በቱፓክ ግድያ ላይ ክስ መመስረቱን እህቱ ‘ወሳኝ ድል’ ነው አለች

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
አሜሪካ ካፈራቻቸው ዕዉቁ እና ለሂፕ ሆፕ ሙዚቃ መሰረት ነው የሚባለው ቱፓክ ሻኩር ግድያ ጋር ተያይዞ ከ27 ዓመታት በኋላ ክስ መመስረቱ እህቱ ወሳኝ ድል መሆኑን ተናገረች።
በራፐሩ ግድያ የቀድሞ የወሮበላ ቡድን መሪ ክስ ተመስርቶበታል።
በጥልቅ ግጥሞቹ እና የወቅቱን የፖሊስ ጭካኔ፣ የጥቁሮች ድህነት፣ ሥርዓታዊ እና መዋቅራዊ ጭቆናን በማንሳት ለማኅበራዊ ፍትህ በሙዚቃው የታገለው ቱፓክ የተገደለው በ25 ዓመቱ ነው።
በላስቬጋስ መኪና ውስጥ እያለ በተተኮሰበት አራት ጥይት በአውሮፓውያኑ 1996 ሕይወቱ አልፏል።
አርብ ዕለት የኔቫዳ ፍርድ ቤት በ60 ዓመቱ ዱአን ዴቪስ ወይም ኬፊ ዲ ላይ የግድያ ክስ መስርቶበታል።
የራፐሩ እህት ሴክይዋ ሻኩር “ዛሬ የድል ዕለት ናት “ ስትል ተናግራለች።
“ዓለም፣ አገራችን እንዲሁም የፍትህ ሥርዓቱ እና ሕዝባችን የሙዚቀኛው መገደል ምን ያህል እንዳጎደለ መረዳታቸው ለኔ መሰረታዊ ነው። ወንድሜ፣ የእናቴ ልጅ፣ የአባቴ ልጅ ማለፉን መቀበል ምን ያህል ከባድ እንደሆነም ሊረዱ ይገባል” ስትልም እህቱ በኢንስታግራም ገጿ ላይ አስፍራለች።
“በወንድሜ ቱፓክ ሕይወት እና ሞት እንዲሁም በአጠቃላይ በሻኩር ቤተሰብ በርካታ ያንዣበቡ ሰዎች አሉ። ገና የሚቀሩ እና ያልተፈቱ ጉዳዮች አሉ።በሁሉም በኩል እውነተኛ ፍትህ እንፈልጋለን” ስትልም አጽንኦት ሰጥታለች።
የሻኩር የእንጀራ ወንድም ሞፕሪም ሻኩር በበኩሉ በግድያው ላይ ክስ መመስረቱ ደስታ እና ምሬት የተቀላቀለበት ነው ብሏል።
“ከሁለት አስርት ዓመታት በላይ በህመም አሳልፈናል። ለአመታት ያህል ይህ ሰው ምን ያወራ እንደነበር ያውቃሉ” ሲልም ለሲኤንኤን ተናግሯል”
“አሁን ለምን ተከሰሰ? ለኛ አሁንም ቢሆን አላከተመም። ለምን እንደሆነ ማወቅ እንፈለጋለን። ተባባሪዎች ከነበሩትም እንዲሁ ልናውቅ ይገባል” ብሏል።
ኬፊ ዲ ላስቬጋስ በሚገኘው ቤቱ አቅራቢያ በቁጥጥር ሥር የዋለው ዐርብ ዕለት ነበር።
አቃቤ ሕግ ኬፊ ዲን ‘ሳውዝ ሳይድ ኮምፕተን ስትሪት ጋንግ’ የተሰኘ የወሮበላ ቡድንን ይመራ እንደነበር እና የቱፓክን ሞት እንዳዘዘ ለፍርድ ቤቱ አስረድተዋል።
የፖሊስ ኃላፊው ጄሰን ጆሃንሰን በበኩላቸው ይህ ከወሮበላ ቡድኖች ጋር የተያያዘ ወንጀል መሆኑ ግልጽ ሆኗል እናም ጉዳዩን በተደጋጋሚ ገምግመነዋል ሲሉም ዐርብ እለት በነበረ ጋዜጣዊ መግለጫ ተናግረዋል።
ሆኖም በአውሮፓውያኑ 2018 አዲስ መረጃ መምጣቱን ተከትሎ ጉዳዩ መጠናከሩን አስረድተዋል።
የፖሊስ ኃላፊው ኬፊ ዲ በቱፓክ በተተኮሰበት መኪና ውስጥ እንደነበር ማመኑንም በዚህ ወቅት ተናግረዋል።
ከ27 ዓመታት በፊት አራት ጥይቶች የተተኮሰበት ቱፖክ ሆስፒታል ከገባ ከቀናት በኋላ ነበር ሕይወቱ ያለፈው።












