ሩሲያ በዩክሬን ጦርነት ተጠያቂ እንዳልሆነች ፕሬዚዳንት ፑቲን ተናገሩ

የፎቶው ባለመብት, Reuters
የሩሲያው ፕሬዚዳንት ቭላድሚር ፑቲን በዩክሬኑ ጦርነት አገራቸው ተጠያቂ እንዳልሆነች ተናገሩ።
ሁለቱም ሃገራት “አሳዛኝ ሁኔታን እየተጋሩም” ነው ብለዋል ፕሬዚዳንቱ
የሩሲያው ፕሬዝዳንት ከከፍተኛ ወታደራዊ ባለስልጣናት ጋር በመሆን በአገሪቱ ቴሌቭዥን ጣቢያ ባደረጉት ንግግር ዩክሬንን እንደ "ወንድማዊ ሃገር" መመልከት እንደሚቀጥሉም ነው የገለጹት።
ጦርነቱ "የሶስተኛ ሀገራት ፖሊሲ ውጤት" እንጂ የሩሲያ ፖሊሲ አይደለም ሲሉም አቋማቸውን አስረድተዋል።
ከዚህ ቀደምም ለጦርነቱ መነሳት መንስኤው የምዕራባውን መስፋፋት እንደሆነ ከሩሲያ በኩል በተደጋጋሚ ሲጠቀስ ይሰማል።
ፕሬዚዳንት ፑቲን ዩክሬንን ጨምሮ የሶቪየት ህብረት አባል የነበሩ ሃገራት ምዕራባውያን ሃገራት በፕሮፓጋንዳቸው ቀይረዋቸዋል ብለዋል።
“ለዓመታት ብድርና ርካሽ ኃይል በመለገስ ከዩክሬን ጋር ጥሩ ጉርብትና ለመፍጠር ሞከርን፤ ግን አልሰራም” ሲሉም አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።
“እኛ የምንወቀስበትም ሆነ የምንከሰስበት ምንም ነገር የለም።ሁልጊዜም ዩክሬናውያንን እንደ ወንድም ህዝቦች ነው የምናያቸው እና አሁንም እንደዛ ይመስለኛል” ብለዋል
"አሁን እየሆነ ያለው አሳዛኝ ነገር ነው። ነገር ግን የእኛ ጥፋት አይደለም." ሲሉም አጽንኦት ሰጥተዋል።
ፕሬዚዳንቱ ንግግራቸውን በሚያደርጉበት ወቅትም ወታደራዊ ባለስልጣናቱ በመጪው የአውሮፓውያኑ አዲስ ዓመት ሃገራቸው የጀመረችውን “ልዩ ወታደራዊ ዘመቻ” እንደምትቀጥልም ቃል ገብተዋል።
ፕሬዝዳንት ፑቲን አክለውም ሩሲያ ለዚህ ዘመቻ የምታወጣው የገንዘብ መጠን ገደብ እንደሌለው ተናግረዋል።
የመከላከያ ሚኒስትሩ ሰርጌይ ሾይጉ በበኩላቸው አስገዳጅ የሆነውን የሩሲያ ወታደራዊ አገልግሎት የዕድሜ ገደብ ለማስፋትም ሐሳብ አቅርበዋል።
በአሁኑ ወቅት ባለው የሩሲያ ህግ መስረት ከ18-27 ዕድሜያቸው የሆኑ ሩሲያውያን ለግዳጅ የውትድርና አገልግሎት ሊጠሩ ይችላሉ ። ሆኖም የመከላከያ ሚኒስትሩ ያቀረቡት ዕቅድ ከ21-30 ዕድሜያቸው የሆኑ ዜጎችን እንዲያጠቃልል ነው።
ሩሲያ በተቆጣጠረቻቸው ሁለት የዩክሬን ወደብ ከተሞች በርዲያንስክ እና ማሪዮፖል ላይ የጦር ሰፈር ለሟቋቋም መታቀዱን ሚኒስትሩ ገልጸዋል።
በአሁኑ ወቅት የዩክሬኑ ፕሬዚዳንት ቮልድሚር ዘለንስኪ ጦርነቱ ከተጀመረ በኋላ የመጀመሪያውን የዋሽንግተን ጉብኝት እያደረጉ ባለበትም ወቅት ነው መግለጫው የተሰማው።












