ከኤሌክትሪክ መኪና አምራቹ ኩባንያ ሕንጻ ላይ የወደቀ መኪና ሁለት ሰዎችን ገደለ

ታትሟል

ከቻይናው የኤሌክትሪክ መኪና አምራች ኩባንያ ኒዮ ዋና መሥሪያ ቤት ሕንጻ ላይ አንድ መኪና ወድቆ ሁለት ሰዎችን ገደለ።

ሻንጋይ ከሚገኘው የኒዮ ዋና መሥሪያ ቤት ሦስተኛ ፎቅ ላይ መኪና መውደቁን ተከትሎ ነው ሰዎቹ ለህልፈት የተዳረጉት።

ኒዮ የኤሌክትሪክ መኪና አምራች ሲሆን፣ ከሞቱት ሰዎች አንደኛው የድርጅቱ ተቀጣሪ ሲሆን ሌላኛው ደግሞ የኒዮ አጋር ድርጅት ሠራተኛ ናቸው ተብሏል።

ሟቾቹ መኪናው ሲወድቅ ውስጡ እንደነበሩ ተገልጿል።

ከመንግሥት አመራሮች ጋር በመጣመር ክስተቱን እየመረመረ እንደሚገኝ የኤሌክትሪክ መኪና አምራቹ ኒዮ አስታውቋል።

የዋና መሥሪያ ቤቱ ሦስተኛ ፎቅ መኪኖች ለዕይታ የሚቀርቡበት ሲሆን፣ መኪኖች ከመሸጣቸው በፊት የሚሞከሩትም በዚህ የሕንጻው ክፍል ነው።

መኪና አምራቹ ባወጣው መግለጫ “ከአገር ውስጥ ደኅንነት ጋር ድርጅታችን ተጣምሮ ስለ አደጋው መንስኤ ምርመራ ጀምሯል። እስካሁን ባገኘነው መረጃ ክስተቱ ድንገተኛ ነው። የተፈጠረውም በመኪናው ምክንያት አይደለም” ብሏል።

ለሟቾች ቤተሰቦች መጽናናትን የተመኘው ድርጅቱ፣ ቤተሰቦቻቸውን የሚደግፍ ቡድን እንዳቋቁመ አክሏል።

ኒዮ ባወጣው መግለጫ፣ አደጋው ከመኪናው ጋር የተያያዘ አይደለም ማለቱ ማኅበራዊ ሚዲያ ላይ ቁጣን ቀስቅሷል።

“ይህ መግለጫ የካፒታሊዝምን አደገኛነትን ያሳብቃል” ሲል አንድ የቻይና ማኅበራዊ ሚዲያ ዌቦ ተጠቃሚ ተናግሯል።

“ይህ አባባል ግድየለሽነታቸውን ነው የሚያሳየው። ሹፌሮች መኪኖችን እንዲሞክሩ እያደረጉ ክስተቱ ከመኪናው ጋር የማይገናኝ አደጋ ነው ይላሉ” ሲል ሌላ የዌቦ ተጠቃሚ ተችቷል።

ሌላ አስተያየት ሰጪ ደግሞ “አደጋ ነበር ወይስ አልነበረም የሚለውን መወሰን ያለበት የአገር ውስጥ ደኅንነት ቢሮ ነው” ብሏል።

መኪና አምራቹ መጀመሪያ ላይ የለጠፈውን መግለጫ አሻሽሎ ‘አደጋው የተከሰተው በመኪናው ምክንያት አይደለም’ የሚለውን አረፍተ ነገር በቅንፍ ውስጥ አስቀምጦታል።

ከዚያ በኋላ የተሰጡት አስተያየቶች “ነፍስ ይማር” የሚሉ ናቸው።

ኒዮ በኤሌክትሮኒክ ተሽከርካሪዎች ምርት ቻይና ውስጥ ግንባር ቀደም ከሚባሉት መካከል ይጠቀሳል።

ኩባንያው መኪኖችን በተደጋጋሚ ቻርጅ ማድረግ ለጉዞ መሰናክል እንዳይሆን ተለዋጭ ባትሪ በማዘጋጀትም ይታወቃል።

ሌላው የኤሌክትሪክ መኪና አምራች፣ የኤሎን መስክ ቴስላ ሻንጋይ ውስጥ ቅርንጫፍ አለው።

ኒዮ የቴስላ ተቀናቃኝ እንደሆነም ይታመናል።