በረራ ላይ መስኮቱ የተገነጠለው የቦይንግ 737 ማክስ አውሮፕላን ምክትል ፕሬዝዳንት ሥራ ሊለቁ ነው

ታትሟል

ባለፈው ጥር ወር 737 ማክስ አውሮፕላን በበረራ ላይ እያለ መስኮቱ መገንጠሉን ተከትሎ ከፍተኛ ጫና ውስጥ የነበረው ቦይንግ ከአውሮፕላኑ ምርት ክፍል ምክትል ፕሬዝዳንቱ ጋር ሊለያይ መሆኑ ተሰምቷል።

ለ18 ዓመታት በኩባንያው የሰሩት ኤድ ካላርክ ከቦይንግ እንደሚለቁ ኩባንያው ትናንት ይፋ ካደረገ በኋላ ከፍተኛ ግርምት ተከስቷል።

ቦይንግ እዚህ ውሳኔ ላይ የተደረሰው የምርቱን ጥራት እና ደህንነት ለማሻሻል እንደሆነ አስታውቋል።

የኃላፊው የመልቀቅ ዜና የተሰማው ኩባንያው ከተቆጣጣሪዎች ጋር ለመገናኘት ዝግጅት እያደረገ ባለበት ሰዓት ነው።

ባለፈው ጥር ንብረትነቱ የአላስካ አየር መንገድ የሆነ አውሮፕላን በረራ ላይ ሳለ ችግር ከገጠመው በኋላ ቦይንግ ከፍተኛ ጫና ውስጥ ወድቋል። የአላስካ አየር መንገድ ንብረት የሆነው ይህ አውሮፕላን መስኮቱ በመገንጠሉ ሰዎች ላይ የደረሰ ጉዳት ባይኖርም በረራው ተቋርጦ እንዲያርፍ ግድ ሆኖበታል።

ታዋቂው 737 ማክስ አውሮፕላን በዚህ ክስተት ብቻ ሳይሆን ከመሻሻሉ በፊት ባለው ምርት የኢትዮጵያ አየር መንገድን ጨምሮ ባጋጠሙ አደጋዎች የ346 ሰዎች ህይወት እንዲያልፍ ምክንያት ሆኗል።

በዚህም ሳቢያ የአምራቹ የምርት ሂደት ላይ ከፍተኛ ጥያቄን አስነስቷል። በእነዚህ አደጋዎች ምክንያት አውሮፕላኖቹ በመላው ዓለም ለ20 ወራት ከአግልግሎት ውጪ ሆነው ቆይተዋል።

የአሜሪካ መንግሰት የፌዴራል አቪዬሽን አስተዳደር ቦይንግ የ 737 ማክስ አውሮፕላንን ምርት እንዳያስፋፋ ያገደው ሲሆን አውሮፕላኖቹ የተመረቱበትን ሂደትም መርምሯል። አውሮፕላኖቹ ከስራ ወጪ በተደረጉበት ጊዜ በተደረገ ምርመራ ለክፉ የማይሰጡ ሌሎች እክሎችም ተገኝተዋል።

አላስካ አየር መንገድ ላይ የገጠመውን ችግር በተመለከተ በተደረገ የመጀመሪያ ደረጃ ምርመራ ቦይንግ ማክስ 737 9 አውሮፕላን በሩን የሚያገናኙ ብሎኖች ላልተው መጥፋታቸው ታውቋል እነዚህ ብሎኖች የጠፉት በቦይንግ የዋሽንግተን ፋብሪካ ውስጥ እንደሆነ ታውቋል።

ኤዲ ክላርክ የቦይንግ ምክትል ፕሬዚዳንት እና በሬንቶን ዋሽንግተን በሚገኘው የአውሮፕላን ማምረቻ 737 ማክስ አውሮፕላን ፕሮግራም ተቆጣጣሪ ናቸው።

ይህ የአውሮፕላን ማምረቻ አየር ላይ መስኮቱ የተገነጠለው አውሮፕላን የተሰራበት ነው።

የተለያዩ የደህንነት ተሟጋቾች በኩባንያው የአመራር ለውጥ እንዲደረግ ሲወተውቱ ቆይተዋል።

ኃላፊውን አሁን ላይ የ737 ማክስ ምርት የምርት ማድረስ ክትትል ምክትል ፕሬዝዳንት የሆኑት ኬቲ ሪንጎልድ ይተኳቸዋል።

ኩባንያው የምርት ጥራትን የሚከታተል የምክትል ፕሬዝዳንትነት ስልጣንን እንደሚከፍትም አሳውቋል።

ትላንት ረቡዕ ለሰራተኞች በተላከ መልዕክት፣ የቦይንግ የንግድ ዘርፍ ኃላፊ የአመራር ለውጥ የተደረገው “የምናመርታቸው ሁሉም አውሮፕላኖች ጥራታቸው እና ደህንነታቸው የጠበቁ እንዲሆን ለማረጋገጥ ነው። ደንበኞቻችን ከዚህ ያነሰ ነገር አይጠብቁም። አይገባቸውምም” ብለዋል።

አክለውም የሚለቁት ኃላፊ ክላርክ ባለፉት 18 ዓመታት በቦይንግ ለነበረው አስተዋጽኦ ከፍተኛ ምስጋና አለው ሲሉም አክለዋል።