ፖምፔዎ ቫይረሱ ከቻይና ቤተ ሙከራ ስለመምጣቱ 'በርካታ ማስረጃዎች' አሉን አሉ

የኮሮናቫይረስን ለመከላከል ክትባትም ሆነ ለማከም የሚውል መድኃኒት እስካሁን አልተገኘም። ነገር ግን በየአገራቱ ያሉ ባለሙያዎች ሌት ተቀን ጥረት እያደረጉ መሆናቸው እየተነገረ ነው። መቼ ውጤት ላይ ሊደርሱ እንደሚችሉ ግን በእርግጠኝነት መናገር አይቻልም። ስለዚህ በእጃችን ላይ ያሉትን የመከላከያ መንገዶች በመጠቀም እራስን ከበሽታው መጠበቅ ብቸኛው መንገድ ነው። ለዚህ ደግሞ አካላዊ ርቀታችንን እንጠብቅ፤ እጃችንን በተደጋጋሚ በሳሙናና በውሃ እንታጠብ። ስለወረርሽኙ የሚቀርቡ የቀጥታ ዘገባዎችንና መረጃዎችን ከዚህ ገጽ ይከታተሉ።

የቀጥታ ሽፋን

  1. በየደቂቃው በኮሮናቫይረስ የሚያዙና የሚሞቱ ሰዎች ቁጥርን የሚያሳይ ካርታ

  2. በስዊድን የእንክብካቤ ማዕከላት የሟቾች ቁጥር እንዳይጨምር ተሰግቷል

    አንዲት አዛውንት ከእንክብካቤ ማዕከል ደጅ ላይ በዊልቸር ተቀምጣ

    የፎቶው ባለመብት, Getty Images

    በስዊድን በጎረቤት ኖርዲክ ከተመዘገበው በሦስት እጥፍ የሚበልጥ የሞት ቁጥር ተመዝግቧል፡፡

    የአገሪቷ የህብረተሰብ ጤና ኢንስቲቲዩት ኤጀንሲ ቫይረሱ በእንክብካቤ ማዕከላት በፍጥነት እንዴት እንደተሰራጨ ተናግሯል፡፡

    የወረርሽኙ ማዕከል በሆነችው ስቶክሆልም ከ400 የአረጋዊያን ማዕከላት ውስጥ 212 በሚሆኑት ኮቪድ -19 እንደተገኘ ኤጀንሲው ያስታወቀው ሰኞ ዕለት ነበር፡፡

    በስቶክሆልም እና ሶርምላንድ በሚገኙ የእንክብካቤ ማዕከላት ሥራ አስኪያጆች ጋር በኦንላይን የዳሰሳ ጥናት የተደረገ ሲሆን ጥናቱ በማዕከላቱ ሰራተኞችና በነዋሪዎቹ መካከል ርቀትን መጠበቅ አስቸጋሪ እንደሆነ አሳይቷል፡፡

    በስቶክሆልም የተላላፊ በሽታዎች ዶክተር የሆኑት ፔር ፎሊን በበኩላቸው የንጽሕና አጠባበቅ ደንቦችን እንዲሁም ሰራተኞችና ነዋሪዎቹ እንዴት መገናኘት እንዳለባቸው ጥናቱ ካሳየ አንስቶ በጣም በፍጥነት ብዙ ነገር ተሰርቷል ብለዋል፡፡

    በአገሪቷ የእንክብካቤ ማዕከላትን መጎብኘት የተከለከለውም ከፈረንጆቹ ሚያዚያ 1 ጀምሮ ነው፡፡

    በስዊድን 2ሺህ 769 ሰዎች በቫይረሱ ሕይወታቸው አልፏል፡፡ አገሪቷ ቫይረሱን ለመከላከል ጥብቅ ውሳኔዎችን ካሳለፉት ዴንማርክ፣ ኖርዌይ እና ፊንላንድ ጋር ሲነጻጸር ቫይረሱን ለመቆጣጠር በፈቃደኝነት አካላዊ ርቀትን መጠበቅ ላይ ትኩረት ማድረጓ ተገልጿል፡፡

  3. በአፍጋኒስታን ዋና ከተማ በድንገት ከተመረመሩ ሰዎች ሲሶው ቫይረሱ ተገኘባቸው

    የአፍጋን መንግሥት የእህል ርዳታ ለሚያስፈልጋቸው በነፃ ዳቦ እየሰጠ ነው

    የፎቶው ባለመብት, EPA

    በአፍጋኒስታን በኮቪድ-19 የተያዙ ሰዎች ቁጥር በይፋ ከተነገረው በላይ ሊሆን እንደሚችል ተገለፀ።

    ይህ ሊባል የቻለው በአፍጋኒስታን ዋና ከተማ ካቡል በድንገት ምርመራ ከተደረገላቸው ሰዎች መካከል አንድ ሶስተኛው በቫይረሱ ተይዘው በመገኘታቸው ነው።

    ሰኞ ዕለት በአፍጋኒስታን በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች ቁጥር 2894 የደረሰ ሲሆን 90 ሰዎች ደግሞ መሞታቸው ታውቋል።

    በአፍጋኒስታን የኮቪድ-19 ምርመራ የሚደረግላቸው ሰዎች ቁጥር አነስተኛ ሲሆን ጤና ስርዓቱም አስርታትን ባስቆጠረው የእርስ በእርስ ግጭት የተነሳ እጅጉን ተጎድቷል።

