በሩሲያ ለሁለተኛ ቀን ከ10ሺህ በላይ ሰዎች በቫይረሱ መያዛቸው ተረጋገጠ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
በሩሲያ ተጨማሪ 10ሺህ 581 ሰዎች በቫይረሱ መያዛቸው መረጋገጡን የአገሪቷ ባለሥልጣናት አስታወቁ፡፡ ይህም አጠቃላይ በቫይረሱ የተያዙ ሰዎችን ቁጥር 145ሺህ 268 አድርሶታል፡፡
አገሪቷ ከ10ሺህ ሰዎች በላይ በቫይረሱ መያዛቸውን ስታረጋግጥ ይህ ሁለተኛ ቀኗ ነው፡፡ በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች ቁጥርም ከቻይና፣ ቱርክ እና ኢራን በልጧል፡፡
ባለፈው ሳምንት ጠቅላይ ሚኒስትር ሚካሃይል ሚሽስቲን በኮሮናቫይረስ መያዛቸው ተረጋግጧል፡፡
ይህንንም ተከትሎ ፕሬዚደንት ፑቲን በአገር አቀፍ ደረጃ ሥራ ዝግ ሆኖ የሚቆይበትን ጊዜ እስከ ፈረንጆቹ ግንቦት 11 ድረስ አራዝመዋል፡፡ በዋና መዲናዋ ሞስኮም የእንቅስቃሴ ገደቡ ባለበት ይቆያል ብለዋል፡፡
ባለሥልጣናት ሕዝቡ በየቤቱ እንዲቀመጥ እያሳሰቡ ነው፡፡ በሩሲያ በተያዘው ወር የሚከበሩ ሕዝባዊ በዓላትን ለማክበርም የተጣሉትን የእንቅስቃሴ ገደቦች ለመጣስ መሞከርም እንደማይቻል ባለሥልጣናቱ አስጠንቅቀዋል፡፡













