“በትግራይ ባለሥልጣናት 570 ሺህ ሊትር ነዳጅ ተሰርቆብናል” የዓለም ምግብ ፕሮግራም

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የዓለም ምግብ ፕሮግራም ትግራይ ውስጥ ለሚያካሂደው የእርዳታ አቅርቦት የሚገለገልበት ግማሽ ሚሊዮን ሊትር በላይ ነዳጅ በትግራይ አመራሮች እንደተሰረቀበት ገለጸ።
የድርጅቱ ዋና ዳይሬክተር ዴቪድ ቢዝሊ በይፋዊ የትዊተር ገጻቸው ላይ እንዳሉት የዓለም የምግብ ፕሮግራም ለእርዳታ ሥራው የሚያውለውን 570,000 ሊትር ነዳጅ “የትግራይ ባለሥልጣናት ሰርቀዋል” ብለዋል።
ቢዝሊ ከድርጅታቸው የተሰረቀውን ነዳጅ በተመለከተ ቁጣቸውን በሚገልጽ ሁኔታ በጻፉት ጽሑፍ ላይ፣ ድርጊቱ “የሚያስቆጣ እና አሳፋሪ ነው” በማለት በአስቸኳይ የተዘረፈው ነዳጅ እንዲመለስ ጠይቀዋል።
ህወሓት እስካሁን ድረስ በጉዳዩ ላይ ምንም ዓይነት ምላሽ አልሰጠም።
የዓለም ምግብ ፕሮግራም ዋና ዳይሬክተር ትዊተር የወጣው ረቡዕ ነሐሴ 18/2014 ዓ.ም. ላይ የህወሓት አመራሮች እና የፌደራል መንግሥቱ አንዳቸው አንዳቸውን ጥቃት ከፍተዋል በማለት መካሰሳቸውን ተከትሎ ነው።
የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዋና ፀሐፊ ቃል አቀባይ ስቴፋን ዱጃሪክ ኒውዮርክ ውስጥ ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ ላይ፣ ረቡዕ ዕለት የትግራይ ኃይሎች መቀለ ውስጥ ወደ ሚገኘው የዓለም ምግብ ፕሮግራም መጋዘን በኃይል ገብተው ዘረፋ መፈጸሙን ገልጸዋል።
በዚህም 570,000 ሊትር ነዳጅ የጫኑ 12 ቦቴዎች መዘረፋቸውና የድርጅቱ ሠራተኞች ይህንን ድርጊት ለማስቆም ቢሞክሩም እንዳልተሳካላቸው አመልክተዋል።
የመንግሥታቱ ድርጅት በትግራይ ኃይሎች ወደ መጋዘኑ ተጥሶ መገባቱን እና በንብረቱ ላይ የተፈጸመውን ዘረፋ ያወገዘ ሲሆን፣ ሁሉም ወገኖች ዓለም አቀፍ የሰብአዊ እርዳታ ሕግጋትን እንዲያከብሩ ጥሪ አቅርቧል።
የተዘረፈው ነዳጅ የዓለም ምግብ ፕሮግራም በትግራይ ክልል ለሚሰጠው የምግብ፣ የማዳበሪያ እና ሌሎች የእርዳታ ቁሶችን ለማቀረብ ሥራ የሚያገለግል መሆኑን እና ዘረፋው በሥራው ላይ እንቅፋትን እንደሚፈጥር ዱጃሪክ ተናግረዋል።
ሁለት ዓመት ሊሞላው በተቃረበውና ከትግራይ ተጀምሮ የአማራ እና አፋር ክልሎችን ባዳረሰው ጦርነት በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ሰዎች ለመፈናቀል እና ሰብአዊ እርዳታ ለመጠበቅ ተገደዋል።
የሰብአዊ እርዳታ እና መሠረታዊ አገልግሎቶች ተቋርጦ በቆየበት የትግራይ ክልል ከወራት በፊት ጦርነቱ ጋብ ማለቱን ተከትሎ የሰብአዊ እርዳታ አቅርቦት ተኩስ አቁም ስምምነት ከተደረሰ በኋላ እርዳታ እና ነዳጅ መግባት መጀመሩ ይታወሳል።
ነገር ግን ወደ ክልሉ የገባውን እርዳታ በተለያዩ የትግራይ ክልል ውስጥ ለሚገኙ ተረጂዎች ለማድረስ የነዳጅ እጥረት መኖሩን የረድኤት ድርጅቶች ሲገልጹ የቆዩ ሲሆን፣ መንግሥትም አስፈላጊው የነዳጅ አቅርቦት እንዲገባ ፈቅዶ ነበር።
በፌደራል መንግሥቱ እና በትግራይ ኃይሎች መካከል መልሶ ያገረሸው ግጭት በችግር ላይ ያሉና የእርዳታ ድጋፍ ለሚያስፈልጋቸው በሚሊዮን የሚቆጠሩ ተረጂዎች ጋር የሚደርሰውን ድጋፍ ያደናቅፈዋል።
የመንግሥታቱ ድርጅት የዓለም ምግብ ፕሮግራም ዋና ዳይሬክተር የሆኑት ዴቪድ ቢዝሊ ትግራይ ውስጥ በባለሥልጣናት የተዘረፈው ነዳጅ በሥራቸው ላይ ከፍተኛ ተጽእኖ እንደሚኖረው ገልጸዋል።
“ትግራይ ውስጥ የምግብ እርዳታ ለማድረስ የሚያስፈልገው ነዳጅ ከሌለን በሚሊዮኖች ለሚቆጠሩ ሰዎች ይራባሉ” ሲሉ ቢዝሊ ትዊት አድርገዋል።