    ባለፈው መጋቢት ወር በቫይረሱ እጅጉን ከተጎዳችው ኢራን 1500 አፍጋናውያን የተመለሱ ሲሆን በአስር ሺዎች ደግሞ የሚቆጠሩ ከፓኪስታን መምጣታቸው ተሰምቷል።

    ይህ ደግሞ ቫይረሱን በአገር ውስጥ እንዲሰራጭ በር ይከፍታል ተብሎ ተሰግቷል።

    ባለፈው ወር ከአስር በላይ የፕሬዝዳንቱ ቤተ-መንግሥት ሰራተኞች በቫይረሱ መያዛቸው ተገልጾ ነበር።

  4. የሴይንት ፒትስበርግ የሕክምና ባለሙያዎች ካሳ ከመቀበላቸው በፊት ጉዳያቸው ይጣራል ተባለ

    የጤና ባለሙያዎች የፊት መከላከያ ለብሰው

    የፎቶው ባለመብት, Getty Images

    በሴይንት ፒተስበርግ የሚገኙ የጤና ባለሙያዎች በኮቪድ-19 ከታመሙ ካሳ እንደሚከፈላቸው ቢገለፅም ከክፍያው በፊት ግን እንዴት እንደተያዙ ምርመራ ይካሄዳል ተባለ።

    የከተማዋ አስተዳደር የጤና ባለሙያዎቹ የኮቪድ-19 ሕሙማንን ሲያክሙ በቫይረሱ ቢያዙ 300 ሺህ ሩብል (3800 ዶላር ገደማ) ለመክፈል ቃል ገብቷል።

    ባለፈው ሳምንት የሴይንት ፒተስበርግ የጤና ኮሚቴ ልዩ ኮሚሽን እንደሚቋቋምና የጤና ሰራተኞቹ ለካሳው ብቁ መሆን አለመሆናቸውን ይገመግማል ብለው ነበር።

    እንደ ሞስኮ ታይምስ ዘገባ ከሆነ ኮሚሽኑ ሠራተኞች በቫይረሱ ለመያዝ ምን ያህል ስህተት እንደሰሩ በመቶኛ ያስቀምጣሉ።

    ባለፈው ሳምንት ፕሬዝዳንት ፑቲን የኮሮናቫይረስ ሕሙማንን የሚያክሙ ባለሙያዎች የመከላከያ አልባሳትና ቁሳቁስ እጥረት እንዳለባቸው ተናግረው ነበር።

    ሩሲያ በተከታታይ ለሁለት ቀናት ከ10ሺህ በላይ ሰዎችን በቫይረሱ መያዛቸውን የመዘገበች ሲሆን ይህም አጠቃላይ በአገሪቱ በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች ቁጥርን 145,268 አድርሶታል።

  5. የአሜሪካው ምክትል ፕሬዝዳንት "ጭምብል ማድረግ ነበረብኝ" አሉ

    ማይክ ፔንስ

    የአሜሪካ ምክትል ፕሬዝዳንት ማይክ ፔንስ ባለፈው ሳምንት የኮቪድ-19 ሕሙማንን የሚያክም ሆስፒታል በጎበኙበት ወቅት የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ ማድረግ እንደነበረባቸው ተናገሩ።

    ማይክ ፔንስ የጎበኙት ሆስፒታል ማዮ ክሊኒክ በሚኒሶታ የሚገኝ ሲሆን የኮቪድ-19 ሕሙማንና ሕክምና ባለሙያዎችን በሚያነጋግሩበት ወቅት የአፍና የአፍንጫ መሸፈኛ ሳያደርጉ የሚታዩት እርሳቸው ብቻ ነበሩ።

    ይህንን የምክትል ፕሬዝዳንቱን ግዴለሽነት የሚያሳየው ቪዲዮ በማህበራዊ ሚዲያ ከተሰራጨ በኋላ ከፍተኛ ትችት ተሰንዝሮባቸዋል።

    "አስፈላጊ ነው ብዬ አላሰብኩም ነበር። ነገር ግን በማዮ ክሊኒክ በነበረኝ ጉብኝት ላይ የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ ማድረግ ነበረብኝ፤ በርግጥ በኢንዲያና የቬንትሌተር ማምረቻን ስጎበኝ አድርጌያለሁ" ብለዋል ለፎክስ ኒውስ።

    ምንም እንኳ ሆስፒታሉ የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ ማድረግን እንደ ግዴታ ቢያስቀምጥም ምክትል ፕሬዝዳንቱ ግን በየወቅቱ የኮሮናቫይረስ ምርመራ እንደሚደረግላቸው በመግለፅ አሻፈረኝ ማለታቸው ተሰምቶ ነበር።

    ክሊኒኩ ከምክትል ፕሬዝዳንቱ ጉብኝት በኋላ ሁሉም ጎብኚዎች የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ እንዲያደርጉ መጠየቁን በትዊተር ገፁ ላይ ጽፎ የነበረ ቢሆንም በኋላ ላይ አጥፍቶታል።

  6. አገራት ማዳጋስካር ሰራሁት ያለችውን 'የኮሮና መድኃኒት' ለማስገባት እያዘዙ ነው

    'መድሃኒቱ' በጠርሙሶች

    የፎቶው ባለመብት, AFP

    በማዳጋስካሩ ፕሬዚደንት አንድሪ ራጆሊና የተዋወቀው እና 'የኮሮናቫይረስ ፈውስ ነው' ለተባለው ባህላዊ መድኃኒት ከሰሃራ በታች ያሉ አገራት ያላቸው ፍላጎት እየጨመረ ነው፡፡

