟቾች ቁጥር 63,000 ደርሷል።
በፈረንሳይ በቫይረሱ የሞቱ ሰዎች ቁጥር 24ሺህ 594 ደረሰ

የፎቶው ባለመብት, EPA
በፈረንሳይ በሆስፒታሎችና የእንክብካቤ ማዕከላት በቫይረሱ የሞቱ ሰዎች ቁጥር በ218 ጨምሮ 24ሺህ 594 መድረሱን የአገሪቷ መንግሥት አስታወቀ፡፡
የሞት ቁጥሩ ከቀደመው ቀን ጋር ሲነጻጸር በመጠኑ ጭማሪ ያሳየ ቢሆንም በአንድ ቀን ውስጥ የሚሞቱ ሰዎች ቁጥር ግን ለላፉት ሁለት ሳምንታት ቀንሷል፡፡
ከአውሮፓ አገራት ፈረንሳይ ከጣሊያን፣ ዩናይትድ ኪንግደም እና ስፔን ቀጥላ ከፍተኛ የሞት ቁጥር የተመዘገበባት አገር ናት፡፡
ፈረንሳይ ከ10 ቀናት በኋላ የጣለቻቸውን ገደቦች ማላላት ትጀምራለች፤ በሕዝብ ትራንስፖርት እና በሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች የአፍና የአፍንጫ መሸፈኛ ማድረግ ግን ይሆናል፡፡
ዘንድሮ የኒው ዮርክ ትምህርት ቤቶች አይከፈቱም ተባለ
የኒው ዮርክ አገረ ገዢ አንድሩ ክዎሞ እስከ ዓመቱ መጨረሻ ድረስ ትምህርት ቤቶች እንደማይከፈቱ ገለጹ።
ኃላፊዎች፤ በምን መንገድ በየቀኑ 4.2 ሚሊዮን ተማሪዎች በሚመላለሱባቸው ትምህርት ቤቶች ማኅበራዊ ርቀት እንዲጠበቅ ማድረግ እንደሚቻል ለመማር ጊዜ የላቸውም ብለዋል።
“አንድ የአስር ዓመት ታዳጊ አካላዊ ርቀት እንዲጠብቅ የምናደርገው እንዴት ነው?” ሲሉ አገረ ገዢው ዛሬ በሰጡት መግለጫ ተናግረዋል።
የክረምት ትምህርት ቤቶችን በተመለከተ ደግሞ በወሩ መጨረሻ ውሳኔ ላይ እንደሚደርሱ አስታውቀዋል።
ባለፈው ወር የቤት ውስጥ ጥቃት 15 በመቶ እንደጨመረም አንድሩ ክዎሞ ተናግረዋል።
ኒው ዮርክ ውስጥ ባለፈው ማክሰኞ 289፣ ረቡዕ ደግሞ 306 ሰዎች በቫይረሱ ሞተዋል።
የዌልስ የእንክብካቤ ማዕከላት ሠራተኞች የገንዘብ ጉርሻ ሊሰጣቸው ነው

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የምስሉ መግለጫ, የዌልስ ቀዳማይ ሚኒስትር ማርክ ድራኬፎርድ ለዌልስ የእንክብካቤ ማዕከላት ሠራተኞች ለእያንዳንዳቸው 500 ፓውንድ የገንዘብ ጉርሻ እንደሚሰጣቸው ቀዳማይ ሚኒስትር ማርክ ድራኬፎርድ አስታወቁ፡፡
የገንዘብ ጉርሻው ከ64 ሺህ በላይ ለሆኑ ሠራተኞች የሚሰጥ ሲሆን 32.2 ሚሊየን ፓውንድ ያስወጣል፡፡
በዌልስ የእንክብካቤ ማዕከላት በቫይረሱ የሚሞቱ ሰዎች ቁጥር ጨምሯል፡፡ በፈረንጆቹ ሚያዚያ 17 የሟቾቹ ቁጥር 184 የነበረ ሲሆን፤ በዋና ከተማዋ ካርድፍ ውስጥ በኮቪድ-19 ከሞቱት 40 በመቶ የሚሆኑትን ይይዛል፡፡
ሚኒስትሩ በዌልስ በማዕከላቱ የሚኖሩም ሆነ የሚመላላሱ ሠራተኞች ከፍተኛውን አደጋ ለመጋፈጥ ፈቃደኛ በመሆናቸው ጉርሻው ለዚህ ተግባራቸው እውቅና ለመስጠት የተዘጋጀ ነው ብለዋል፡፡
ሠራተኞቹ ዝቅተኛ ክፍያ እንደነበራቸው ያስታወሱት ሚኒስትሩ ከገንዘብ ጉርሻው ላይ ግብር እንዳይቆርጥባቸውና ጥቅማቸውን እንዳይቀንስባቸው ለዩናይትድ ኪንግደም መንግሥት ጥሪ አቅርበዋል፡፡
ቤተ ክርስቲያኗ ሀኪሞችን ቅዱሳን የሚያስመስሉ ሥዕሎችን ኮነነች

