አበረታች መድኃኒት የሚጠቀሙ አትሌቶቿ በርካታ ቢሆኑም “ኬንያ ለጥፋተኞች ከለላ አትሰጥም” ሴባስቲያን ኮ

ታትሟል

በስፖርቱ ሕገ ወጥ የሚባሉ አበረታች መድኃኒቶች ተወዳዳሪዎቿ እንዲጠቀሙ ኬንያ ቢያንስ በመንግሥት ደረጃ “አልደገፈችም” ሲሉ የዓለም አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ፕሬዝዳንት መሰከሩ።

ኬንያን እየጎበኙ ያሉት ፕሬዝዳንቱ ሎርድ ሴባስቲያን ኮ፣ ይህ ኬንያ የተወነጀለችበት የአበረታች መድኃኒት ጉዳይ ቢያንስ እንደ ሩሲያ የመንግሥት እጅ የለበትም ሲሉ ተናግረዋል።

ኬንያ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ከአበረታች መድኃኒቶች ጋር በተያያዘ ስሟ በዓለም መድረክ እየጎደፈ መጥቷል።

ኬንያ እንደ ሩሲያ ባይሆንም በዚህ የአበረታች መድኃኒት ጉዳይ ስሟ “አስጊ ደረጃ” ላይ ካሉ አገራት ጋር ተመዝግቧል።

ኬንያ በዚህ ረገድ በዓለም አቀፉ ፌዴሬሽን ብትወገዝም ስፖርቱን የሚያስተዳድረውን ተቋም በመንቀፍ ረገድ ተደጋጋሚ የገለልተኝነት ጥያቄ የሚነሳበትን የዓለም አትሌቲክስ ፌዴሬሽንን በማውገዝ ከሩሲያ ጋር አልተሰለፈችም።

ሩሲያ ከፈረንጆቹ 2016 ጀምሮ በተደጋጋሚ ስፖርተኞቿ አበረታች መድኃኒት ወስደው በመገኘታቸው እና ይህም እየሆነ ያለው በመንግሥት ጭምር በታገዘ መንገድ መሆኑ ስለተደረሰበት ከስፖርቱ ስትገለል ቆይታለች።

ይህን መገለል ተከትሎ ሩሲያ ከፌዴሬሽኑ ጋር ከፍተኛ ውዝግብ ውስጥ ገብታ ነበር።

ሩሲያ ስሟ ከአበረታች መድኃኒቶች ጋር በስፋት ይነሳ እንጂ አትሌቲክስን በተመለከተ ግን ኬንያን የሚስተካከል የለም።

ከስፖርቱ ከታገዱት 40 ከመቶ የሚሆኑት የኬንያ ስፖርተኞች ናቸው።

“ኬንያን እንደ ሩሲያ አይደለም የምናያት፤ የኬንያ መንግሥት ችግሩን ለመቅረፍ ይጥራል” ሲሉ ፕሬዝዳንት ኮይ በናይሮቢ ለጋዜጠኞች ተናግረዋል።

“ኬንያ በፍጹም ከሩሲያ ጋር ስሟ ሊነሳ አይገባም” ሲሉም አገሪቱ ስሟን ለማጽዳት እያደረገች ያለችውን ጥረት አሞካሽተዋል።

በአንጻሩ ፕሬዝዳንቱ ሩሲያ እነዚህን የአበራታች መድኃኒቶች በማበረታታት እንዲሁም ለሚወስዱ ስፖርተኞች ከለላ በመስጠት ከሰዋል።

ኬንያ ግን ከእንዲህ ዓይነቱ ተግባር ንጹህ እንደሆነች መስክረዋል።

የኬንያ የስፖርት ሚኒስትር አባዱ ናምዋምባ በበኩላቸው ይህን የአበረታች መድኃኒትን ጉዳይ ለመዋጋት 25 ሚሊዮን ዶላር ለሚቀጥሉት አምስት ዓመታት እንደተመደበ አውስተዋል።

ይህ ብቻም ሳይሆን አበረታች መድኃኒት በስፖርት ውድድሮች መጠቀም የሚያሳስር ወንጀል እንዲሆን ለማድረግ እየተሰራ ነው ብለዋል።

የዓለም አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ፕሬዝዳንት ሴባስቲያን ኮ የአዲስ ዓመት ጉብኝታቸውን ከኬንያ የጀመሩ ሲሆን ከአገሪቱ ፕሬዝዳንት ዊሊያም ሩቶ ጋር መክረዋል።