    'ባህላዊ መድኃኒቱ' ከኮሮናቫይረስ እንደሚያድን የሚያረጋግጥ ሳይንሳዊ መረጃ እንደሌለ ቢነገርም ፍላጎታቸው አልተገታም፡፡

    'መድኃኒቱን' ካዘዙት መካከልም መድኃኒቱን ለማምጣት ወደ ደሴቷ አገር አውሮፕላን የላኩት የታንዛኒያው ፕሬዚደንት ጆን ማጉፋሊ ይገኙበታል፡፡

    ከዚህም በተጨማሪ ኮንጎ ብራዛቪል፣ ኮንጎ ፣ ጋቦን እና ኮሞሮስ መድሃኒቱን ወደ አገራቸው የማስገባት ፍላጎት እንዳላቸው አስታውቀዋል፡፡

    ኢኳቶሪያን ጊኒ እና ጊኒ ቢሳዎም የተወሰኑ መድኃኒቶችን ለማምጣት አውሮፕላን ልከዋል፡፡

    ባለፈው ሳምንት የማዳጋስካሩ ፕሬዚደንት አንድሪ ለምዕራብ አፍሪካ አገራት የኢኮኖሚ ህብረት (ኢኮዋስ) 15 አባላት 'መድሃኒቱ'ን በጠርሙሶች የለገሱበት ዝግጅት አካሂደዋል፡፡

    ይሁን እንጅ አሁንም የዓለም ጤና ድርጅት ለኮሮናቫይረስ በግል የሚዘጋጅ ባህላዊ መድኃኒት ከኮቪድ -19 ሊያድን እንደሚችል የሚያረጋግጥ ሳይንሳዊ መረጃ አለመኖሩን በመግለጽ እያስጠነቀቀ ነው፡፡

  7. በጣሊያን በኮቪድ-19 የሞቱት ሰዎች ቁጥር ከተመዘገበው በላይ ሊሆን ይችላል ተባለ

    ጣሊያን

    የፎቶው ባለመብት, Getty Images

    በጣሊያን የተደረገ ጥናት በኮቪድ-19 መሞታቸው የተመዘገቡ ሰዎች ቁጥር ከተባለው በላይ ሊሆን እንደሚችል አስታወቀ።

    የጣሊያን ብሄራዊ ስታትስቲክስ ተቋም ያካሄደው ጥናት እንደሚያሳየው የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ በርካቶችን ሕይወት በነጠቀበት ጊዜያት የነበሩ በሺዎች የሚቆጠሩ ሞቶች በኮሮና ምክንያት መሆናቸው ባይገለፅም ነገር ግን ከኮቪድ-19 ጋር ሊያያዙ ይችላሉ ተብሏል።

    በጣሊያን በኮሮና ምክንያት የተመዘገበው ሞት 28,884 ነው የተባለ ሲሆን ይህም ከአሜሪካ ቀጥሎ በዓለማችን ላይ ሁለተኛው ከፍተኛው የሞት ቁጥር ነው።

    በጣሊያን የመጀመሪያው ከኮሮናቫይረስ ጋር የተያያዘ ሞት ከተመዘገበበት ወቅት ጀምሮ የነበሩ የ11 ሺህ 600 ሰዎች ሞት መንስዔው ኮሮና መሆን አለመሆኑ አለመመዝገቡን ጥናቱ ያሳያል።

    ተቋሙ አክሎም እነዚህ ግለሰቦች ሳይመረመሩ በኮቪድ-19 ሞተው ሊሆን፣ አልያም የጤና ስርዓቱ በነበረበት ከፍተኛ ጫና ሰበብ በሌላ ሕመም ቢታመሙም ተገቢውን አገልግሎት ሳያገኙ ቀርተው ሞተው ሊሆን ይችላል ብሏል።

  8. የኮቪድ-19ን ክትባት ለማግኘትና ለማሰራጨት ከተለገሰው አምስት እጥፍ ገንዘብ ይጠይቃል- የተባበሩት መንግሥታት

    የተባበሩት መንግሥታት ዋና ፀኃፊ አንቶኒዮ ጉታሬዝ

    የፎቶው ባለመብት, Getty Images

    የተባበሩት መንግሥታት ዋና ፀኃፊ አንቶኒዮ ጉታሬዝ ኮሮናቫይረስን ለመዋጋትና ለመከላከል እንዲሁም ክትባት፣ መድሃኒት ለመስራትና ለማሰራጨት የሚደረግ ዓለም አቀፍ ጥረትን ለመደገፍ አገራት ገንዘብ እንዲለግሱ ጥሪ አቀረቡ።

    የዓለም አቀፍ መንግሥታት ዛሬ በነበራቸው ስብሰባ ላይ 8.2 ቢሊየን ዶላር ለመሰብሰብ የታቀደ መሆኑ ታውቋል።

    ለጉባዔው ታዳሚዎች በቪዲዮ ባስተላለፉት መልዕክት የሚደረገውን ልግሥና አበረታተው፤ መከላከያ ክትባቱን መድሃኒት ለማግኘት፣ እንዲሁም አስፈላጊ ቁሳቁሶችን በዓለም ላይ በእኩል ለማዳረስ ከዚህ አምስት እጥፍ የሆነ ገንዘብ እንደሚያስፈለግ ገልፀዋል።

    አክለውም "ሁሉም አጋሮች በዚህ ጉዳይ ላይ እንዲተባበሩ ጥሪ አቀርባለሁ" ብለዋል ዋና ፀኃፊው።

    እስካሁን ድረስ ገንዘብ ለማዋጣት ቃል የገቡት አገራት፣ ብሪታንያ፣ ኖርዌይ፣ ጃፓን፣ ካናዳ እና ሳዑዲ አረቢያ ሲሆኑ አሜሪካ ግን አልተሳተፈችም።

