በአውስትራሊያ ታሪክ ትልቅ የሆነ 2,700 ኪሎግራም አደንዛዥ ዕፅ በቁጥጥር ሥር ዋለ

ታትሟል
የንባብ ጊዜ: 2 ደቂቃ

የአውስትራሊያ ፖሊስ 2,700 ኪሎግራም (2.7 ቶን) የሚመዝን ኮኬይን መሬት ውስጥ ከተቀበረ ምሽግ መያዙን አስታወቀ። አደንዛዥ ዕፁ በአገሪቱ ታሪክ በቁጥጥር ሥር የዋለ ትልቁ ነው።

ዕፁ 816 ሚሊዮን የአውስትራሊያ ዶላር የሚያወጣ ሲሆን አርብ ዕለት በምዕራብ ስድኒ በሐሰተኛ በሮች በሦስት ኮንቴይነሮች ተደብቆ እንደተገኘ ተነግሯል።

ከ21 ዓመት እስከ 25 ዓመት የተገመቱ ሁለት ተጠርጣሪዎች ከፖሊስ ለማምለጥ ሲሞክሩ በቁጥጥር ሥር ውለዋል። ተጠርጣሪዎቹ ለንግድ የሚውል መጠን ያለው ዕፅ በመያዝ እና ሕገ ወጥ ዕፅ ወደ አገር ውስጥ በማስገባት ወንጀል ተከስሰዋል።

ፖሊስ ኮኬይኑ ወደ አውስትራሊያ የገባው በአነስተኛ ከተማ በሰሜን ኩዊንስላንድ እንደሆነ እና በተደራጀ የወንጀል ቡድን ትዕዛዝ መሆኑን ገልጿል።

ቅዳሜ ፍርድ ቤት ቀርበው በእስር እንዲቆዩ ትዕዛዝ የተላለፈባቸው ሁለቱ ተጠርጣሪዎች ጥፋተኛ ሆነው ከተገኙ የዕድሜ ልክ እስራት ከፊታቸው ይጠብቃቸዋል።

ፖሊስ ያደረገው ብርበራ ባለፈው መጋቢት ወር 40 ኪሎግራም ኮኬይን በጀልባ መወጣጫ አካባቢ በውሃ ላይ እየተንሳፈፈ ካገኘ በኋላ በጀመረው "ተልዕኮ ሚንጂያንግ" የሚል ስያሜ የሰጠው ዘመቻ አካል መሆኑን አስታውቋል።

ተጨማሪ ስድስት ሰዎች በኪውንስላንድ እና ኒው ሳውዝ ዌልስ በቁጥጥር ሥር ውለው ክስ ተመስርቶባቸዋል።

የኮንትሮባንድ ዝውውሩ አካል ነው ተብሎ የተጠረጠረ "እናት መርከብ" በሶሎሞን ደሴት በቀጥጥር ሥር እንደዋለም ፖሊስ አስታውቋል።

ምንም እንኳ ርቀት ቢኖራትም አውስትራሊያ ለአደንዛዥ ዕፅ ንግድ ትርፋማ ገበያ ሆናለች። አንድ ግራም ኮኬይን በ300 የአውስትራሊያ ዶላር እንደሚሸጥ በኒው ሳውዝ ዌልስ ዩኒቨርስቲ የሕገ ወጥ ዕፆችን የመከታተያ ስርዓት መርጃ ይጠቁማል።

አውስትራሊያዊያን እና ኒውስላንዳዊያን በዓለም ከፍተኛ የኮኬይን ተጠቃሚዎች እንዳሏቸው የመንግሥታቱ ድርጅት ሪፖርት ያመለክታል።

የአውስትራሊያ የፌደራል ፖሊስ አዛዥ ስቴፈን ጄይ የተጠረጠረው ሴራ "በከፍተኛ ሁኔታ ምን ያህል የተደራጀ እና የወንጀል መረቦቹ ቁርጠኛ እና ትርፍ ለማግኘት የሚሄዱበትን ረጅም ርቀት ያሳያል" ብለዋል።

"የአደንዛዥ ዕፆቹ የመጀመሪያ መነሻ ለማወቅ እስካሁን ምርመራው እየተደረገ ነው። እና የወንጀል ቡድኖችን እና ማንኛውንም ይህን ዕፅ ያሳለጠ ግለሰብ ለመለየት በአገር ቤት እና ውጭ ካሉ የሕግ አስከባሪ አጋሮቻችን ጋር እንሠራለን።"