ከአሜሪካ የውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት ከ1,000 በላይ ሠራተኞች ተቀነሱ

ታትሟል
የንባብ ጊዜ: 3 ደቂቃ

የትራምፕ አስተዳደር የፌደራል መንግሥቱን ሠራተኞች ቁጥር ለመቀነስ ባደረገው ጥረት ከ1,000 በላይ የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት ሠራተኞች ከስራ ተባረሩ።

የሠራተኞች ቅነሳው 1,107 ሲቪል ሰርቪስ እና 246 የውጭ አገልግሎት ሠራተኞችን ያካተተ መሆኑን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መሥርያ ቤቱ ለሠራተኞቹ አርብ ዕለት የላከው ደብዳቤ ያስረዳል።

ከ1,500 የሚበልጡ ሌሎች የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ሠራተኞች በዚህ ዓመት መጀመሪያ ላይ የፌዴራል መንግሥት ባደረገው መጠነ ሰፊ የመልሶ ማደራጀት ጥረት አካል ሆነው በፈቃደኝነት ሥራቸውን ለቅቀዋል።

የትራምፕ አስተዳደር እርምጃን የሚተቹ የጅምላ ቅነሳው ተቋሙ በሚሠራው ሥራ ላይ ተጽዕኖ እንደሚያሳድር በመጥቀስ ተከራክረዋል ።

በአሜሪካ የቢቢሲ አጋር የሆነው ሲቢኤስ ኒውስ እንደዘገበው በሥነ ሕዝብ ቢሮ፣ በስደተኞች እና ፍልሰት ቢሮ ውስጥ የሚገኙ ሁሉም የሲቪል ሰርቪስ ሠራተኞች ተሰናብተዋል።

ለአሜሪካ ውጭ ጉዳይ ቢሮ የአፍጋኒስታናውያን መልሶ ማቋቋሚያ ጽሕፈት ቤት አስተባባሪ በመሆን የሚሰሩ እንዲሁ ከሥራቸው ከተሰናበቱት መካከል ናቸው።

በማኅበራዊ ድረ ገጾች ላይ የተጋሩ ቪዲዮዎች የመስርያ ቤቱ ባልደረቦች ንብረታቸውን ይዘው ሲወጡ ያሳያሉ።

ሌሎች ሠራተኞች የቀድሞ ባልደረቦቻቸውን በማጨብጨብ ሲያበረታቱ እና እርስ በእርስ ሲተቃቀፉ ታይተዋል።

ከሕንፃው ውጭ ተቃዋሚዎች "የአሜሪካ ዲፕሎማቶች እናመሰግናለን" እና "ሁላችንም የተሻለ ይገባናል" የሚሉ መፈክሮችን ይዘው ተገኝተዋል።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ማርኮ ሩቢዮ ሐሙስ ዕለት በማሌዥያ በነበሩበት ወቅት "ሰዎችን ለማባረር የመሞከር ውጤት አይደለም" ብለዋል ።

"ቢሮውን ከተዘጋ ግን እነዚያን የሥራ መደቦች አያስፈልጉም። ከእነዚህ ውስጥ አንዳንዶቹ የተዘጉ ሥራዎች እንጂ ሰዎች እንዳልሆኑ ተረዱ" ብለዋል።

በሴኔቱ የውጭ ግንኙነት ኮሚቴ ውስጥ ያሉ ዲሞክራቶች "በመቶዎች የሚቆጠሩ የሲቪል ሰርቪስ እና የውጭ አገልግሎት ባልደረቦችን ከውጭ ጉዳይ ለማባረር መወሰኑ ብሄራዊ ደህንነታችንን የሚጎዳ ነው" ሲሉ መግለጫ አውጥተዋል።

"የእኛ መንግሥት በእያንዳንዱ የታክስ ገንዘብ ላይ ያለውን ተጽእኖ ከፍ ለማድረግ ሊከተላቸው የሚችላቸው ማሻሻያዎች ቢኖሩም ይህ ግን አንዱ አይደለም" ሲሉ ሴናተሮች በመግለጫቸው ላይ ተናግረዋል።

"በጅምላ እና ያለ ምንም ልዩነት የተደረገ ማባረር፤ ከኤሎን መስክ የከሸፈው የዶጅ ጥረት የቀረ ውርስ፣ ወጪ ቆጣቢ በሆነ መንገድ መንግሥታችንን ለአሜሪካ ሕዝብ የማገልገል አቅሙን ያዳክማል" ብለዋል።

ቅነሳው የመጣው ከፍተኛው ፍርድ ቤት የትራምፕ አስተዳደር የፌደራል የሰው ኃይልን ለመቀነስ ያቀደውን እቅድ ሊቀጥል ይችላል ሲል ከወሰነ ከቀናት በኋላ ነው።

በጥር ወር መምሪያው በፍቃደኝነት እና በአስገዳጅ ሁኔታ የሰው ኃይሉን በ18 በመቶ ለመቀነስ ያለውን ፍላጎት ለኮንግረስ አሳውቆ ነበር።

መምሪያው ከ18,700 በላይ ሠራተኞች እንዳሉት ገልጿል።

የሠራተኞች ቅነሳው የመጣው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ በምርጫ ቅስቀሳ ወቅት የመንግሥትን ወጪ ለመቀነስ ቃል መግባታቸውን ተከትሎ ነው።

በዚህ ወር መጀመሪያ ላይ የአሜሪካ ዓለም አቀፍ ልማት ኤጀንሲ (ዩኤስኤአይዲ) በትራምፕ አስተዳደር መመሪያ መሰረት በይፋ ሥራውን አቁሟል።

ከ80 በመቶ በላይ የኤጀንሲው ሥራዎች እስከ መጋቢት ወር ድረስ ተቋርጠዋል፤ ከሐምሌ 1 ጀምሮ ቀሪው ሥራ በውጭ ጉዳይ መስርያ ቤቱ በመደበኛነት ተካትቷል።