
የፎቶው ባለመብት, EPA
የዩናይትድ ኪንግደም ጠቅላይ ሚኒስትር ቦሪስ ጆንሰን በኮሮናቫይረስ በጠና
ታመው በነበሩበት ወቅት በሆስፒታል ስለተደረገላቸውን ህክምና ተናገሩ፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ዘ ሰን ጋዜጣ ጋር እሁድ ዕለት ባደረጉት ቃለምልልስ ሕይወታቸውን ለማትረፍ "በርካታ
ሊትር ኦክስጅን እወስድ ነበር" ብለዋል፡፡
ቦሪስ በለንደን ቅዱስ ቶማስ ሆስፒታል
ያሳለፉት አንድ ሳምንት ጊዜ ሌሎች በዚህ ወረርሽኝ እንዳይሰቃዩ ወረርሽኙን መግታት እና አገራቸው ቀድማ
ወደነበረችበት ሁኔታ እንድትመለስ የማድረግ ፍላጎት አሳድሮባቸዋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከጋዜጣው
ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ፤ "በጣም አስቸጋሪ ጊዜ ነበር፤ ልክድ አልፈልግም!" ሲሉ እንዴት ከሆስፒታል እንደሚወጡ
ራሳቸውን ሲጠይቁ እንደነበር አስታውሰዋል፡፡
ቦሪስ ቫይረሱ እንደተገኘባቸው የተረጋገጠው በጎርጎሮሳዊያኑ መጋቢት 26 ሲሆን ከአስር ቀናት በኋላ ሆስፒታል እንዲገቡ
ተደርገዋል፡፡ ከዚያም ወደ ጽኑ ሕሙማን ክፍል ያመሩት በሁለተኛው ቀን ነበር፡፡
"በጥቂት
ቀናት ውስጥ ጤንነቴ በዚህ ደረጃ መቃወሱን ለማመን አስቸጋሪ ነበር" ብለዋል ቦሪስ በቃለ ምልልሳቸው፡፡
ዶክተሮቹም
የከፋ ነገር ከመጣ ማድረግ ስላለባቸው ነገር ከፍተኛ ዝግጁነት ነበራቸው ብለዋል፡፡
ቦሪስ
በርካቶች በበሽታው እየተሰቃዩ እንደነበር ገልጸው፤ "በመዳኔ እድለኛ እንደሆንኩ ነበር የተሰማኝ" ይላሉ፡ ይህም የሌሎችን ስቃይ ለማቆም
ከፍተኛ ፍላጎት እንዳሳደረባቸው ገልጸዋል፡፡
"አገራችንን ቀድሞ ወደነበረችበት ሁኔታ፣
ጤና ለመመለስ ፍላጎት አሳድሮብኛል፤ በእርግጥም እዚያ እንደምንደርስ እርግጠኛ ነኝ" ብለዋል ቦሪስ፡፡
ቦሪስ ጆንሰን ከበሽታው ድነው ወደ ሥራ የተመለሱት ባለፈው ዕሁድ ሲሆን ባሳለፍነው ሳምንትም የወንድ ልጅ አባት ሆነዋል፡፡
እጮኛቸው ካሬ ሲመንድስ አዲስ የተወለደው ልጃቸው ዊልፍሬድ ላውሬ ኒኮላስ ጆንሰን እንደተባለ አስታውቀው ነበር፡፡
የልጃቸው ስምም ለአያቶቻቸው እና ቦሪስን ላከሟቸው ለሁለት ዶክተሮች ማስታወሻነት እንዲሆን የተሰየመ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡
ሲሞንድ በኢንስታግራም ገጻቸው ላይ ባሰፈሩት ጽሁፍ ልጃቸው የተወለደው ቦሪስ የኮሮና ሕክምናቸውን አጠናቀው ከሆስፒታል ከወጡ ከሳምንታት በኋላ ነበር፡፡
በዩናይትድ ኪንግደም
እስካሁን 183ሺህ 500 ሰዎች በቫይረሱ መያዛቸው የተረጋገጠ ሲሆን 28ሺህ 131 ሰዎች ሕይወታቸው ማለፉን የጆንስ ሆፕኪንስ
መረጃ ያሳያል፡፡