    ጉታሬዝ ከቢቢሲ ጋር በነበራቸው ቆይታ የዓለም መንግሥታትን የተቹ ሲሆን " ደንግጫለሁ ግን አልተደነቅኩም" በማለት የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝን ለመመከት የተባበረ ዓለም አቀፍ አመራር መታጣቱን ተናግረው ነበር።

  9. በሞቃዲሾ ባለፉት ሁለት ሳምንታት ብቻ ከ500 በላይ ሰዎች መሞታቸው ተመዝግቧል

    በሶማሊያ የጤና ባለሙያዎችና የኃይማኖት አባቶች ስለኮሮና መከላከል ሲያስተምሩ

    የፎቶው ባለመብት, Getty Images

    የሱማሊያ ዋና ከተማ ሞቃዲሾ ከንቲባ ከተማቸው ውስጥ ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ ባልተለመደ ሁኔታ በርካታ ሞት መመዝገቡን በመጥቀስ የኮሮናቫይረስ በአገሪቱ በከፍተኛ ሁኔታ እየጨመረ እንደሆነ በመግለፅ ነዋሪዎችን አስጠነቀቁ።

    በሁለት ሳምንት ብቻ በአገሪቱ በኮሮናቫይረስ የተያዙ ሰዎች ቁጥር በሦስት እጥፍ የጨመረ ሲሆን በእያንዳንዱ ግዛትም በቫይረሱ የተያዘ ሰው ተገኝቷል።

    በሶማሊያ 722 ሰዎች በቫይረሱ ሲያዙ 32 ሰዎች ደግሞ በቫይረሱ ምክንያት መሞታቸውን የፌደራል መንግሥቱ መዝግቧል።

    ከንቲባው፣ ኦማር ፊሊሽ ግን በሳምንቱ መጨረሻ ላይ በነበራቸው የጋዜጣዊ መግለጫ ላይ ባለፉት ሁለት ሳምንታት ብቻ የከተማዋ የጤና ባለስልጣናት ከ500 በላይ ሞቶች መመዝገባቸውን ተናግረዋል።

    እኤአ ከሚያዚያ 19 ጀምሮ የከተማው አስተዳደር በቀን ከ17 ሰው እስከ 49 ሰው ድረስ መሞቱን መዝግቧል።

    አስተዳደሩ በሚያዝያ ወር መጀመሪያ ላይ በሶማሊያ በርካታ ያልተመረመሩ ከኮሮናቫይረስ ጋር የሚያያዙ ሞቶች ሊኖሩ እንደሚችሉ አስጠንቅቆ ነበር።

    የከተማዋ የጤና ባለሙያዎች ከከንቲባው ሃሳብ ጋር የሚስማሙ ይመስላሉ።

    የሆስፒታል ሠራተኞች የሕሙማን ቁጥር መጨመሩን ሲናገሩ፣ የመቃብር ቆፋሪዎች በበኩላቸው ባልተለመደ መልኩ በርካታ ሰዎች መሞታቸውንና መቀበራቸውን አረጋገግጠዋል።

  10. በሜክሲኮ የአደንዛዥ ዕፅ አዘዋዋሪዎች አለቃ ቤት ለጨረታ ቀረበ

    በሜክሲኮ የአደንዛዥ ዕፅ አዘዋዋሪዎች አለቃ መኖሪያ ቤት

    የፎቶው ባለመብት, Indep

    የሜክሲኮ መንግሥት የአደንዛዥ ዕፅ አዘዋዋሪዎች አለቃ የሆነውን አማዶ ካሪሎ ፉንቴስ መኖሪያ ቤትን ለጨረታ አቀረበ።

    የአደንዛዥ ዕፅ አዘዋዋሪዎች አለቃው ቤት ለጨረታ የቀረበው አገሪቱ የኮቪድ-19ን ለመዋጋት የምታደርገውን ጥረት በገንዘብ ለመደገፍ ነው ተብሏል።

    ካሪሎ ፉንቴስ፣ በቅጽል ስሙ 'የሰማያቶች ጌታ' በመባል የሚታወቅ ሲሆን የተደረገለት የፕላስቲክ ቀዶ ጥገና ከተበላሸ በኋላ እአአ በ1997 ሕይወቱ አልፏል።

    የቀድሞ ቤቱ መኪናዎቹን፣ ጌጣጌጦችና አውሮፕላን ጨምሮ በአጠቃላይ 4.5 ሚሊዮን አውጥቷል። የቤቱ ዋጋ ብቻውን 2 ሚሊዮን ዶላር እንደሆነ የወጣው ዜና ጨምሮ ያሳያል።

    ገንዘቡም የኮቪድ-19ን ለመዋጋት እንደሚውል መንግሥት አስታውቋል።

  11. በጀርመን በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች ቁጥር መንግሥት ካሳወቀው 'በ10 እጥፍ ሊበልጥ ይችላል' ተባለ

    ጀርመን በወረርሽኑ ምክንያት የጣለቻቸውን ገደቦች ማላላት ጀምራለች

    የፎቶው ባለመብት, Getty Images

    የምስሉ መግለጫ, ጀርመን በወረርሽኑ ምክንያት የጣለቻቸውን ገደቦች ማላላት ጀምራለች

    በጀርመን በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች ቁጥር መንግሥት በይፋ ካሳወቀው በ10 እጥፍ ሊበልጥ እንደሚችል አንድ ጥናት አመለከተ።

