ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
የሩሲያ ጦር ለወራት ሊቆጣጠራት እየሞከረ ባለችው ከተማ ሁኔታዎች መክፋታቸው ተነገረ
በምሥራቃዊ ግንባር በባኽሙት ከተማ ያለው ሁኔታ በጣም አስቸጋሪ እየሆነ መምጣቱን የዩክሬን ፕሬዝዳንት ቮሎዲሚር ዜሌንስኪ ተናገሩ።
የሩሲያ ኃይሎች ከስድስት ወራት በላይ ለሆነ ጊዜ ከተማዋን ለመቆጣጠር ጥረት ሲያደርጉ ቆይተዋል።
ፕሬዝዳንት ዜሌንስኪ “ጠላቶቻችን ይዞታችንን ለመጠበቅ የምንጠቀምበትን ሁሉንም ነገር እያወደሙት ነው” ብለዋል።
ፕሬዝዳንቱ ይህን ያሉት የአሜሪካ የገንዘብ ሚኒስትር ጃኔት የለን ሰኞ ዕለት በኪዬቭ ከተማ ባደረጉት ጉብኝት ቻይና ሩሲያን ማስታጠቋን እንድታቆም ማስጠንቀቃቸውን ተከትሎ ነው።
ከአንድ ዓመት በፊት ሩሲያ ዩክሬንን ከወረረች ጀምሮ በከፊል በሩሲያ እና ተገንጣይ አጋሮቿ ቁጥጥር ሥር በሚገኘው የዩክሬን ዶኔስክ ክልል ውስጥ በምትገኘው ባኽሙት ከተማ ከባድ ውጊያ እየተካሄደ ነው።
በቅርቡም የሩሲያ ኃይሎች የኢንዱስትሪ ከተማዋን ለመያዝ ከባድ ውጊያ እያካሄዱ ሲሆን ወታደሮቿም ገዢ ቦታዎችን መያዛቸው ተሰምቷል።
ራስ ገዝ በሆነችው የዶኔስክ ሕዝቦች ሪፐብሊክ የተገንጣይ ቡድኑ መሪ የሆኑት ዴኒስ ፑሺሊን “ወደ ከተማዋ የሚወስዱ ሁሉም መንገዶች በሩሲያ ቁጥጥር ሥር ናቸው” ብለዋል።
ፕሬዝዳንት ዜሌንስኪ በአካባቢው ስላለው ሁኔታ ምሽት ላይ ባደረጉት ንግግር፣ ሩሲያ በፈጸመችው ጥቃት በባኽሙት ላይ ጉዳት እየደረሰ መሆኑን ገልጸው፣ እያንዳንዱ ሰው አካባቢውን ለመከላከል ለሚያሳየው ጀግንነት ምስጋና አቅርበዋል።
ፕሬዝዳንቱ የአገራቸውን ግዛት ከሩሲያ ወረራ ለመጠበቅ ዘመናዊ የሆኑ ተዋጊ አውሮፕላኖች ድጋፍ እንዲደረግላቸውም በድጋሚ ጥሪ አቅርበዋል።
የአሜሪካ የገንዘብ ሚኒስትር ጃኔት የለን በኪዬቭ ባደረጉት ድንገተኛ ጉብኝት ወቅት፣ በቅርቡ ለዩክሬን የ1.25 ቢሊዮን ዶላር ድጋፍ መደረጉን አስታውቀዋል።
ባለፈው ሳምንት የአሜሪካው ፕሬዝደንት ጆ ባይደን በኪዬቩ ጉብኝታቸው ወቅት ዩክሬን በጦርነቱ እስከምታሸንፍ ድረስ ዋሽንግተን ከጎኗ እንደምትቆም ያስተላለፉትን መልዕክት ሚኒስትሯም ደግመውታል።
የለን ፣የሩሲያ ምጣኔ ሃብት ምዕራባውያን በተጣሉት ማዕቀብ እስካሁን አልተገታም ቢባልም ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተዳከመ ይሄዳል ብለው እንደሚጠብቁ ለሲኤንኤን ተናግረዋል።
ሚኒስትሯ ጨምረውም ሩሲያ በዩክሬን ላይ በፈፀመችው ጥቃት የወደሙ ወታደራዊ መሣሪያዎቿን ለመተካት ያላት አቅምም "ቀስ በቀስ አደጋ ላይ እየወደቀ ነው" ሲሉም፣ በቻይና ለሩሲያ የጦር መሣሪያ ለማቅረብ የሚደረግ ማንኛውም እርምጃ "ከባድ" መዘዝ እንደሚያስከትል አስጠንቅቀዋል።
"በዚህ ጦርነት ሩሲያ ወታደራዊ መሣሪያ እንዳታገኝ ለማድረግ ያስቀመጥነውን ማዕቀብ የትኛውም አገር የሚያደርገውን ስልታዊ ጥሰቶችን እንደማንቀበል ግልፅ አድርገናል" ሲሉም አስታውሰዋል።
እነዚህን ማዕቀቦችን መጣስ የሚያስከትለውን መዘዝ በተመለከተ ለቻይና ኩባንያዎችና የፋይናንስ ተቋማት ግልጽ ማድረጋቸውንም ሚኒስትሯ ተናግረዋል።
ባለፈው ሳምንት የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት ኃላፊ አንቶኒ ብሊንከን ቻይና ለሩሲያ የጦር መሣሪያ እና ጥይቶችን ለማቅረብ እያሰበች እንደሆነ ደርሰንበታል ብለው ነበር።
ቤይጂንግ ግን የቀረበባትን ክስ ተቃውማለች።
ይሁን እንጂ በርካቶች ባለፈው ሳምንት የቻይና ከፍተኛ ዲፕሎማት ዋንግ ይ እና የሩሲያ ፕሬዚደንት ቭላድሚር ፑቲን በሞስኮ ያደረጉት ውይይት ቻይና ከሩሲያ ጋር ያላትን የጠበቀ ግንኙነት ማሳያነት ተመልክተውታል።