ፕሬዚዳንት ባይደን 1.2 ቢሊዮን ዶላር የተማሪዎችን ዕዳ ሰረዙ

ታትሟል

የባይደን አስተዳደር 153 ሺህ ተበዳሪዎችን ተጠቃሚ የሚያደርግ 1.2 ቢሊዮን ዶላር የትምህርት ዕዳ መሰረዙን አስታወቀ።

የአሜሪካ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ከዚህ ቀደም ከ40 ሚሊዮን በላይ ለሚሆኑ አሜሪካውያን የትምህርት ዕዳቸውን ለመሰረዝ ፕሬዚዳንት ባይደን አቅርበው የነበሩትን ዕቅድ ማገዱ ይታወሳል።

ፍርድ ቤቱ ፕሬዚዳንት ባይደን ሥልጣናቸውን ተላልፈው በቢሊዮን የሚቆጠር የትምህርት ዕዳ ለመሰረዝ መወሰናቸው ትክክል አይደለም ሲል ቀልብሶታል።

የአሁኑ ዕዳ ስረዛ የሚመለከተው በክፍያ ዕቅድ ውስጥ የተካተቱ እና የተወሰኑ መስፈርቶችን ለሚያሟሉ ብቻ ተግባራዊ ይሆናል።

የዕዳ ስረዛው የሚመለከታቸው በባይደን አስተዳደር በተዘረጋው የፍቃደኝነት የክፍያ ዕቅድ ውስጥ የተመዘገቡና ቢያንስ ለ10 ዓመታት ክፍያ ሲፈጽሙ የቆዩ እና መጀመሪያውኑ 12 ሺህ ዶላር ወይም ከዚያ በታች የተበደሩትን የሚመለከት ይሆናል።

የዕዳ ስረዛው የሚመለከታቸው አሜሪካውያን ከተነገራቸው በኋላም ወዲያውኑ ተፈጻሚ እንደሚሆንም ተገልጿል።

“በተለይም አነስተኛ ዕዳ ያለባቸውን የማሕበረሰብ ኮሌጆች የቀድሞ ተማሪዎች እና ሌሎች ተበዳሪዎችን የሚጠቅም ይሆናል። አብዛኛውንም ከትምህርት ዕዳ በፍጥነት ነጻ አውጥቶ ወደ ትክክለኛው መስመር ያስገባቸዋል” ሲልም ዋይት ሃውስ በመግለጫው አትቷል።

በትምህርት ዲፓርትመንት መረጃ መሰረት በባይደን አስተዳደር በተቋቋመው የክፍያ ዕቅድ ውስጥ የተመዘገቡ አሜሪካውያን ቁጥር 7.5 ሚሊዮን መሆኑን ነው።

በዚህ ዕቅድ ውስጥ የተመዘገቡት ሁሉም ሰዎች ከ20-25 ዓመታት ውስጥ ክፍያ ከከፈሉ በኋላ በዕዳ ስረዛ ውስጥ ለመካተት ብቁ ይሆናሉ።

ሆኖም ፕሬዚዳንት ጆ ባይደን አነስተኛ ዕዳ ላለባቸው ግለሰቦች ጊዜውን በማሳጠር ለአስር ዓመታት ያህል ብድራቸውን የከፈሉ ሰዎች በዕዳ ስረዛው ፕሮግራም መካተት እንዲችሉ አድርገዋል።

የአገሪቱ የትምህርት ዲፓርትመንት በዕዳ ስረዛው ለመካተት ብቁ የሆኑትን ነገር ግን በዚህ የክፍያ ዕቅድ ውስጥ ያልተመዘገቡ ሰዎችን ማነጋገር እንደሚጀምርም ተገልጿል።

ባይደን እስካሁን ድረስ ፕሬዚዳንታዊ ስልጣንን በመጠቀም 3.9 ሚሊዮን ለሚጠጉ ሰዎች 138 ቢሊዮን ዶላር የትምህርት ዕዳቸውን መሰረዛቸውንም ዋይት ሃውስ ገልጿል።

የአሜሪካ የትምህርት ስርዓትን በሚያጠናው የትምህርት መረጃ ኢኒሺዬቲቭ መሰረት የአሜሪካ የትምህርት ዕዳ 1.77 ትሪሊዮን እንዲሁም አንድ ሰው በአማካኝ ከ37 ሺህ ዶላር በላይ ብድር አለበት።