አርሰናል ከማንቸስተር ሲቲ፡ በውጥረት የተሞላውን ፍልሚያን ማን ይረታል?

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ከውድድር ዘመኑ ትልቅ ፍልሚያዎች አንዱ የተባለው አርሰናል ከሲቲ የሚያደርጉት ጨዋታ እሑድ ምሽት ይደረጋል።
ማንቸስተር ሲቲ ከአርሰናል ባለፈው መስከረም በኢቲሀድ ተገናኝተው ነበር።
አርሰናል ጨዋታውን እየመራ ሳለ አንድ ተጫዋች በቀይ ወጣበት።
ከዚያ በኋላ በነበሩት ደቂቃዎች ሲቲ ኳስ ይዞ ለማግባት ሲጥር አርሰናል ሲከላከል ቆይታ ጨዋታው ሊጠናቀቅ ደቂቃዎች ሲቀሩት ጆን ስቶንስ ባስቆጠረው ጎል ፍልሚያ 2-2 ተገባደደ።
ሲቲዎች ጎል ማስቆጠራቸውን ተከትሎ ደስታቸውን ሲገልፁ ኧርሊንግ ሀላንድ ጋብርኤልን በኳስ መታው።
የጨዋታው መጠናቀቂያ ፊሽካ ከተነፋ በኋላ ሀላንድ ወደ አርሰናሉ አሰልጣኝ ሚኬል አርቴታ ሄዶ 'ስተይ ሀምብል' አሊያም በግርድፉ 'ፀባይ ግዛ' ሲል ተናገረው።
ይህ ጨዋታ በክስተት የተሞላ ነበር። ስቶንስ እና ካይል ዎከር መድፈኞቹ የሚጠቀሙት መንገድ 'ፀሊም ጥበብ' ነው ሲሉ ሐሳባቸውን ሰጡ።
በዚህ ጨዋታ ጉዳት ያጋጠመው የሲቲ የመሐል መስመር ደጀን ሮድሪ በያዝነው የውድድር ዘመን ወደ ሜዳ አይመለስም።
ምንም እንኳ ይህ ጨዋታ የተከናወነው በውድድር ዘመኑ መባቻ ላይ ቢሆንም ፍልሚያው እልህ የተሞላበት እና ለገለልተኛ ተመልካች አጓጊ የሚባል ነበር።
እነሆ ከ133 ቀናት በኋላ ድጋሚ ይገናኛሉ። ምንም እንኳ አሁን ሲቲ በነጥብ ከአርሰናል ዝቅ ብሎ ቢገኝም በመጀመሪያው ዙር የነበረው ውጥረት እንደሚቀጥል ይጠበቃል።
ያለፉትን አራት የእንግሊዝ ፕሪሚዬር ሊግ ዋንጫ ያነሳው ሲቲ ሁለት ጊዜ ዋንጫውን ከአርሰናል ጉሮሮ ነጥቋል።
በያዝነው የውድድር ዘመን ደካማ አቋም ላይ የሚገኙት ሲቲዎች አሰልጣኝ ፔፕ ጉዋርዲዮላ ዘንድሮ ዋንጫ መብላት የሚታሰብ አይደለም ብሏል።
ባለፈው የአውሮፓውያኑ ዓመት መገባደጃ በሁሉም ውድድሮች ከ13 ጨዋታዎች አንድ ጊዜ ብቻ ማሸነፋቸው ይታወሳል።
ሲቲ ሙሉ በሙሉ ወደ ቀደም አቋሙ ባይመለስም ካለፉት አምስት ጨዋታዎች 13 ነጥብ መሰብሰብ ችሏል።
ሲቲ ከመሪው ሊቨርፑል 15 ነጥቦች ዝቅ ብሎ ይገኛል።
አርሰናል ከሊቨርፑል 9 ነጥብ ዝቅ ብለው ተቀምጠዋል። ከሲቲ ጋር በሚያደርጉት ጨዋታ ማሸነፍ ካልቻሉ ለዋንጫው የመፎካከር ዕድላቸው እየመነመነ እንደሚመጣ ያውቁታል።
እኒህ ተደማምረው በኤሜሬትስ ስታድየም ውጥረት የተሞላበት ጨዋታ ልንመለከት እንደምንችል ይጠቁማሉ።
በ2019 የአርሰናል አሰልጣኝ ሆነው ከመሾሙ በፊት የጉዋርዲዮላ ምክትል የነበረው አርቴታ ከፔፕ ጋር ያለው ግንኙት አሁንም ሰላማዊ እንደሆነ ተናግሯል።
ባለፈው መስከረም የተፈጠረው ግርግር ሜዳ ላይ የሚከሰተው ነው ያለው አርቴታ "እኔም ተጫዋች ነበርኩ አውቀዋለሁ" ሲሉ አጣጥሏል።
የቢቢሲ ስፖርት ተንታኙ ክሪስ ሰቱን አርሰናል ሲቲን ይረታል ሲል ግምቱን አስቀምጧል።
ከምሽቱ ተጠባቂ ጨዋታ ቀደም ብሎ 11፡00 ብሬንትፈርድ ከቶተንሀም፤ ማንቸስተር ዩናይትድ ከክሪስታል ፓላስ ይጫወታሉ።
ቅዳሜ ምሽት ቦርንመዝን የረታው ሊቨርፑል ሊጉን በ56 ነጥብ ይመራል። አርሰናል እና ኖቲንግሀም ፎረስት በጎል ልዩነት በእኩል 47 ነጥብ ሁለተኛ እና ሶስተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጠዋል። ሲቲ በ41 ነጥብ አራተኛ ደረጃ ላይ ይገኛል።












