ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
እስራኤል-ጋዛ፡ በግብጽ አሸማጋይነት የተደረሰው የተኩስ አቁም ተግባራዊ ሆነ
ለሦስት ቀናት በዘለቀውና ቢያንስ 43 ሰዎች የሞቱበትን ግጭት ተከትሎ በእስራኤል እና በፍልስጤም ታጣቂዎች መካከል የተኩስ አቁም ስምምነት ተግባራዊ ሆነ።
በግብጽ አሸማጋይነት የተደረሰው ስምምነት ከእኩለ ለሊት ጀምሮ ተግባራዊ መደረጉን የፍልስጤም እስላማዊ ጂሃድ (ፒአይጄ) ተናግረዋል።
የእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር ያይር ላፒድ ጽህፈት ቤት የተኩስ አቁም መደረጉን አረጋግጧል።
የሰሞኑ ግጭት እአአ 2021 ለ11 ቀናት ከዘለቀው ግጭት በኋላ በእስራኤል እና በጋዛ መካከል ከተፈጠረው ከባዱ ነው ተብሏል።
ስምምነቱ ተግባራዊ ከመደረጉ በፊት ለተተኮሱ ሮኬቶች ምላሽ ነው በሚል የእስራኤል ወታደራዊ ኃይል በጋዛ የእስልምና ጂሃድ ዒላማዎችን እየመታ መሆኑን አረጋግጧል። የአገሪቱ መገናኛ ብዙሃን ከስምምነቱ መተግበር በኋላ ከጋዛ የተወሰኑ ሮኬቶች መተኮሳቸውን ዘግበዋል።
ኋላም የተኩስ አቁም ስምምነቱ ተግባራዊ እየሆነ ይመስላል።
በታጣቂ ቡድን ለተፈጠረው ስጋት የእስራኤል ጦር በጋዛ ሰርጥ በሚገኙ ቦታዎች ላይ የአጸፋ ምላሽ መስጠት መጀመሩን ገልጾ ነበር። ይህም እስራኤል በዌስት ባንክ ከፍተኛ የፒአይጄ አባል በቁጥጥር ስር ካዋለች በኋላ የተፈጠረውን ውጥረት ተከትሎ የተከሰተ ነበር።
እሑድ ማምሻውን የፍልስጤም የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር እንዳስታወቀው ሕይወታቸው ካለፉት 43 ሰዎች መካከል 15ቱ ህጻናት መሆናቸውን መረጋገጡን አስታውቋል። የጋዛ ጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ለፍልስጤማውያን ሞት እና ከ300 በላይ ለሚሆኑት ሰዎች መቁሰል "የእስራኤል ጥቃትን" ተጠያቂ አድርጓል።
የፒአይጄ አዛዥ ሁለተኛ ሰው የሆነው ካሊድ መንሱርን ጨምሮ በእስራኤል ጥቃት የተገደሉትን የቀብር ስነ-ስርዓት ለማከናወን እሑድ ዕለት ከፍተኛ ህዝብ ተሰብስቧል።
የጤና ባለስልጣናት ሆስፒታሎች ለተጨማሪ ሁለት ቀናት ጄነሬተሮችን ለማንቀሳቀስ የሚያስችል ነዳጅ ብቻ እንዳላቸው ማስጠንቀቃቸውን እና በጋዛ የሰብዓዊ ድጋፍ ለማድረስ ያለው ስጋት ከተገለጸ በኋላ ነው የተኩስ አቁም ስምምነቱ የተደረሰው።
የእስልምና ጂሃድ ቃል አቀባይ ታሪቅ ሰልሚ “እስራኤል በሕዝባችን ላይ የምታደርሰውን ጥቃት ለማስቆም በግልጽ የተደረገውን ጥረት እናደንቃለን“ ብለዋል።
እስራኤል የተኩስ አቁም ስምምነቱ ከተጣሰ "ጠንካራ ምላሽ የመስጠት መብቴን እጠቀማለሁ" ብላለች።
በጋዛ ከደረሰው ሞት የተወሰነው የተፈጸመው በፒአይጄ ታጣቂዎች ነው ስትል እስራኤል ትከሳለች።
የሰሞኑ ግጭት የተቀሰቀሰው እስራኤል የፒአይጄ ኃላፊ እንደሆነ የሚነገርለትን ባሴም ሳዲን ሰኞ ምሽት ዌስት ባንክ ውስጥ በቁጥጥር ስር ማዋሏን ተከትሎ ነው።
በእስራኤላውያን አረቦች እና በፍልስጤማውያን ጥቃት 17 እስራኤላውያን እና ሁለት ዩክሬናውያን ሕይወታቸውን ካጡ በኋላ ነው የእስር ዘመቻው በጄኒን አካባቢ የተጀመረው።
በጋዛ ውስጥ ከሚንቀሳቀሱት ጠንካራ ታጣቂ ቡድኖች አንዱ ፒአይጄ ነው። ቡድኑ በኢራን የሚደገፍ ሲሆን ዋና መስሪያ ቤቱን በሶሪያ ርዕሰ መዲና ደማስቆ ይገኛል።
በእስራኤል ላይ ሮኬት ማስወንጨፍን ጨምሮ ለበርካታ ጥቃቶች ተጠያቂ ነው።
እአአ 2019 እስራኤል ላይ ጥቃት ለመፈጸም አቅዶ ነበር ያለችውን የፒአይጄን አዛዥ መግደሏን ተከትሎ በእስራኤል እና በቡድኑ መካከል ለአምስት ቀናት የዘለቀ ግጭት ተካሂዷል።
በግጭቱ 34 ፍልስጤማውያን ሲሞቱ 111 ቆስለዋል። 63 እስራኤላውያን ደግሞ የህክምና ድጋፍ አስፈልጓቸዋል።
ከተገደሉት ፍልስጤማውያን መካከል ሮኬቶችን ለማስወንጨፍ በዝግጅት ላይ የነበሩትን ጨምሮ 25 ያህሉ ታጣቂዎች ናቸው ስትል እስራኤል ትገልጻለች።