ኬንያ ከሰሃራዊ አረብ ዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ጋር ግንኙነቷን ማቋረጧን አስታወቀች

ማክሰኞ የተሾሙት የኬንያው አዲሱ ፕሬዘዳንት ዊልያም ሩቶ

የፎቶው ባለመብት, William Ruto / Twitter

ታትሟል

ከተሾሙ ቀናትን ያስቆጠሩት የኬንያው ፕሬዘዳንት ዊልያም ሩቶ አገራቸው ከሰሃራዊ አረብ ዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ (ሳዲአር)ጋር ያላትን ግንኙነት ማቋረጧን ገለጹ።

ፕሬዚዳንቱ ትላንት ረቡዕ በትዊተር ገጻቸው ላይ ይህንኑ መልዕክት አስፍረው የነበረ ሲሆን ከሰአታት በኋላ ግን ልጥፉን አንስተዋል።

የቀድሞ የስፔን ቅኝ ግዛት የነበረው ይህ የምዕራብ ሰሃራ አካባቢ እ.ኤ.አ በ1975 ከቅኝ ግዛት ከተላቀቀ በኋላ ሞሮኮ ግዛቴ ነው በሚል በቁጥጥሯ ስር ለማድረግ ሙከራዎችን አድርጋለች።

ከዚያን ጊዜ ጀምሮ የሰሃራዊ ነባር ሕብረተሰቦች እና የሞሮኮ መንግስት መካከል ዘላቂ የግጭት ምክንያት ሆኖ ዘልቋል።  

ታዲያ የኬንያ አዲሱ ፕሬዘዳንት ዊሊያም ሩቶ ሰሃራዊ አረብ ዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ በኬንያ ያላትን ሕጋዊ ቆይታ እና ግንኙነት እንዲያበቃ ለማድረግ እርምጃዎች መጀመራቸውን ተናግረዋል።  

በምዕራብ ሰሃራ ያሉትን ያለመግባባቶች ዘላቂ መፍትሄ የሚያገኙት የተባበሩት መንግስታት በሚያዘጋጀው ማዕቀፍ ብቻ ውስጥ ነው ብላ ኬንያ እንደምታምንም ተናግረዋል።

የሰሃራዊ አረብ ዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ መሪ ብራሂም ጋሃሊ ማክሰኞ በተካሄደው የፕሬዚዳንት ዊሊያም ሩቶ በአለ ሲመት ላይ ተገኝተው ነበር።

ፕሬዘዳንት ሩቶ ይህንን ውሳኔያቸውን ይፋ ያደረጉት የሞሮኮው ንጉስ መሀመድ ስድስተኛ የእንኳን ደስ አለዎት መልዕክት ከደረሳቸው ከጥቂት ሰአታት በኋላ ነበር።

ከአርባ አመታት በላይ ሕጋዊ ቅቡልነት ያላት አገር ለመሆን እየሰራች የምትገኘው ሰሃራዊ አረብ ዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ የአፍሪካ ሕብረት ሙሉ አባል ስትሆን በርካታ አገራት ዕውቅና ሰጥተዋታል። በአሁን ሰአትም ከፊል ቅቡልነት ያላት አገር ናት።

ሞሮኮ በበኩሏ ምዕራብ ሰሃራ ግዛቴ ነው የሚል ጠንካራ አቋሟን የምታራምድ ሲሆን በአካባቢው የሚኖሩ ሕዝቦች ፍላጎታቸውን እንዲያሳዩ የሕዝበ ውሳኔ ይደረግ የሚለውን ሃሳብም አትቀበልም።

ይህ የሰሀራ በረሃ አካል የሆነው ክፍል እስካሁን ድረስ ያልተነካ የነዳጅ ዘይት ክምችት ያለበትን የባሕር ክፍል እንደሚይዝ ይታመናል። ከዛም ባሻገር ከፍተኛ የፎስፌት ክምችት ያለው ሲሆን በአሳ ሃብቱ የበለጸገ ነው።