የፎቶው ባለመብት, Reuters
ሀኪሞችን ቅዱሳን የሚያስመስሉ ሥዕሎች ክብረ ነክ ናቸው ስትል የሮማንያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን አወገዘች።
ሀኪሞች እንደ ቅዱሳን በብርሀን ተከበው የሚያሳዩ ፖስተሮችን ያዘጋጀው ድርጅት፤ ኮሮናቫይረስን እየተዋጉ ያሉ የህክምና ባለሙያዎችን ለማመስገን እንጂ ማንንም ለማስቀየም አስቤ አልነበረም ብሏል።
የቤተክርስቲያኒቷ ቃል አቀባይ በበኩላቸው ሥዕሎቹ ክርስትናን የሚጻረሩ ናቸው ብለዋል።
አዘጋጁ ‘መክን’ የተባለው ድርጅት ደግሞ የጤና ባለሙያዎችን ለማሞገስ የመረጥኩት ጥበባዊ መንገድ ነው ይላል።
የሮማንያ መዲና አስተዳደር ፖስተሮቹ በሌላ ምስል እንዲለወጡ አደርጋለሁ ብሏል።
በሮማንያ 12,000 ሰዎች በኮሮናቫይረስ ተይዘው ከ700 በላይ ሕይወታቸውን አጥተዋል።
በዚምባብዌ በቫይረሱ ምክንያት በርካታ ታራሚዎች ከእስር ተፈቱ
ዚምባብዌ በኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ምክንያት ለበርካታ ታራሚዎች ምሕረት አድርጋለች፡፡
መንግሥት እንዳስታወቀው በይቅርታው የእድሜ ልክ እስራት የተፈረደባቸውና 20 ዓመታትን በእስር ያሳለፉ ታራሚዎች ከእስር ይለቀቃሉ፡፡
ይቅርታው በወንጀል የተከሰሱ ሴቶች በሙሉ ከእስር እንዲለቀቁ ያደረገ ሲሆን፤ አፍላ ወጣቶች እና የታመሙ ሰዎችም እንደሚለቀቁ ተነግሯል፡፡
በትንሹ ከተፈረደባቸው የሦስት ዓመት እስራት ጊዜ አንድ ሶስተኛውን ያጠናቀቁ ወንዶችም እንዲሁ ይለቀቃሉ ተብሏል፡፡
በዚምባብዌ በፈረንጆቹ መጋቢት ወር 1ሺህ 500 የሚሆኑ ታራሚዎች የተለቀቁ ቢሆንም በተቀሩት 20 ሺህ ታራሚዎች እስር ቤቶቹ እንደተጨናነቁ ናቸው፡፡ እስር ቤቶቹ የመያዝ አቅማቸው 17 ሺህ ብቻ ነው፡፡
በዚህም ምክንያት አገሪቷ በአንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ የእስር ቤቶችን መጨናነቅ ለመቀነስ ለበርካታ እስረኞች ይቅርታ ብታደርግም አሁንም ያው ናቸው፡፡
እንደ ባለሥልጣናት መረጃ ከሆነ በአገሪቷ የቫይረሱ ስርጭት አነስተኛ ቢሆንም ቁጥሩ ከጨመረ ግን ያሉት የጤና ተቋማት ማስተናገድ አይችሉም የሚል ስጋት አለ፡፡
ኮቪድ-19፡ ዓለም እንዴት ዋለች?

የፎቶው ባለመብት, PA Media
ኮሮናቫይረስ ዓለምን እንዳልነበረች ካደረገ ወራት ተቆጥረዋል። የቫይረሱ ስርጭት ምጣኔ ሀብትን ጨምሮ በበርካታ ዘርፎች ላይም ተጽዕኖ እያሳደረ ይገኛል።
የተባበሩት መንግሥታት እንደሚለው፤ በቫይረሱ ሳቢያ በረራ በመቆሙ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ሕጻናት ሕይወታቸውን የሚታደግ ክትባት ላያገኙ ይችላሉ።
በሌላ በኩል የዛሬውን የላብ አደሮች ቀን በማስመልከት የተካሄዱ ሰልፎች አካላዊ ርቀትን በመጠበቅ ነው የተከናወኑት።
በአውስትራሊያ በቫይረሱ የሚያዙ ሰዎች ቁጥር መቀነሱን ተከትሎ እንቅስቃሴ እየተጀመረ ነው። በተቃራኒው ሕንድ እንቅስቃሴ ላይ ጥላ የነበረውን ገደብ በሁለት ሳምንት አራዝማለች።
የአሜሪካው ፕሬዘዳንት ዶናልድ ትራምፕ ለወረርሽኙ ተጠያቂ ያደረጓት ቻይናን ‘የእጅሽን ታገኛለሽ’ እያሉ እያስፈራሩ ነው።
በአገሪቱ 30 ሚሊዮን ሰዎች ሥራ አጥ ሲሆኑ፤ አስር ግዛቶች የእንቅስቃሴ ገደባቸውን እያነሱ ይገኛሉ።
በሌላ በኩል የዩናይትድ ኪንግደም ጠቅላይ ሚንስትር ቦሪስ ጆንሰን፤ አገራቸው ከፍተኛውን የበሽታ ስርጭት ወቅት ማለፏን ተናግረዋል። በሚቀጥለው ሳምንት የእንቅስቃሴ ገደብ የሚነሳበትን እቅድ አሳውቃለሁም ብለዋል።
በቀን 100,000 ሰው የመመርመር እቅዳቸውን ሊያሳኩ እንደሆነም አክለዋል።
በጆንስ ሆፕኪንስ መረጃ መሰረት፤ በመላው ዓለም ከአንድ ሚሊዮን በላይ ሰዎች ከበሽታው አገግመዋል።
