የአሜሪካው ፕሬዝዳንት በምድርና በአየር የሚጓዙባቸው ተሽከርካሪዎች ምስጢራት

ታትሟል

የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ጆ ባደን ለመጀመሪያ ጊዜ ወደ ባህር ማዶ ጉብኝታቸው ለቡድን 7 ስብሰባ ወደ ዩናይትድ ኪንግደም ተጉዘው ከዚያም ወደ ሌሎች ጉብኝቶች አቅንተዋል።

ባይደን አውሮፓ ውስጥ ለስምንት ቀናት እንደሚቆዩ ተነግሯል። በፕሬዚዳንትነት የመጀመርያውን የኔቶ ጉባኤ መሳተፍን ጨምሮ የሩሲያው ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲንን በጄኔቫ ላይ ያገኛሉ።

በዚህ ሁሉ ሂደት ባይደን በቀላሉ ከቦታ ቦታ አይጓዙም። የአሜሪካው ፕሬዝዳንት በደኅንነት እና በምቾት በመሬት እና በአየር ላይ ለመንቀሳቀስ የሚረዱ ልዩ ልዩ ተሽከርካሪዎች አሏቸው።

ከፕሬዝዳንቱ አውሮፕላን ኤር ፎርስ ዋን የበለጠ ጥሩ ምሳሌ የለም።

የዋይት ሐውስ ድረ ገጽ እንሚያብራራው ከሆነ ኤር ፎርስ ዋን የሚለው መጠሪያ የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ለተሳፈሩበት የትኛውም የአየር ኃይል አውሮፕላን በአየር ትራፊክ ቁጥጥር ባለሙያዎች የተሰጠ መለያ ነው።

መጠሪያው በአብዛኛው ጥቅም ላይ የሚውለው ለሁለቱ ታዋቂ ነጭ እና ሰማያዊ አውሮፕላኖች ነው። በልዩ መልኩ የተጣጣሙ የቦይንግ 747-200B አውሮፕላኖች ሲሆኑ የመለያ ኮዳቸውም 28000 እና 29000 ነው።

አውሮፕላኖቹ የተራቀቁ የግንኙነቶች፣ የመከላከያና ሌሎች ብቃቶች አላቸው። የእሳት አደጋን ጨምሮ ከኤሌክትሮማግኔቲክ ቁሶችች መከላከያ እና የሙቀት-ፈላጊ ሚሳኤሎችን ለመከላከል የሚያስችሉም ናቸው። ይህ ማለት በአሜሪካ ላይ አውዳሚ ጥቃት ቢሰነዘር ፕሬዝዳንቱ ከርቀት ማዘዣ ማዕከል ሆነው መሥራት ይችላሉ።

በአየር ላይ ነዳጅ የመሙላት ችሎታ ስላላቸው በንድፈ ሃሳብ ደረጃ አውሮፕላኖቹ ያልተገደበ በአየር ላይ የመቆየት አቅም አላቸው።

አውሮፕላኑ በውስጡ በሦስት ደረጃዎች የተከፋፈለ 372 ካሬ ሜትር የወለል ቦታ አለ። ከፕሬዝዳንታዊ መሰብሰቢያ በተጨማሪ ለአማካሪዎች፣ ለደኅንነት ጥበቃ መኮንኖች፣ ለጋዜጠኞች፣ የህክምና መስጫ እና የምግብ ማብሰያ ቦታም አለው።

ለአጭር ጉዞዎች ፕሬዚዳንቱ ሄሊኮፕተሮችን ይጠቀማሉ። ይህም በአብዛኛው በአረንጓዴ የውጭ ክፍሉና በነጭ የአናት ቀለሙ የታወቀ ነው።

'ማሪን ዋንም' አንድ ሄሊኮፕተር ብቻ አይደለም። የአሜሪካ ፕሬዝዳንትን የሚያጓጉዘው የባሕር ኃይል አውሮፕላን ስም ሲሆን ብዙውን ጊዜ የሚያመለክተው ቪኤች-3ዲሲ ኪንግ ወይም ቪኤች-60ኤን ዋይት ሃውክን ነው።

የማሪን ዋን የ'ዲኮይ' ስሪቶች ብዙውን ጊዜ ከፕሬዝዳንቱ ሄሊኮፕተር ጋር ይብራሉ። 'ግሪን ቶፕ' በመባል የሚታወቀው ኦስፕሬ ኤምቪ-22ን ጨምሮ በአጃቢ አውሮፕላኖች በአየር ላይ ብዙውን ጊዜ ይበራል።

ሳይንደረደሩ መነሳት እና ማረፍ የሚችሉ ሲሆን የሄሊኮፕተርን ተግባራት ከትርቦፕሮፕ አውሮፕላን ክልል ጋር ለማጣመር የተዘጋጁ ናቸው።

ባይደን ከበረራ በኋላ ፕሬዝዳንት ባይደን አብዛኛውን ጊዜ ከአየር ኃይል አንድ ወይም ከባህር ኃይል ወደ ካዲላክ ቢስት [የፕሬዝዳንቱ መኪና] ይተላልፋሉ።

5.5 ሜትር ርዝመት ያለው 'ዘ ቢስት' የተባለው የፕሬዝዳንቱ ልዩ ተሽከርካሪ ሰባት ሰዎችን መያዝ የሚችል ሲሆን፤ ድንገተኛ አደጋ በሚከሰትበት ጊዜ ከፕሬዚዳንቱ የደም ዓይነት ጋር የሚመሳሰል ደም የያዘ ፍሪጅን ጨምሮ ሰፊ የህክምና አቅርቦቶች አሉት።

አዲሱ የቢስት ስሪት በአውሮፓውያኑ 2018 ይፋ ተደርጓል። አምራቹ ጄኔራል ሞተርስ እና የፕሬዝዳንቱ የደኅንነት ጥበቃ አገልግሎት (ሴክሬት ሰርቪስ) ስለ መኪናው ልዩ የደኅንነት ባህሪያት ብዙም አይናገሩም።

ነገር ግን ዘገባዎች እንደሚያመለክቱት ክብደቱ ወደ ዘጠኝ ሺህ ኪሎ ግራም ይመዝና። እንደጋሻ የሚያገለግል አካል እና ጥይት ተከላካይ መስታወቶች አሉት።

አስለቃሽ ጋዝ የእጅ ቦምብ ማስተኮሻ፣ የሌሊት መመልከቻ ካሜራዎች እና አብሮት የተሠራ የሳተላይት ስልክ እንዳለው ይነገራል። የተሳፋሪው መቀመጫ የታሸገ እና ጎማዎቹም እጅግ ጠንካራ ከመሆናቸው የተነሳ ተንፍሰወ እንኳን መንቀሳቀስ ያስችላሉ።