ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ሩሲያ ምግብ ለሰሜን ኮሪያ ሰጥታ በምላሹ ጦር መሳሪያ ልትቀበል መሆኑን አሜሪካ ገለጸች
ሩሲያ ምግብ በጦር መሣሪያ ለመለወጥ ልዑካን ቡድን ወደ ሰሜን ኮሪያ ልትልክ መሆኗን የአሜሪካ ብሔራዊ ደኅነንት ቃል አቀባይ ጆን ኪርቢ ተናገሩ።
ቃል አቀባዩ በሰሜን ኮሪያ እና በሩሲያ መካከል የሚደረግ ማንኛውም የጦር መሣሪያ ስምምነት የተባበሩት መንግሥታትን የጸጥታ ምክር ቤት ውሳኔዎችን ይጥሳል ብለዋል።
አሜሪካ ከዚህ ቀደም ሰሜን ኮሪያ በዩክሬን ለሚገኘው የሩሲያ ጦር እና ለሩሲያ ተቀጣሪ ዋግነር ግሩፕ መሣሪያ ታቀርባለች የሚል ክስ አቅርባ ነበር።
ፒዮንግያንግ ግን የቀረበባትን ክስ ውድቅ አድርገዋለች።
የደኅንነት ቃል አቀባዩ በሰጡት መግለጫ ሩሲያ እና ሰሜን ኮሪያ ስለሚያደርጉት ስምምነት አሜሪካ አዲስ መረጃ አላት ብለዋል።
“ሩሲያ በምግብ ጥይት ለመለወጥ ወደ ሰሜን ኮሪያ ልዑክ ልትልክ እንደሆነ አውቀናል” ብለዋል።
ቃል አቀባዩ ጨምረውም አሜሪካ ሁኔታውን እና የተባለውን ስምምነት በአንክሮ እየተከታተለች እንደሆነም ገልጸዋል።
ሰሜን ኮሪያ በዓለም ላይ ድሃ ከሆኑ አገሮች መካከል አንዷ ስትሆን እንደ ከአወሮፓውያኑ 1990 አጋማሽ እስከ መጨረሻው ድረስ የተከሰተውን የከፋ ረሃብን ጨምሮ ለአስርት ዓመታት ከፍተኛ የሆነ የምግብ እጥረት አጋጥሟታል።
የካቲት ወር ላይም ባለሙያዎች በዓለም ላይ አምባገነን ከሆኑ መንግሥታት አንዱ የሆነውን የሰሜን ኮሪያ መንግሥት በአየር ንብረት ለውጥ፣ ጥብቅ በሆነ የድንበር ቁጥጥር እና በዓለም አቀፍ ማዕቀብ ምክንያት የምርት እጥረት በማጋጠሙ አስከፊ የሆነ የምግብ ቀውስ እንደሚከሰት አስጠንቅቀው ነበር።
ከደቡብ ኮሪያ ባለሥልጣናት የተገኘ የሳተላይት ምስል እንደሚያሳየው ሰሜን ኮሪያ በ2022 ከ180 ሺህ ቶን ያነሰ ምግብ ያመረተች ሲሆን ይህም ከቀደመው ዓመት ጋር ሲነጻጸር ዝቅተኛ ነው።
ሐሙስ ዕለት የአሜሪካ ግምጃ ቤት በሰሜን ኮሪያ እና በሩሲያ መካከል እንደ ደላላ ሆኖ ሲያገለግል ነበር የተባለ ስሎቫኪያዊ ግለሰብን በጥቁር መዝገብ ላይ መዝግቧል።
ግምጃ ቤቱ እንዳለው የ56 ዓመቱ ግለሰብ አሾት ሚክርይቼቭ፣ በ2022 መጨረሻ እና በ2023 መጀመሪያ ላይ ሰሜን ኮሪያ ወደ ሩሲያ መሣሪያ ለመላክ የሚያስችላትን ስምምነት ሲያስተባብር እና ሽያጭ ሲያመቻች ነበር።
በምላሹም ፒዮንግያንግ ጥሬ ገንዘብ፣ አውሮፕላን፣ ቁሳቁሶችና ጥሬ እቃዎችን ተቀብላለች ብሏል።
በማዕቀብ ጥቁር መዝገብ ውስጥ መግባት ማለት የአሜሪካ የንግድ ተቋማት ከሚክሪቼቭ ጋር ግንኙነት እንዳይኖራቸው የሚያደርግ ሲሆን በአሜሪካ ያሉት ንብረቶቹ በሙሉ እንዲታገዱ ያደርጋል።
የምዕራባውያኑ ማዕቀብ ሩሲያ በዩክሬን ጦርነት የተጠቀመችውን እና የወደሙባትን የጦር መሣሪያዎች ለመተካት የሚያስችላት አቅም ላይ ከፍተኛ ተጽዕኖ አሳድሯል።
ከዚህም በተጨማሪ ማዕቀቡ ሩሲያ የጦር መሣሪያ ለማግኘት ፊቷን ወደ ሌሎች አገራት እንድታዞር አስገድዷታል።
ባለፈው ዓመት ታኅሥሣ ወር ላይ አሜሪካ ኢራን ዋና የሩሲያ ጦር ደጋፊ መሆኗን ገልጻ ነበር።