    ጀርመን በይፋ ያስታወቀችው በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች ቁጥር 160 ሺህ የሚጠጋ ነው።

    የቦን ዩኒቨርሲቲ ተመራማሪዎች ግን 1.8 ሚሊየን ሰዎች በቫይረሱ ሳይያዙ እንዳልቀሩ ግምታቸውን አስቀምጠዋል።

    ገና ግምገማ ያልተደረገበት ጥናቱ፤ በአገሪቱ ክፉኛ በቫይረሱ ከተጠቁ አካባቢዎች አንዷ በሆነችው ሄንስበርግ ከተማ የሚኖሩ 919 ሰዎች ናሙና ላይ ትኩረት አድርጓል።

    በዚህም በቫይረሱ ከተያዙ አምስት ሰዎች ውስጥ ቁጥራቸው ከአንድ በላይ የሆኑ ሰዎች ምልክት አላማሳየታቸውን ጥናቱ ደርሸበታለሁ ብሏል።

    ጀርመን በወረርሽኑ ምክንያት የጣለቻቸውን ገደቦች ማላላት የጀመረች ሲሆን፤ የእንስሳት ፓርኮች፣ ቤተ መዘክሮች እንዲሁም ጸጉር ቤቶች ተከፍተዋል። የተወሰኑ ተማሪዎችም ወደ ትምህርት ቤት ተመልሰዋል።

  12. የአሜሪካ ጠቅላይ ፍርድ ቤት የያዛቸውን ጉዳዮች በስልክ ሊያስችል ነው

    የአሜሪካ ጠቅላይ ፍርድ ቤት

    የፎቶው ባለመብት, Getty Images

    የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ በተለያዩ አገራት ቀድሞ የነበሩ አሰራሮችን እየቀየረ ነው። ክፉኛ በቫይረሱ የተጠቃችው አሜሪካም የገጠማት ይሄው ነው።

    የአሜሪካ ጠቅላይ ፍርድ ቤት በፍርድ አሰጣጥ ሂደቱ ላይ ለውጥ አድርጓል።

    በሚቀጥሉት ሁለት ሳምንታት ፍርድ ቤቱ በታሪኩ ለመጀመሪያ ጊዜ የፍርድ ቤት ክርክሮችን በስልክ ሊያድምጥ እንደሆነ አስታውቋል። በችሎቱ የሚሰሙ ድምጾችም በቀጥታ ይሰራጫሉ ተብሏል።

    በመሆኑም በርካታ ጠበቆች የያዟቸውን ጉዳዮች ከቤታቸው ሆነው መስራት የሚችሉ ሲሆን ዳኞች ግን ቢሮ መግባት ይጠበቅባቸዋል።

    በፍርድ ሂደቱ ላይ የሚሰየሙትም መደበኛ የሥራ ልብሳቸውን ለብሰው ነው።

    የትራምፕን የፋይናንስ መዝገብ ጨምሮ በርካታ ከፍተኛ ጉዳዮችም መታየት እንዲቀጥሉ ቀጠሮ ተይዞላቸዋል።

  13. "የሰው ያልሆኑ ናሙናዎችን ሲመረምሩ ነበር" የተባሉ የታንዛኒያ የኮሮናቫይረስ ላብራቶሪ ኃላፊዎች ከሥራ ታገዱ

    በጎ ፈቃደኞች እጅ ሲያስታጥቡ

    የፎቶው ባለመብት, Getty Images

    የታንዛኒያ ብሔራዊ የጤና ላብራቶሪ ዳይሬክተር እና የጥራት ሥራ አስኪያጁ ከሥራ ታግደው ምርመራ እየተካሄደባቸው እንደሆነ ተገለጸ፡፡

    ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎቹ ከሥራ የታገዱት ፕሬዚደንት ጆን ማጉፋሊ በላብራቶሪው ያሉት የኮሮናቫይረስ መመርመሪያ መሳሪያዎች ትክክለኛነት ላይ ጥያቄ ካነሱ ከአንድ ቀን በኋላ ነው፡፡

    ፕሬዚደንቱ ትናንት ከትውልድ ቀያቸው ቻቶ በቀጥታ ሥርጭት ላይ "በምስጢር ስምና እድሜ የተሰጣቸው፣ በዘፈቀደ የተወሰዱና የሰው ያልሆኑ ናሙናዎችን ሲልኩ እንደነበር ገልጸው፤ ላብራቶሪው ይህንን ሲመረምር ነበር" ብለዋል፡፡

    ፕሬዚደንቱ እንዳሉት ከእንስሳት እና ከፍራፍሬ የተወሰዱ ናሙናዎች ያልተገመተ ውጤት አሳይተዋል፤ የተወሰኑት በቫይረሱ እንደተያዙ ሌሎቹ ነጻ እንደሆኑ ተገልጿል፡፡

    "ለምሳሌ ያህል የነዳጅ ዘይት የ30 ዓመት ጃቢር ሃምዛ (ወንድ) በሚል ተሰይሞ ከቫይረሱ ነጻ መሆኑ ተገልጿል፡፡ የፍራፍሬ ናሙና የ45 ዓመት ሴት ሳራ ሳምዌሊ ብለን ላክን ውጤቱ አልታወቀም፡፡ የፓፓያ ናሙናን የ26 ዓመት ኤልሳቤጥ አኔ ብለን ስንልክ ፓፓያው በቫይረሱ እንደተያዘ ተረጋግጧል" ሲሉ በምሳሌ አስረድተዋል።

