ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
እስራኤል በተደጋጋሚ ያመለጣትን የፍልስጥኤም ታጣቂ ቡድን መሪን ገደለች
የፍልስጤማዋውያን ታጣቂ ቡድን መሪ እስራኤል በወረራ በያዘችው ዌስት ባንክ ውስጥ ዛሬ በፈጸመችው ጥቃት መገደሉ ተነገረ።
በጥቃቱ የ‘አል አቅሳ ሰማዕታት ብርጌድ’ በመባል የሚታወቀው ታጣቂ ቡድን አካባቢያዊ መሪ የሆነው የ26 ዓመቱ ኢብራሂም አል-ናቡልሲን ጨምሮ ሁለት ሌሎች ሰዎች የእስራኤል ኃይሎች ናብሉስ ውስጥ በአንድ ቤት ላይ በፈጸሙት ጥቃት ተገድለዋል።
የፍልስጥኤም ቀይ ጨረቃ ማኅበር እንዳለው በጥቃቱ ቢያንስ 40 ሰዎች ቆስለዋል።
የ‘አል አቅሳ ሰማዕታት ብርጌድ’ ዌስት ባንክን የሚቆጣጠረው ፋታህ ከተባለው ንቅናቄ ጋር ግንኙነት ያለው የታጣቂዎች ቡድን ነው።
አስራኤል አሁን የተገደለውን ባቡለሲን በዌስት ባንክ በዜጎቿ ላይ ለተፈጸሙ ተከታታይ ጥቃቶች ተጠያቂ የምታደርገው ሲሆን፣ ባለፈው የካቲት ወር ሦስት አጋሮቹን ስትገድል ለማምለጥ ችሎ ነበር።
ዛሬ ማክሰኞ የእስራኤል ወታደሮች ናብሉሲን ከቤቱ ለማስወጣት በቤቱ ላይ ከትከሻ ላይ የሚቀነጨፉ ሮኬቶችን መተኮሳቸው ተነግሯል።
በቤቱ አቅራቢያ እና በከተማዋ ውስጥ በተደረገ የተኩስ ልውውጥ በርካታ ፍልስጤማውያን ቆስለዋል። ከእነዚህም ውስጥ አራቱ በአስጊ ሁኔታ ተጎድተዋል።
በእስራኤል ወታደሮች ላይ የደረሰ ጉዳት የለም ተብሏል።
የእስራኤል መገናኛ ብዙኃን እንደዘገቡት የአልአቅሳ ሰማዕታት ብርጌድ ከፍልስጥኤም እስላማዊ ጂሃድ ቡድን ጋር በመሆን በዌስት ባንክ እስራኤላውያንን ኢላማ ያደረጉ ጥቃቶች ፈጽመዋል።
በቅርቡ የአስራኤል ወታደሮች በዋናነት የፍልስጥኤም እስላማዊ ጂሃድ ቡድን ታጣቂዎችን ለመያዝ በዌስት ባንክ ውስጥ በርካታ ጥቃቶችን ፈጽመዋል።
በዚህም ባሲም ሳዲቅ የተባለው ከፍተኛ የቡድኑ መሪን የያዘች ሲሆን ከዚሁ ጋር ተያይዞ ባለፈው ቅዳሜ እና እሁድ በጋዛ ሰርጥ ላይ እስራኤል በፈጸመቻቸው የአየር ጥቃቶች፣ ሁለት ከፍተኛ የታጣቂ ቡድኑ አዛዦችን ጨምሮ ቢያንስ 44 ፍልስጤማውያን ተገድለዋል።
የፍልስጥኤም ታጣቂዎችም በበኩላቸው የእሰራኤል ከተሞችን ቴል አቪቭና ኢየሩሳሌምን ኢላማ ያደረጉ በመቶዎች የሚቆጠሩ ሮኬቶችን ከጋዛ ሰርጥ ተኩሰዋል። ነገር ግን እስራኤል ባላት የሚሳኤል መከላከያ ሥርዓት ሮኬቶቹ ጉዳት ሳያደርሱ ከሽፈዋል።
ግብፅ ጣልቃ ገብታ በማሸማገል በአስራኤልና በፍልስጥኤም ቡድኖች መካከል ተኩስ አቁም እንዲደርግ አስችላ ነበር።
አስራኤል በዜጎቿ እና በወታደሮች ላይ ጥቃት ፈጽሟል በሚል ዛሬ የተገደለውን ኢብራሂም አል ናቡልሲን ለመያዝ ከአንድ ዓመት በላይ ስታድነው ቆይታለች። ናቡልሲ በፍልስጤማ ወጣቶች ዘንድ ታዋቂ እና በቲክቶክ ላይ ከፍተኛ ተከታይ ያለው ወጣት ነው።
በተደጋጋሚ ተደርሶበት ከመያዝና ከግድያ ለማምለጥ በመቻሉ እስራኤል ከፍተኛ ትኩረት የሰጠችው ኢላማዋ ሆኖ ቆይቷል።
የአል ናብሉሲ አስከሬን በፍልስጥኤም ሰንደቅ አላማ ተሸፍኖ የሚያሳዩ ፎቶዎች በማኅበራዊ ሚዲያዎች ላይ በስፋት እየተሰራጩ ሲሆን፣ በዚህ ግድያ ምክንያት በራማላህ እና ሔብሮን ውስጥ ግጭቶች ተቀስቅሰዋል። ቤተልሔም ውስጥ ደግሞ አጠቃላይ አድማ ተጠርቷል።