ሰርጌይ ላቭሮቭ የሚጎበኟት ማሊ ከፍተኛ የተባበሩት መንግሥታት ባለሥልጣንን አባረረች

ታትሟል

የሩሲያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሰርጌይ ላቭሮቭን ዛሬ ተቀብለ የምታስተናግደው ማሊ፤ አንድ ከፍተኛ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ባለሥልጣንን ከአገሯ አባረረች።

የማሊ ወታደራዊ መንግሥት የተባበሩት መንግሥታት ሰላም አስከባሪ ኃይል የሰብዓዊ መብቶች ኃላፊ የሆኑት ጉኢላኡሜ ናጌፋ-ኣንቶዶኮ አንዳሊ አገሪቱን ጥለው እንዲወጡ አዛላች።

አንዳሊ የተባሉት የተመድ ከፍተኛ ኃላፊ በ48 ሰዓታት ውስጥ አገሪቱን ለቅቀው እንዲወጡ የታዘዙት በመንግሥታቱ ድርጅት የፀጥታው ምክር ቤት ስብሰባ ላይ የማሊን ሉዓላዊነት ዝቅ አድርገዋል በሚል ነው።

ግለሰቡ በፀጥታው ምክር ቤት ማሊን በተመለከተ በቀረበ ገለጻ ላይ የመረጧቸው የዐይን እማኞችን የማሊን ሥልጣን የሚያጥላላ ነው ብሏል የአገሪቱ መንግሥት የድርጅቱን ኃላፊ መባረር ይፋ ባደረገበት መግለጫ።

ባለፈው ወር አንድ የማሊ ሲቪል ሶሳይቲ ቡድን የማሊ መንግሥት አጋር የሆኑት የሩሲያ ጦር አባላት በአገሪቱ ፈጽመውታል ያለውን የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች ለፀጥታው ምክር ቤት አቅርቦ ነበር።

ምዕራብ አፍሪካዊቷን አገር የሚያስተዳድረው ወታደራዊ መንግሥት የተመድ ከፍተኛ ኃላፊን ማባረሩን የተገለጸው የሩሲያው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሰርጌይ ላቭሮቭ ለጉብኝት ወደ አገሪቷ እንደሚያቀኑ በተገለጸበት ወቅት ነው።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ዛሬ ሰኞ ጥር 29/2015 ዓ.ም. ለሁለት ቀናት የሥራ ጉብኝት ማሊ ይገባሉ ተብሎ ይጠበቃል።

ላቭሮቭ ወደ ማሊ የሚያቀኑት በሁለቱ አገራት መካከል የመከላከያ እና የደኅንነት ትስስራቸውን ለማጠናከር ነው ተብሏል።

ላቭሮቭ በሁለት ቀናት ቆይታቸው በመፈንቅለ መንግሥት ሥልጣን ላይ ከወጡት አሲሚ ጎይታ ጋር ተገናኝተው ይነጋገራሉ ተብሏል።

ዋግነር የተባለው ቅጥረኛ የሩሲያ ወታደራዊ ቡድን በማሊ ከተሰማራ በኋላ በማሊ ውስጥ ያለው የሞስኮ ተጽእኖ በከፍተኛ ሁኔታ እንደጨመረ ይነገራል።

የዚህ ቡድን አባላት በክፍያ የሚሰጧቸውን ወታደራዊ ኃላፊነት ሲፈጽሙ ከፍተኛ የሰብዓዊ መብት አና ዓለም አቀፍ ሕግጋትን ይጥሳሉ ተብለው ይወቀሳሉ።

ዋግነር የተሰኘው ይህ የቅጠረኛ ተዋጊዎች ቡድን በሶሪያ፣ በሞዛምቢክ፣ በሱዳን፣ በሊቢያ እና በማዕከላዊ አፍሪካን ሪፐብሊክ እና በማሊ ወታደራዊ ተልዕኮዎችን ገንዘብ ተቀብሎ ስለማስፈሙ ምዕራባውያን ይናገራሉ።

ሩሲያ በበኩሏ ከዚህ ቡድን ጋር ምንም አይነት ግንኙነት አንደሌላት ትገልጻለች። ሞስኮ ዋግነር የተሰኘው የግል ወታደራዊ ኩባንያ ከማንኛውም የመንግሥት አካል ጋር ግንኙነት የለውም ስትል እራሷን ታርቃለች።

በቀጠናው ጸንፈኛ ቡድኖችን ለመዋጋት ወታደሮቿን አሰማርታ የነበረቻው ፈረንሳይ ከማሊ ወታደራዊ አስተዳደር ጋር በገባችው እሰጣገባ ሠራዊቷን ከቀጠናው ማስወጣቷ ይታወሳል።

በዚህ ላቭሮቭ ፈረንሳይ ወታደሮቿን በማስወጣቷ በሳህል ቀጠና የደኅንነት ክፍተት እንዲፈጠር አድርጋለች ማለታቸውን ተከትሎ፣ ማሊ የተፈጠረውን ክፍተት ሞስኮ እንድትሞላ ጥያቄ አቅርቧል።

ላቭሮቭ ከሳምንት በፊት ሳምንታት ወደ አፍሪካ አህጉር በመምጣት በደቡብ አፍሪካ፣ በአንጎላ፣ በኢስዋቲኒ እና በኤርትራ ጉብኝነት አድርገው ነበር።