    በተጨማሪም ከወፍ እና ከፍየል የተላከ ናሙና ሁለቱም በቫይረሱ መያዛቸው ተረጋግጧል፤ ሆኖም ከጥንቸል የተላከው ናሙና ምንም ሳያመላክት ቀርቷል-ብለዋል ፕሬዚደንቱ፡፡

    በጤና ሚኒስቴር ባወጣው መግለጫ ሚኒስትሩ ጉዳዩን ለማጣራት 10 ሰዎች ያሉበት ኮሚቴ ማዋቀሩን ገልጸው፤ ውጤቱ ከ9 ቀናት በኋላ ይታወቃል ብለዋል፡፡

    ይሁን እንጅ በላብራቶሪው አሁንም የኮሮናቫይረስ ምርምራ እየተካሄደ ነው።

    ታንዛኒያ ኮሮናቫይረስን ለመከላከል የምትወስደው እርምጃ እምብዛም ነው በሚል ይተቻል።

    ይሁን እንጅ መንግስት ከዓለም ጤና ድርጅት የሚሰጠውን መመሪያ በሙሉ እየተከተልኩ ነው ሲል ትችቱን ተቃውሞታል።

    በቅርብ የወጡ መረጃዎች እንደሚያሳዩት በአገሪቷ በአጠቃላይ 480 ሰዎች በቫይረሱ መያዛቸው ሲረጋገጥ ከእነዚህ መካከል 167 ሰዎች ያገገሙ ሲሆን 16 ሰዎች ደግሞ ሕይወታቸው አልፏል።

  14. በካናዳ የሚኖረው ኢትዮጵያዊ ቤተሰቡን ከኮቪድ-19 እንዴት እየተከላከለ ነው?

  15. ኡጋንዳውያን 6 ሚሊየን ዶላር በመሰብሰብ ለመንግሥታቸው ሰጡ

    የኡጋንዳ ፖሊስ

    የፎቶው ባለመብት, AFP

    ኡጋንዳውያን ለኮቪድ-19 መከላከል የሚውል 6 ሚለዮን ዶላር አዋጥተው ለመንግሥታቸው ሰጡ።

    ይህ ገንዘብ መንግሥታቸው የኮሮናቫይረስ ስርጭትን ለመከላከል የሚጠቀምባቸውን መኪኖችን የሕክምና ቁሳቁስ አቅርቦት ለመደገፍ ይውላል ተብሏል።

    ኡጋንዳ ኮሮናቫይረስን ለመከላከል ከኢቦላ ያገኘችውን ትምህርት በግብዓትነት መውሰዷን ትናገራለች።

    የኮቪድ-19 ወረርሽኝ የዜጎችን ጤና ብቻ ሳይሆን የምግብ ዋስትና ጭምር በመጉዳቱ፣ ኡጋንዳውያን ለአቅመ ደካሞች የምግብ ድጋፍ እያደረጉ ይገኛሉ።

    ፕሬዝዳንት ዩዌሪ ሙሴቪኒ ዜጎች አቅም ለሌላቸው ሰዎች የሚያደርጉትን የምግብ ድጋፍ ያደነቁ ሲሆን በተጨማሪም ገንዘብ፣ መኪና፣ እና የሕክምና ቁሳቁስ እንዲደግፉም ጠይቀዋል።

    ከዚህ የድጋፍ ጥያቄ በኋላ ግለሰቦችና ድርጅቶች 50 ፒክአፕ መኪኖችና አምቡላንሶች ድጋፍ ያደረጉ ሲሆን ይህም አገሪቱ የኮቪድ-19 መከላከል በመላው አገሪቱ ለማካሄድ ለአስቸኳይ ጊዜ የምትጠቀምባቸውን መኪኖች ወደ 1300 ከፍ አድርጎታል።

    የገንዘብ ድጋፉ በጨመረ ቁጥር የሚገኘው ገንዘብ ተጨማሪ መኪኖችን ለመግዛት ይውላል ተብሏል።

  16. ለስድስት ሳምንታት ቤት ውስጥ በመቀመጥ የተለወጡ ፊቶች

    ጀምስ ስፑነር

    የፎቶው ባለመብት, James Spooner

    የምስሉ መግለጫ, ጀምስ ስፑነር

    የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝን ተከትሎ አገራት በጣሏቸው ገደቦች ምክንያት በርካታ ለውጦች ተስተውለዋል፡፡

    ከእነዚህ ለውጦች መካከል በሰዎች አካላዊ ገጽታዎች ላይ የታዩ ናቸው፡፡

    ይህንንም ተከትሎ የተለያዩ ሰዎች ለስድስት ሳምንታት ቤት ውስጥ በመቀመጣቸው በፊታቸው ላይ ያዩዋቸውን ለውጦች በፎቶ ሲያጋሩ ነበር፡፡

    የ48 ዓመቱ ጀምስ ስፑነር "ሚስቴ 'ጸጉርህ ሲያድግ ወደ ታች እየወደቀ ሳይሆን ወደላይ ቀጥ እያለ እየሄደ ነው' ብላኛለች" ሲል በጣም ያሳቀው ነገር እንደሆነ ተናግሯል፡፡

    ኢላ ሮድናይት

    የፎቶው ባለመብት, Eila Rodnight

    የምስሉ መግለጫ, ኢላ ሮድናይት

    የ66 ዓመቷ ኢላ ሮድናይት ጸጉሯ ጥሩ ላይ እንዳልሆነ እንደሚሰማት ተናግራለች፡፡ በዚያ ሁኔታ ይዛው መቆየትም አልፈለገችም፡፡ በመሆኑም በ43 ዓመታት የትዳር ጊዜ ውስጥ ለመጀመሪያ ጊዜ ባለቤቷን ጸጉሯን እንዲቆርጣት ጠይቀዋለች፡፡

