የሰብአዊ እርዳታ አቅርቦት ተሽከርካሪዎች ለጦርነት አላማ እየዋሉ ነው ሲል መንግሥት ከሰሰ

እርዳታ የጫኑ ተሽከርካሪዎች

የፎቶው ባለመብት, AFP

የምስሉ መግለጫ, የዓለም ምግብ ፕሮግራም በትግራይ የሰብዓዊ እርዳታ እያከፋፈለ ነው።
ታትሟል

የሰብአዊ እርዳታ ተሽከርካሪዎችን እና ግብአቶች ለወታደራዊ አገልግሎት እያዋሉ ነው ሲል የኢትዮጵያ መንግሥት ከሰሰ።

መንግሥት ይህንን ያለው ሰብዓዊ እርዳታ ጭኖ የነበረ የዓለም ምግብ ፕሮግራም ተሽከርካሪ ትግራይ ውስጥ በሰው አልባ አውሮፕላን (ድሮን) በተፈፀመ ጥቃት በፍንጣሪ መመታቱ ከተገለጸ በኋላ ነው።

ሮይተርስ የዜና ወኪል የዓለም ምግብ ፕሮግራም ቃል አቀባይን ጠቅሶ እንደዘገበው በጥቃቱ በድርጅቱ አሽከርካሪ ላይ ጉዳት ማጋጠሙን ሪፖርት እንደደረሳቸው ገልጸዋል።

የድሮን ጥቃቱን ተከትሎ በተፈጠረ ፍንጣሪ የዓለም ምግብ ፕሮግራም ሠራተኛ በሆነው አሽከርካሪ ላይ ጉዳት መድረሱን እና በተሽከርካሪው ላይም ቀላል ጉዳት ማጋጠሙን ቃል አቀባዩ ጨምረው ለሮይተርስ ተናግረዋል።

የህወሓት ቃል አቀባይ ጌታቸው ረዳ አደጋውን “አሳፋሪ ወንጀል” ሲሉ እሁድ ዕለት በትዊተር ገጻቸው ላይ ባሰፈሩት መልዕክት ላይ ገልጸውታል።

ጥቃት ደረሰበት የተባለው የዓለም ምግብ ፕሮግራም ተሽከርካሪ በሰሜን ምዕራብ ትግራይ ዛና ወደሚባል አካባቢ እርዳታ ጭኖ እየተጓዘ እንደነበር ተገልጿል።

ይህንን ተከትሎ የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ባወጣው መግለጫ ላይ ህወሓት የሰብአዊ እርዳታ ተሽከርካሪዎችን ለጦርነት መጠቀሙን ቀጥሎበታል ሲል ከሷል።

የመንግሥት ኮሙኒኬሽን፣ ህወሓት የሰብዓዊ እርዳታ ማመላለሻና ሌሎች ተሽከርካሪዎችን “የዓለም ምግብ ድርጅት እና የተመድ ዓርማ በመቀባት የጦር መሣሪያ እና ተዋጊዎችን በማመላለስ ለወታደራዊ ዓላማ እየተጠቀመ ነው” ብሏል።

ስለዚህም የእርዳታ ድርጅቶች የሚጠቀሙባቸው ተሽከርካሪዎች ለቡድኑ ጥቅም አለመዋላቸውን እንዲያረጋግጡ አሳስቧል።

አሁንም “የአገርን ህልውና እና የዜጎችን ደኅንነት ለማስከበር የመከላከል እርምጃ እየወሰደ ባለባቸው አካባቢዎች የእርዳታ ድርጅቶቹ ከመንቀሳቀስ እንዲቆጠቡ መንግሥት በድጋሚ ያስጠነቅቃል” ብሏል።

ቡድኑ ከዚህ በፊት “የእርዳታ ተሽከርካሪዎችን ለጦርነት ዓላማ፣ እንዲሁም እርዳታውንም ለታጣቂዎቹ ግብዓት ሲያደርግ ነበር” በማለት ዓለም አቀፍ ተቋማት ይህንን እንዲያስቆሙ መንግሥት ተደጋጋሚ ጥሪ ማቅረቡንም መግለጫው አስታውሷል።

ጨምሮም “የአገርን ህልውና እና የዜጎችን ደኅንነት ለማስከበር የመከላከል እርምጃ እየወሰደ ባለባቸው አካባቢዎች የእርዳታ ድርጅቶቹ ከመንቀሳቀስ እንዲቆጠቡ መንግሥት በድጋሚ ያስጠነቅቃል” ብሏል።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

ጋብ ብሎ የቆየው የሰሜን ኢትዮጵያው ጦርነት ነሐሴ ወር ላይ ካገረሸ ወዲህ በትግራይ አማጺያን ላይ በርካታ የአየር ድብደባዎች መፈፀማቸው ተነግሯል።

ይህንን በተመለከተ የፌደራል መንግሥቱ ያለው ነገር ባይኖርም ከዚህ ቀደም የክልሉ ነዋሪዎች ከወታደራዊ ኢላማዎች እንዲርቁ አስጠንቅቆ ነበር።

በፌደራል መንግሥቱና በህወሓት ኃይሎች መካከል ያገረሸው ግጭት በችግር ላይ ያሉና የእርዳታ ድጋፍ ለሚያስፈልጋቸው በሚሊዮን የሚቆጠሩ ተረጂዎች ጋር የሚደርሰውን ድጋፍ እንደሚያደናቅፈው የዓለም ምግብ ፕሮግራምን ጨምሮ ሌሎች የሰብዓዊ እርዳታ ድርጅቶች ሲገልጹ ቆይተዋል።

በተደጋጋሚም የሰብዓዊ እርዳታ አቅርቦቱን የሚያስተጓጉሉ ክስተቶች ከተለያዩ ወገኖች እንዳጋጠሟቸው ተናግረዋል።

ባለፈው ወር የዓለም ምግብ ፕሮግራም በክልሉ ውስጥ ለሚያካሂደው የእርዳታ አቅርቦት የሚገለገልበት ግማሽ ሚሊዮን ሊትር ነዳጅ በህወሓት ባለሥልጣናት እንደተዘረፈበት የገለጸ ሲሆን፣ የህወሓት ባለሥልጣናት ክሱን ማጣጣላቸው የሚታወስ ነው።

የተባበሩት መንግሥታት የእርዳታ ማስተባበሪያ ጽ/ቤት ( ኦቻ)ም አዲስ ባገረሸው ጦርነት ምክንያት ወደ ትግራይ ክልል የሚያደርሰውን የሰብዓዊ እርዳታ አቅርቦት ማቋረጡን ነሐሴ ወር አጋማሽ ላይ አስታውቋል።

የዓለም ምግብ ፕሮግራም በትግራይ ክልል 5.2 ሚሊዮን ሕዝብ እርዳታ እንደሚያስፈልገውና እርዳታውን ማድረስ ካልተቻለ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች ለከፋ የረሃብ አደጋ እንደሚጋለጡ በተደጋጋሚ አስጠንቅቋል።

የሰሜን ኢትዮጵያው ጦርነት በድርድር እንዲፈታ የተለያዩ ጥረቶች ሲደረጉ ቢቆዩም አሁንም ግን አልባት አላገኘም።

የተለያዩ ዓለም አቀፍ ድርጅቶች እና አገራትም ለበርካቶች ሞት፣ ጉዳትና መፈናቀል ምክንያት የሆነው ግጭት በሰላም እንዲፈታ አሁንም ውትወታቸውን አላቆሙም።