በአየርላንድ የጂምናስቲክ ውድድር ተለይታ ሜዳሊያ ያልተሰጣት ጥቁር ታዳጊ ጉዳይ ውዝግብ አስነሳ

በአየርላንድ የጂምናስቲክ ውድድር ከሁሉም ነጮች ተለይታ ሜዳሊያ ያልተሰጣት የ10 ዓመት ጥቁር ታዳጊ ጉዳይ ውዝግብ አስነሳ።
ባለፈው ዓመት በደብሊን በተካሄደ ዝግጅት ላይ አንዲት ባለስልጣን ለሁሉም ተሳታፊዎች ሜዳሊያ ካደሉ በኋላ ጥቁር ታዳጊዋን አልፈው ሲሄዱ የሚያሳይ ቪዲዮ በቅርቡ ወጥቷል።
በርካቶች ይህ ፍጹም ዘረኝነት ነው ሲሉም ድርጊቱን አውግዘውታል።
ጉዳዩን አስመልክቶ የአየርላንድ ጂምናስቲክ ለቤተሰቦቿ ይቅርታ የጠየቀ ሲሆን የታዳጊዋ እናት “ይቅርታው ፋይዳ የለውም” ስትል ተናግራለች።
የታዳጊዋ እናት በወቅቱ በልጇ ላይ የተከሰተውን ሁኔታ መመልከቱ “አሰቃቂ” ነው ስትልም ገልጻዋለች።
በርካቶች ይህንንም ተከትሎ ቁጣቸውን የገለጹ ሲሆን የአየርላንድ ጂምናስቲክም “ለተፈጠረው ሁኔታ” ይቅርታ እንጠይቃለን ብሏል።
በዚህ መግለጫውም ክስተቱ እንዳሳዘነው ገልጾ “እንዲህ አይነት ነገር ዳግም እንዳይከሰት የበለጠ መስራት እንደሚያስፈልግ እና “ማንኛውንም ዘረኝነት እናወግዛለን” ብሏል።
ሆኖም የታዳጊዋ እናት እንደገለጸችው የስፖርት ተቋሙ በይፋ ይቅርታ የጠየቀው ክስተቱ ከተፈጠረ ከተፈጠረ ከ18 ወራት በኋላ እንደሆነ ገልጻ “አለም ስለጠየቃቸው ነው” ብላለች።
“ይቀርታው ከሞላ ጎደል ከንቱ ነው። ርህራሄ የማይታይበትና ከልባቸው እንዳልሆነም ይሰማኛል” ብላለች።
“18 ወራት አልፈዋል እናም ይቅርታ እንዲጠይቁን ጫና የተደረገባቸው ይመስላል” ስትል ለቢቢሲ ተናግራለች።
“ለረጅም ጊዜ አልቅሻለሁ። ይቅርታው ከመምጣቱ በፊትም በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች አብረውኝ አልቅሰዋል” ስትልም አስረድታለች።
ባለፈው ዓመት በአየርላንድ ዋና ከተማ ደብሊን ጂምስታርት በተባለ ዝግጅት ላይም ነው ታዳጊዋ ሜዳሊያ ያልተሰጣት።
ሁሉም ህጻናት የተሳትፎ ሜዳሊያዎችን ሲቀበሉ ጥቁሯ ታዳጊን አልፈዋታል።
የዝግጅቱ ዳኛ ሰራሁት ላሉት “ስህተት” ለታዳጊዋ ቤተሰቦች ይቅርታ የጠየቁ ሲሆን “በፍጹም ዘረኛ አይደለሁም” ብለዋል።
ይሁን እንጂ የታዳጊዋ ቤተሰቦች ልጃቸው ሜዳሊያ ከሌሎቹ ተለይታ ያልተሰጣት በዘረኝነት ምክንያት ነው ይላሉ።
በ21ኛው ክፍለ ዘመን በዚህ ወቅት እንዲህ አይነት ነገር መፈጸሙም የማይታመን መሆኑን ነው እናቲቱ ያስረዳችው።
“በእርግጥ ግልጽ ብሎ የወጣን ነገር መናገር ከፍተኛ ህመም ይፈጥራል። ልጄ በዚያ ውድድር ላይ ብቸኛዋ ጥቁር ነበረች። በጥሩ ሁኔታም ተሳትፋ ነበር።ለተፈጠረው ነገር ምክንያት መፍጠር አያስፈልግም። ልጄን በጣም ነው ያበሳጫት” ስትልም ተናግራለች።
“ጥቁር በመሆኗ ሊቀጧት የፈለጉ ይመስላል። ለ10 ዓመት ታዳጊ በዚህ ሁኔታ ማለፍ በጣም አሳዛኝ ነው” ብላለች።