    አሊስተርን

    የፎቶው ባለመብት, Alistair Davidson

    አሊስተርን "በቤት ውስጥ የመቀመጥ ገደቡ ይህንን ለመሞከር እድል ሰጥቶናል፤ በረዥም ጸጉር ምን እንደምንመስል አሳይቶናል፡፡ ወድጀዋለሁ፡፡" ብለዋል፡፡

    ተመሳሳይ የእንቅስቃሴ ገደብ በተጣለባቸው አገራት የምትኖሩ ወዳጆቻንስ ለሳምንታት በቤት ውስጥ በመቀመጣችሁ በራሳችሁ ላይ ምን ለውጥ አያችሁ? እስኪ ፎቶዎቻችሁን አጋሩን፡፡

  17. ኮቪድ-19ን ለመከላከል 3 ሺህ የጎዳና ተዳዳሪዎች መጠለያ ውስጥ ገቡ

    የጎዳና ተዳዳሪዎች በመጠለያ ውስጥ

    የፎቶው ባለመብት, ELSHADAY

    ከአዲስ አበባና ከሐዋሳ የተሰበሰቡ የጎዳና ተወዳዳሪዎች በሐዋሳ በተዘጋጀላቸው መጠለያ ውስጥ እንዲገቡ ተደረገ።

    ወደ ሶስት ሺህ የሚጠጉት እነዚሀ የጎዳና ተዳዳሪዎች ወደ መጠለያ የገቡት የኮሮናቫይረስን ለመከላከል ነው ተብሏል።

    የጎዳና ተዳዳሪዎቹን በመሰብሰብ መጠለያ ጣቢያ እንዲገቡ የሚያደርገው ኤልሻዳይ ሪሊፍ ኤንድ ዴቨሎፕመንት ከመንግሥት ጋር በመተባበር መሆኑን የድርጅቱ የሚዲያ ኃላፊ አቶ ገብረ ጊዮርጊስ ንጉሴ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

    የጎዳና ተዳዳሪዎቹ በመጠለያ ጣቢያ ውስጥ ምግብ፣ ልብስና ስልጠና ይሰጣቸዋል ተብሏል።

    የሚዲያ ኃላፊው እንደተናገሩት ይህንን ስራ የሚሰሩት ከአዲስ አበባ ማህበራዊና ሰራተኛ ጉዳይ፣ የሀዋሳ ከተማ አስተዳደር፣ የወጣቶችና የሕፃናት ሚኒስቴር ጋር መሆኑን ለቢቢሲ ተናግረዋል።

    እንደ ኃላፊው ገለፃ ከሆነ በሚቀጥለው ወር በአገሪቱ ከሚገኙ የተለያዩ ከተሞች የጎዳና ተዳዳሪዎችን በመሰብሰብ ይህንን ቁጥር ወደ 10 ሺህ ከፍ ለማድረግ እየሰሩ ነው።

    አክለውም የበሽታውን ስርጭት ከመከላከል ባሻገር የሰዎቹን ሕይወት ለመቀየር ጥረት ይደረጋል ብለዋል።

    እንደ ኃላፊው ገለፃ በተለያዩ የኢትዮጵያ ትላልቅ ከተሞች በሺዎች የሚቆጠሩ የጎዳና ተዳዳሪዎች ይገኛሉ።

  18. ማዳጋስካር ከዕጽዋት የሰራችውን "የኮቪድ-19 ፈዋሽ መድሃኒት" ልታስመረምር ነው

    አንድሪያ ራጆሊና

    የፎቶው ባለመብት, AFP

    የማዳጋስካር ፕሬዝዳንት አገራቸው ከአሪቲ ቅጠል የሰራችውን መጠጥ በክሊኒክ ውስጥ ለኮቪድ-19 ፈዋሽ መሆን አለመሆኑ ሙከራ ሊደረግበት መሆኑን አስታወቁ።

    ፕሬዝዳንቱ ከዕፅዋት አገኘሁት ያሉት መድኃኒት ከአርቲሜዥያ ወይም በኢትዮጵያውያን ዘንድ አርቲ ከሚባለው ተክል የተሰራ ነው።

    እንደ አንድሪያ ራጆሊና ከሆነ በሚቀጥለው ሳምንት ክትባቱ ሙከራ ይደረግበታል።

    ሕዝባቸውንም አሪቲ ትከሉ ሲሉ መክረዋል።

    ፕሬዝዳንት ራጆሊና ከአሜሪካውያን ተመራማሪዎች ጋር መነጋገራቸውን ገልፀዋል።

    ይህ ፕሬዝዳንቱ ፈዋሽ ነው ብለው ያዘጋጁት መጠጥ ከዓለም ጤና ድርጅት እውቅና እንዲያገኝ እየሰሩ መሆኑን ጨምረው አስታውቀዋል።

    ይህ ኮቪድ-19 ይፈውሳል የተባለ መጠጥ ወደ ጊኒ ቢሳዋና ኢኳቶሪያል ጊኒ የተከፋፈለ ሲሆን፣ ታንዛኒያ በበኩሏ ይህንን መጠጥ ለመውሰድ ወደ ማዳጋስካር አውሮፕላን እንደምትልክ ተናግራለች።

    የዓለም ጤና ድርጅት ግን ኮቪድ-19 ለመከላከል ተብለው በግል የሚወሰዱ መድሃኒቶችን እንደማይመክር ለቢቢሲ በላከው ደብዳቤ ላይ ገልጿል።

  19. በርግጥ ኮሮናቫይረስን ከሌሊት ወፍ ተቀብሎ ወደ ሰው ያስተላለፈው የዱር እንስሳ የቱ ነው?

