በሩሲያ የአረጋውያን መንከባከቢያ ውስጥ በደረሰ የእሳት አደጋ ቢያንስ 20 ሰዎች ሞቱ

ታትሟል

በሩሲያዋ ግዛት ሳየቤሪያ ውስጥ በምትገኘው ኬሜሮቮ ከተማ በሚገኝ የአረጋውያን መንከባከቢያ ውስጥ በተነሳ እሳት ቢያንስ 20 ሰዎች መሞታቸውን ባለሥልጣናት ተናገሩ።

የእድሜ ባለጸጎቹ እንክብካቤ ያገኙበት የነበረው ከእንጨት የተገነባው ባለ ሁለት ፎቅ ሕንጻ የላይኛው ክፍል በእሳት በተያዘበት ጊዜ በአደጋው ከሞቱት በተጨማሪ ስድስት ሰዎች ላይ ጉዳት ደርሷል።

እሳት አደጋው የተነሳው ችግር በነበረበት የውሃ ማሞቂያ ምክንያት ሊሆን እንደሚችል የወጡ የመጀመሪያ ደረጃ ሪፖርቶች አመልክተዋል።

የሩሲያ የዜና አገልግሎት የሆነው ታስ እንደዘገበው ለአረጋውያን እንክብካቤ የሚደረግበት የግል መኖሪያ ቤት ፈቃድ ሳይኖረው የሚሠራ መሆኑን ባለሥልጣናት ተናግረዋል።

የእሳት አደጋው ከተከሰተ በኋላ በርካታ የእሳት አደጋ መከላከያ ባለሙያዎች ተሰማርተው እሳቱን ያጠፉት ቢሆንም፣ ቢያንስ 20 ሰዎች በእሳቱ ሳቢያ ለሞት ተዳርገዋል።

አደጋውን ተከትሎ የግዛቱ አስተዳዳሪ በተመሳሳይ የአረጋውያን መንከባከቢያ ማዕከላት ላይ ምርመራ እንደሚደረግ ተናግረዋል።

በለሥልጣናት እንዳሉት ለበርካታ ሰዎች ሞት ምክንያት በሆነው የእሳት አደጋ ዙሪያ የወንጀል ምርመራ ተጀምሯል።

የአካባቢው የእሳት አደጋ መከላከያ አገልግሎት ባለሥልጣን ለዜና አገልግሎቱ እንደተናገሩት፣ በመላዋ ሩሲያ በርካታ ሕገወጥ የአረጋውያን መንከባከቢያ ማዕከላት አሉ።

ጨምረውም መንከባከቢያዎቹ የግል መኖሪያ ቤቶች በመሆናቸው የእሳት አደጋ የደኅንነት ቁጥጥር አይደረግባቸውም፤ በዚህም ሳቢያ ለአደጋ የተጋለጡ ሊሆኑ እንደሚችሉ ተናግረዋል።

ከአራት ዓመት በፊት አሁን የእሳት አደጋ ተከስቶ በርካታ ሰዎችን በገደለባት ኬሜሮቮ ውስጥ በመዝናኛ ቦታ ላይ በተከሰተ እሳት 37 ህጻናትን ጨምሮ 60 ሰዎች ለሞት ተዳርገው ነበር።