    የዉሃን ከተማ የዱር እንስሳ ገበያ

    የፎቶው ባለመብት, Reuters

    በቻይናዋ ዉሃን ግዛት የተቀሰቀሰውና ወደ ተለያዩ የዓለም አገራት በመዛመት ላይ ያለው ኮሮናቫይረስ (ኮቪድ-19) እንዴት ከእንስሳት ወደ ሰዎች እንደተላለፈ ለማወቅ ተመራማሪዎች ከባድ ጥናት ላይ ናቸው።

    በአሁኑ ወቅት ያለው መላምት በቻይና ጫካ ውስጥ ከተገኘ የሌሊት ወፍ እንጥብጣቢ ፈሳሽ በራሪ ነፍሳትን ወደሚመገቡ እንስሳት ተላልፎ፣ በመጨረሻ ወደ ዱር እንስሳት ተዛምቷል የሚል ነው።

    ከዚያም በቫይረሱ የተያዘ እንስሳ ሰው እጅ ወደቀ፤ ቫይረሱ ከዚህ ሰው የዱር እንስሳት መሸጫ ገበያ ውስጥ ወደሚሰሩ ሰዎች ተላልፎ በመጨረሻ የዛሬው ዓለም አቀፍ የኮሮና ስርጭት ላይ ተደረሰ።

    በአሁኑ ወቅት ሳይንቲስቶች በዚህ መላምት ላይ እርግጠኛ ለመሆን ከፍተኛ ጥረት እያደረጉ ነው።

    ኮሮናቫይረስ ከእንስሳ ወደ ሰው እንደተላለፈ ቢረጋገጥም ተመራማሪዎች የመጀመሪያው ሰው እንዴት እንደተያዘ እርግጠኛ አይደለንም እያሉ ነው።

    የዓለም ጤና ድርጅት የኮቪድ-19 መነሻን ከሌሊት ወፍ ወደ ሰው እንደተላለፈ ቢጠቁምም፣ ከሌሊት ወፍ ቫይረሱ የተላለፈበት የዱር እንስሳ ላይ አንዳንድ ተመራማሪዎች እርግጠኛ አይደለንም ሲሉ ተደምጠዋል።

    ከዚህ ቀደም በዉሃኑ የእንስሳት ገበያ ኮሮናቫይረስን በመርጨት የተጠረጠረው እንስሳ ጉንዳን በሊታው ፓንጎሊን ነበር።

    እንደ ተመራማሪዎቹ ከሆነ ቫይረሱ ያለበት እንስሳ በዉሃን የዱር እንስሳት ገበያ ይሸጥ አይሸጥ ግልጽ አይደለም ብለዋል።

    ይሁን አንጂ የዱር እንስሳት ንግዱ ለቫይረሱ መምጫነት ምክንያት መሆኑን ተመራማሪዎቹ አልካዱም።

    የለንደን ዩኒቨርስቲ የእንስሳት ጥናት ማህበር አባል የሆኑት ፕሮፌሰር አንድሪው ከኒንግሃም፣ "ይህ ሊሆን እንደሚችል እየጠበቅን ነበር" ብለዋል።

    አክለውም “ይህ በሽታ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ሰውና የዱር እንስሳት ባላቸው የቅርብ ግንኙነት የተነሳ ቶሎ ቶሎ እየተከሰተ ነው።” ሲሉ ተናግረዋል።

  20. በቫይረሱ ስጋት ስደተኞች ከግሪክ ካምፖች ወደ ሌላ ቦታ ተዛወሩ

    ማስክና ጓንት ያደረጉ ህጻናት ሲጫወቱ

    የፎቶው ባለመብት, Getty Images

    የምስሉ መግለጫ, ከሌስቦስ ደሴት የመጡ በመቶዎች የሚቆጠሩ ስደተኞች ሰኞ ዕለት አቴንስ ደርሰዋል

    በግሪክ የኮሮናቫይረስ ሥርጭትን ለመቀነስ ይረዳ ዘንድ በሌስቦስ ደሴት በተጨናነቀ ካምፕ ውስጥ የነበሩ ስደተኞች ወደ ሌሎች ከተሞች መዛወራቸው ተነገረ፡፡

    መንግሥት በግሪክ ደሴቶች ከሚገኙ ማዕከላት ቤተሰቦቻቸውንና በእድሜ የገፉ ሰዎችን ጨምሮ 2ሺህ 300 ስደተኞችን ወደ ከተሞች ለማዛወር አቅዷል፡፡ ግለሰቦቹም ለሁለት ሳምንታት በለይቶ ማቆያ ይቆያሉ ብሏል፡፡

    የስደት ጉዳዮች ሚኒስትር ኖቲስ ሚታራቺ እንዳሉት በማዕከላቱ እስካሁን እንድም ሰው በቫይረሱ እንዳልሞተ እሁድ ዕለት አስታውቀዋል፡፡ ነገር ግን ወረርሽኙ እነርሱ ጋር እንዳልደረሰ ለማወቅ ምርመራ ማካሄድ ያስፈልጋል ብለዋል፡፡

    ባለፈው ወር የሰብዓዊት መብት ተሟጋቹ ሂውማን ራይትስ ዎች በስደተኞቹ ማዕከላት ወረርሽኙን ለመቆጣጠር መንግሥት የሚገባውን ያህል አልሰራም ሲል ትችት ሰንዝሮ ነበር፡፡